Connect with us

የህወሓት ዕጣ ፈንታ ለሚያሳስባቸው

የህወሓት ዕጣ ፈንታ ለሚያሳስባቸው
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

የህወሓት ዕጣ ፈንታ ለሚያሳስባቸው

የህወሓት ዕጣ ፈንታ ለሚያሳስባቸው

(እሱባለው ካሳ)

ሰሞኑን ለመንግስት ኃይሎች እጇን የሰጠችው የህወሓት ከፍተኛ አመራር ወ/ሮ ኬርያ ኢብራሂም “ተሸንፈናል” ስለማለቷ በማህበራዊ ድረገጾች ሲንሸራሸር ተመልክቻለሁ፡፡ ቃሉን ሴትየዋ ብትለውም፤ ባትለውም የህወሓት ሽንፈት እውነት ነው፡፡ ህወሓት ደርግን ስለማሸነፉ ብቻ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ እንደዘመረ፣ እንደሸለለ፣ እንደፎከረ ተፈጥሮአዊ ሞቱን ለመጎንጨት ተገድዷል፡፡

ብዙዎች ህወሓት “ለምን በአሸባሪነት አይፈረጅም” ማለት የጀመሩት ከጦርነቱ በፊት ጀምሮ ነው፡፡ ይህ ድምጽ እየጎላ ለመምጣቱ አንድ አስረጂ የሚሆነው በፓርላማ አባላት ደረጃ ለጠ/ሚኒስትሩ መቅረቡ ነው፡፡ ለነገሩ ፓርላማው ስልጣኑ የማያውቅ ሆኖ እንጂ ሕግ አርቅቆ ህወሓትን በአሸባሪነት መፈረጅ በእጁ ያለ ስልጣን ነበር፡፡

 ሌሎች ደግሞ ፊታቸውን ወደምርጫ ቦርድ በማዞር ለምን ከፓርቲ ዝርዝር ውስጥ አያሰናብተውም በሚል የሚጠይቁ አሉ፡፡ በተለይ ህወሓት ሕግ ጥሶ የራሱን ክልላዊ ምርጫ ቦርድ አቋቁሞ ምርጫ እስከማካሄድ የሄደበት ርቀት ከህጋዊ ፓርቲነት ለማሰረዝ ከበቂ በላይ ምክንያት ነው በሚል የሚሞግቱ ብዙዎች ናቸው፡፡ ያም ሆነ ይህ በገዥው ፓርቲ ብልጽግና በኩል እነዚህ ጥያቄዎች አልተሰሙም፡፡ ለምን? የግል መላልምቴን ላስቀምጥ፡

ምንም ቢሆን ህወሓት ኢህአዴግ ነበር፤ ያውም የኢህአዴግ ወላጅ አባት፡፡ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት  በዚህች ሀገር ለተፈጠሩ ችግሮች ሁሉ መቶ በመቶ ኃላፊነት ብቻውን ሊወስድ አይችልም፡፡ ሌሎቹና በአሁን ሰዓት ብልጽግና ውስጥ ገብተው የከሰሙት የቀድሞዎ አዴፓ፣ ኦዴፓ እና ደኢህአዴን የድርሻቸውን ያነሳሉ፡፡ እና በአጭሩ ህወሓትን አሸባሪ ድርጅት ብለህ ስትፈርጅ እነአዴፓ እና ኤዴፓንም አሸባሪዎች ናቸው እያልክ ነው፡፡

በዚህ ደረጃ የተጠያቂነት መስመር ስትዘረጋ መስመሩ ስቦ ስቦ ሌሎቹ ጋርም መውሰዱ እንደማይቀር የብልጽግና ሰዎች በሚገባ ተረድተውታል፡፡ እናም ህወሓት በራሱ ተፈጥሮአዊ ሞቱን እንዲያጣጥም ትተውታል፡፡ ይህ ምን ማለት ነው?

አዎ!.. ህወሓት በአሸባሪነት ባለመፈረጁ፣ በምርጫ ቦርድ ባለመሰረዙ ሕጋዊነቱ አሁንም አለ፡፡ ዘንድሮ በሚካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ በወንጀል ከሚፈለጉት በስተቀር እንደፓርቲ ቀርቦ መወዳደር ይችላል፡፡ ግን ጥያቄው ከዚህ ሁሉ ምስቅልቅል በኋላ፣ ከዚህ ሁሉ ቀውስ በኋላ ህወሓት የትግራይን ሕዝበ እወክላለሁ ብሎ ለመቆም ሞራል ያገኛል ወይ የሚለው የመጀመሪያ ጥያቄ ነው፡፡

እስቲ ይህንን አልፎ ሞራል አግኝቶ ወደምርጫ ቢመጣ በትክክለኛ ምርጫ ሰሞኑን እንዳደረገው 98 በመቶ አይደለም፤ 10 በመቶ ወንበር ማግኘት ይችላል ወይ የሚለው በጥያቄ መልክ የሚነሳ ነው፡፡ ለምን ቢባል ጦርነቱ ብዙ ዋጋ አስከፍሎታል፡፡ ደም ገብሬአሁ፣ ታግዩበታለሁ የሚለው ዓላማ ገና በጠዋቱ አንኮታኩቶት ራሱን የሙስና ባህር ውስጥ ወርውሯል፡፡

መልካም ስሙ የሚያጠለሹና ሕዝባዊ ነኝ የሚል የአንገት በላይ ዲስኩሩን ገደል የሚከቱ ወንጀሎችን ለአመታት ፈጽሟል፡፡ እናም ህወሓትን የሚረከብ አዲስ ትውልድ ማግኘት ሊቸግር ይችላል፡፡ ቢገኝ እንኳን ሕወሓትን አምኖ አብሮት የሚሰለፍ ሕዝብ ማግኘት ይከብደዋል፡፡

ዛሬ የትግራይ ሕዝብ ቢሆን እውነታውን በመረዳቱ እንደቀድሞ ጎሮ ወሸባዬ ሊልለት እንደማይችል የታወቀ ነው፡፡ ደግሞም ምርጫ ውስጥ ቢገባም በማጭበርበር ወንበር ማግበስበስ የለመደ ፓርቲ በነጻና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተዘርሮ መወደቁ አይቀሬ ይሆናል፡፡ እነሆ ይኸ መንገድ አይቀሬውን የህወሓት ግብዐተ መሬት የሚፈጽም ይሆናል፡፡

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top