Connect with us

ከጦርነቱ በኋላ ያለው ተስፋና ስጋት

ከጦርነቱ በኋላ ያለው ተስፋና ስጋት
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ከጦርነቱ በኋላ ያለው ተስፋና ስጋት

ከጦርነቱ በኋላ ያለው ተስፋና ስጋት

(በፍቱን ታደሰ)

ለአስራ ሰባት አመታት የትጥቅ ትግል አድርጋ የገዥነት መንበርን የተቆናጠጠችው ህወሓት በ17 ቀን ጦርነት ግብዓተ መሬቷ ተፈፅሟል፡፡ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም እኩለ ሌሊት ላይ በመከላከያ ሠራዊት የሰሜን እዝ ላይ “መብረቃዊ” ብለው ያገነኑትን ጥቃት በመፈጸም የለኮሱት የጦርነት እሳት በሁለት ሳምንት ውስጥ እራሳቸውን    ዶግ አመድ አድርጓቸው ተጠናቋል፡፡

ህዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት መከላከያ ሠራዊት መቀሌን በድል መቆጣጠሩን ያበሰረውን ሰበር ዜና ተከትሎ የኤፌዴሪ ጠቅላይ ኤታማጆር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ጦርነቱ በድል መጠናቀቁንና ውጊያው ማብቃቱን ተናግረዋል፡፡ በዚህ የድል ብስራት በባህር ዳር ከተማ ሌሊቱን ህዝቡ አደባባይ ወጥቶ ደስታውን ሲገልጽ አድሯል፡፡ 

በባሌ ሮቤ፣ በአዲስ አበባና በሌሎች የሃገራችን ክፍሎች ህዝቡ ደስታውን በመግለጽ ላይ ይገኛል፡፡ ሠራዊታችን መቀሌን የተቆጣጠረ ቢሆንም የህወሓት አመራሮች መቀሌ ውስጥ አልተገኙም፤ፍለጋው ግን ቀጥሏል፡፡

ከድል ዜናው ባሻገር ተስፋ የምናደርጋቸው ነገሮች ያሉትን ያህል ስጋትም አለን፡፡ በዚህ ጦርነት  ህወሓት በመደምሰሱ በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች በተለይ በቤንሻንጉል፣ በጉራፈርዳና በወለጋ በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ የሚፈጸመው የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ይቆማል የሚል ተስፋ አለ፡፡ በህወሓት ከፍተኛ የገንዘብና የመሳሪያ ድጋፍ በተጠቀሱት አካባቢዎች በሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ  ላለፉት 27 ዓመታት በተለይ ደግሞ ከለውጡ በኋላ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ እጅግ በከፋ ሀኔታ ተፈፅሟል፡፡ በበርካታ አካባቢዎች የወረዳና የዞን አመራሮች እቅድ አውጥተው ግድያውን የሚያስፈጽሙበት ሁኔታ ነበር፡፡ 

ለእነዚህ አመራሮች ትዕዛዙ የሚመጣላቸው ከህወሓት ሲሆን እንደ ግድያ አፈጻፀማቸው መጠን የሚያገኙት ጥቅም ይወሰንላቸዋል፡፡ በተለይ በቤንሻንጉልና በጉራ ፈርዳ የዘር ማጥፋት ያስፈጸሙ የክልል የካቢኔ አባላትና የወረዳ አመራሮች ሰሞኑን በቁጥጥር ስር ሲውሉ ከህወሓት ጋር የተጋመዱበትን የጥቅም ቋጠሮ በመፍታት ውሉን ለማግኘት ተችሏል፡፡     

የህወሓት የዘረኝነትና የክፋት ሴራ ገፈት ቀማሽ የሆኑት በዋናነት የአማራ ብሄር ተወላጆች ቢሆኑም በኮንሶ፣ በአርባምንጭ፣ በቅማንት፣ በጌዲኦ፣ በአኙዋክና በአርጎባ ብሔር ተወላጆች ላይ የአማራን ያህል ባይከፋም ግድያና ማፈናቀል ሲፈጸም ነበር፡፡ 

