ዛሬ የዓለም አቦ ሸማኔዎች ቀን ነው፤ፈጣኖቹ እንስሳት በፍጥነት ከሀገራችን ሳይጠፉ እንታደጋቸው
(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም)
በየዓመቱ በዛሬው ቀን የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የአቦ ሸማኔዎች ቀን አስመልክቶ ፈጣኖቹን እንስሳት እንታደግ ሲል የጥፋት ምክንያታቸውንና ዓለም አቀፍ እውነታቸውን እንዲህ ይተርክልናል፡፡)
(ከሄኖክ ስዩም በድሬ ቲዩብ)
ዓለም የስልጣኔው ጫፍ ደርሶም ከተፈጥሮ መታረቁ ከብዶታል፡፡ የስልጣኔ ድካም ፍሬውን እንዳይበላ ያወደመው ተፈጥሮ እያወደመ አሰቃይቶታል፡፡ በዚህ ጥፋት በበዛበት ዓለም ለመጥፋት ከደረሱት አውሬዎች አንዱ አቦ ሸማኔ ነው፡፡
አቦ ሸማኔ የዓለም ፈጣኑ ሯጭ እንስሳ ነው፡፡ የብስ ላይ አድኖ ከሚበላ ፍጥረት ማንስ እንደ እሱ ይሮጣል የተባለለት፡፡ ፈጣኑ እንሰሳ በፍጥነት ከምድራችን እየጠፋ ነው፡፡ እንደ መንግስታቱ ድርጅት ሪፖርት በመላው ዓለም ዱር ውስጥ የሚገኘው የአቦ ሸማኔ ቁጥር ሰባት ሺህ ገዳማ ነው፡፡
ቀድሞ ከመካከለኛው ምሥራቅ እስከ ሕንድ ጫፍ የትምና ማንም የሚያውቀው፤ በአፍሪቃ ሜዳዎች የሚምዘገዘገው አቦ ሸማኔ ዛሬ በዓለም ከፍተኛና እጅግ አሳሳቢ በኾነ ደረጃ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበት ዝርዝር ውስጥ የገባ እንሰሳ ተብሏል፡፡
ህንድ አቦ ሸማኔዋን ያጣችው በአንድ ጎልማሳ እድሜ ነው፡፡ አፍሪቃም እንዲሁ ከቀን ቀን የአቦ ሸማኔዋን መጠን ወደ አለመኖር እየወሰደችው እንደሆነ የአቦ ሸማኔ ጥበቃ ዓለም አቀፍ ተቋም መረጃ ያመላክታል፡፡
በሰዓት 120 ኪሎ ሜትር የሚሮጠው አቦ ሸማኔ በፍጥነት በሚሮጥበት ክስተት ውስጥ እንደ አሞራ ምድር ለቆ የሚቀዝፍ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡ የእንባ መውረጃ በመሰሉ ጥቁር ከዓይኖቹ ወደ ከንፈሩ በሚወርዱ መስመሮች ከቤተሰቦቹ በቀላሉ የሚለየው ፍጥረት በኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ እየጠፋ ያለ እንሰሳም ነው፡፡
ቀደምት የኢትዮጵያ አባቶች በአቦ ሸማኔ ጥበቃ ከዓለም ረቀቅ ያለ ስልትን ጭምር የሚከተሉ እንደነበር ሰነዶች ይነግሩናል፡፡ በተለይም ከቅዱሳን አባቶች መንፈሳዊ ተጋድሎ ጋር ተያይዞ አቦ ሸማኔ የሚገደል እንስሳ ሳይሆን የአባቶች የታጋድሎ አጋር እንደሆነ አንብበናል፡፡
ከቅዱሳኑ ጋር ሳይቀር መነጋገር ይችል እንደነበር የሚነግሩን ገድሎች ዛሬ ዓለም ጭምር ፈተና ውስጥ ከገባበት የጥበቃ ስራው ጋር ስናነጻጽረው ብዙ የምንማርበት ይሆናል፡፡
የአቦ ሸማኔ የጥፋት ምክንያት ከሚባሉት ውስጥ ከሰው ጋር የሚገባበት ግጭት አንዱ ነው፡፡ ያም ቢኾን የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ከመታረቅ ስልጣኔውንና ንቃቱን ተጠቅሞ የሚያደርሰው ጥቃት ውጤት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ መኖሪያውን ማሳጣት ነው፡፡
የከተማ መስፋፋት፣ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ አለመገንባት፣ የተፈጥሮ ጥበቃ ባህል መውደቅና መሰል ተግባራት በአቦ ሸማኔዎች መኖሪያ ላይ ጉዳት ሲያደርስ አብሮ የሚጎዳው ፍጥረት ቁጥሩ እየቀነሰ መጥፋት አፋፍ ደረሰ፡፡
ደግሞ የመካከለኛው ምስራቅ ሁሉን በገንዘብ የመግዛት በሽታ የአፍሪቃ አቦ ሸማኔዎች ከነ ሕይወታቸው እንዲሸጡ ሌላ የዚህ ዘመን ምክንያት ኾነ፡፡ የዚህም ውጤት በአያያዝና በጉዞ ወቅት ከሚሞተው ቁጥር በላቀ ድርጊቱ እንደ ገቢ ምንጭ የሚጠቀመው አዳኝ የአቦ ሸማኔ ጥፋት ማስፈጸሚያ ለመሆን በቃ፡፡
ህገ ወጥ አደኑና ውጤቱን ለመጠቀም መፈለጉም ሌላው ምክንያት ነው፡፡ ይኼ ሁሉ ተዳምሮ ግን አሁን አቦ ሸማኔ ዓለምን ያስጨነቀ የስስት ተፈጥሮ እስከመሆን ደርሷል፡፡ የራሳችንን አቦ ሸማኔዎች ስንታደግ፤ የዓለምን እንታደገለንና፤ ትኩረት ለአቦ ሸማኔ፡፡