Connect with us

ለሀገራችን የመጀመሪያ የሆነው የካንሰር የጨረር ህክምና ማሽን በጥቁር አንበሳ ሆ/ል ሥራ ጀመረ

ለሀገራችን የመጀመሪያ የሆነው የካንሰር የጨረር ህክምና ማሽን በጥቁር አንበሳ ሆ/ል ሥራ ጀመረ
Ethiopian Broadcasting Corporation

ዜና

ለሀገራችን የመጀመሪያ የሆነው የካንሰር የጨረር ህክምና ማሽን በጥቁር አንበሳ ሆ/ል ሥራ ጀመረ

ለሀገራችን የመጀመሪያ የሆነው የካንሰር የጨረር ህክምና ማሽን በጥቁር አንበሳ ሆ/ል ሥራ ጀመረ

የካንሰር ህመምን በጨረር በማከም ዘርፍ እጅግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሆነዉ /Linear Accelerator /LINAC/ የተባለዉ ህክምና መሳሪያ ወደ ኢትዮጵያ በመግባቱና በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል  ዉስጥ አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸዉ የቀድሞዋ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ ገለጹ፡፡   ለሀገራችን የመጀመርያ የሆነዉ Linear Accelerator የጨረር ህክምና ማሽን ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬን ጨምሮ ዶ/ር ሊያ ታደሰ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የጤና ሚኒስትር፣  የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት፣ዶ/ር ይርጉ ገብረህይወት የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል  የክሊኒካል አገልግሎት ዳይሬክተር፣ ዶ/ር ዳዊት ወንድማገኝ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ስራ አ ስፈጻሚ ዳይሬክተር እንዲሁም ሌሎች እንግዶችና የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ኅዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም ተመርቋል፡፡

በታካሚዎች ላይ ተዛማጅ ጉዳቶችን በማያስከተል መልኩ የካንሰር በሽታን በማከም አስተማማኝ ዉጤት ለማምጣት የሚያስችለዉ Linear Accelerator ማሽን በሀገራችን አገልግሎት ላይ ባለፉት በርካታ አመታት ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች በተለይም ለካንሰር በሽታ ትኩረት እንዲሰጥ የተሰሩት የአድቮኬሲ፣ የአመራርና ፕሮግራም ተኮር ስራዎች ፍሬ የማፍራታቸዉ አንዱ ማሳያ መሆኑን ወ/ሮ ሮማን ገልጸዋል፡፡ ” የጨረር ህክምና መጀመሩ የካንሰር ህክምና አቅማችንን የሚያጎለብት ከመሆኑም በላይ ረዥም የህክምና ወረፋ የመጠበቅያ ጊዜን  በእጅጉ  የሚያሳጥር በመሆኑ በሺዎች ለሚቆጠሩ ባካንሰር ህመም ለሚሰቃዩ ዜጎቻችንና ቤተሰቦቻቸዉ ታላቅ የምስራች ነዉ” ብለዋል ወ/ሮ ሮማን፡፡

የካንሰር በሽታን በመከላከልና ህክምናዉንም ተደራሽ በማድረግ ረገድ ከተገኙት ዉጤቶች ዉስጥ ብሔራዊ የካንሰር መቆጣጠር ስትራቴጂ በጤና ሚኒስቴር ተቀርጾ በትግበራ ላይ መዋሉ፣ በ600 ወረዳዎች ዉስጥ የማህጸን ጫፍ ካንሰር ቅድመ ምርመራ እና ህክምና አግልግሎት ተደራሽ መደረጉ እንዲሁም የሀገሪቱ የካንሰር ህክምና ባለሞያዎች (oncologists) ቁጥር በጥቂት አመታት ዉስጥ ከአራት ወደ ሃያ ከፍ ማለቱ ተጠቃሽ መሆናቸዉን  የገለጹት ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ ስራዉን በማስተባበር የሚመራዉን የጤና ሚስቴርን እንዲሁም የብሔራዊ ካንሰር ኮሚቴዉንና  አጋር ድርጅቶችን ለሰጡት ትኩረትና ድጋፍ አመስግነዋል፡፡  

በቀጣይም ቀድሞ በተያዘዉ እቅድ መሰረት በሌሎች አምስት የክልል ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች ዉስጥ Linear Accelerator የጨረር ህክምና መሳርያዎች ተተክለዉ በቅርቡ ለታካሚዎች አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ እንዲሁም የብሔራዉ የካንሰር መቆጣጠር ስትራቴጂዉ የእስከዛሬ ትግበራ ተመዝኖና ወደፊትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል  አሳስበዋል፡፡   

ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ  በሀገራችን ገዳይነቱ ከቀን ወደቀን እየተባበሰ የመጣዉን የካንሰር በሽታን በተለይም ለሴቶች ሞት ከተቀዳሚ ምክንያቶች ተርታ የሚሰለፉትን የማህጸን ጫፍና የጡት ካንሰርን ለመከላከልና ህክምናዉን በመላ ሀገራችን ተደራሽ ለማድረግ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከክልል የጤና ቢሮዎች፣ ከብሔራዊ የካንሰር ኮሚቴና በርካታ የሀገር ዉስጥና የዉጭ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ጠንካራ የአመራርና የአድቮኬሲ ስራዎችን ሲያከናዉኑ እንደቆዩ  ይታወቃል፡፡ 

በካንሰር መከላከልና ህክምና ዙርያ የጀመሩዋቸዉ ስራዎች በኃይለማርያምና ሮማን ፋዉንዴሽን የእናቶችና ህጻናት ጤና ፕሮግራም ዉስጥ ተካተዉ የቀጠሉ ሲሆን በዘርፉ ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦና የጠራ አመራርም በ2009 ዓ.ም በአሜሪካ ከካንሰር ሶሳይቲ የእዉቅና ሽልማት እንደተሸለሙ ይታወሳል፡፡

(ኃይለማርያምና ሮማን ፋዉንዴሽን)

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top