ከህወሓት መደምሰስ በኋላ የዘር ማጥፋት ዘመቻው ዋነኛ ሰለባ የነበሩት የአማራ ብሔር ተወላጆችና ሌሎቹም ከዚህ በኋላ በዘራቸው ምክንያት አይገደሉም፡፡ የሐይማኖት ተቋማትም በየጊዜው ከመቃጠል ይተርፋሉ፡፡ የህወሓት ሴራ በዘር ማጥፋትና ብሔረሰቦችን በማገዳደል ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ የሐይማኖት ግጭት እየቀሰቀሱ ቤተ ክርስቲያናትንና መስጊዶችን ማቃጠል፣ የሃይማኖት አባቶችንና ምዕመናንን በእምነታቸው ምክንያት እንደ ከብት እንዲታረዱ  በማድረግ ለአእምሮ የሚዘገንኑ ተግባራትን ሲፈጽም ነበር፡፡

ከህወሓት ህልፈት በኋላ እንዲህ ያለው መከራ በሃገራችን አይደገምም የሚል ተስፋ አለን፡፡ አሁን የተገኘው ድል ከዚህ በኋላ ዘረኝነትና ጠባብነት ከሃገራችን እንደሚወገዱ ተስፋ አሳድሮብናል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ስጋት የሚያሳድሩ ሁኔታዎች ይታያሉ፡፡ መንግስት በታንክና በድሮን ያባረረውን ህወሓት እስከመጨረሻው ሰንኮፉን የመንቀል ስራ እስካልሰራ ከስጋት ነጻ ለመሆን አይቻልም፡፡ ትግራይ መሽገው የነበሩት የወያኔ መሪዎች ተይዘው ለፍርድ መቅረባቸው አይቀርም፡፡ አንዳንዶቹም በቁጥጥር ስር ለማዋል በሚወሰድ እርምጃ ሊገደሉ ይችላሉ፡፡ ይህ ብቻውን ግን ከስጋት ነጻ ሊያደርግ አይችልም፡፡ ምክንያቱም ወደ ጦርነት ከመግባታቸው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ አቶ ስዬ አብረሃ፣ ጄኔራል ፃድቃን ገብረትንሳኤ፣ ጄኔራል አበበ ተ/ኃይማኖት (ጆቤ) እና ሌሎች የህወሃት የቀድሞ አመራሮች ከሃገር ወጥተው ወደ አሜሪካ ሄደዋል፡፡ 

በተለይ አቶ ስዬ አብረሃ በመቀሌ ቆይታቸው ወጣቶችን ለጦርነት ሲያነሳሱ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ማይካርዳ ውስጥ በሚኖሩ አማሮች ላይ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ የፈጸሙት “ሳምሪ” በሚል መጠሪያ የሚታወቁት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች ግድያውን ፈጽመው ቀጥታ ወደ ሱዳን የሄዱት በእቅድ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ 

የዘር ማጥፋት ዘመቻውን እቅድ አውጥተውና በማይካድራ አቅራቢያ ከሚገኘው ሳምረ ከሚባለው አካባቢ ወጣቶችን መልምለው ከሃገር የወጡ ሲሆን ግድያውን የፈጸሙትም ወደ ጎረቤት ሃገር የመሄዳቸውን ግጥምጥሞሽ ስንመለከት ህወሓት ከሞተ በኋላም ገዳይ የሆኑ ወራሾች ማዘጋጀቱን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡

ከዚህ ስጋት ነፃ ለመሆን የሚቻለው መንግስት በውጭ ሃገራት የሚገኙትን ነባር የህወሓት አመራሮችና የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽመው ሱዳን የሚገኙትን “ሳምሪ” የተባሉ ወጣቶች ካሉበት ሃገራት ተላልፈው እንዲሰጡት አድርጎ ለፍርድ ሲያቀርባቸው ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ህወሓት በዘረፋ ያከማቸውን ሃብት እየተጠቀሙ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ሰላም መንሳታቸው አይቀሬ ይሆናል፡፡

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top