Connect with us

እንኳን ለእመቤታችን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም አመታዊ የመታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሰን/ አደረሳችሁ!!

እንኳን ለእመቤታችን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም አመታዊ የመታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሰን/ አደረሳችሁ!!
Photo: Social media

ባህልና ታሪክ

እንኳን ለእመቤታችን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም አመታዊ የመታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሰን/ አደረሳችሁ!!

እንኳን ለእመቤታችን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም አመታዊ የመታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሰን/ አደረሳችሁ!!

ስለታቦተ ጸዮን የማናውቀው

(ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት)

የአክሱም ጽዮን ያለቺበት እና እቴጌ መነን ያሠሩት መቅደስ እያፈሰሰ ነው የሚል ዘገባ በመውጣቱ አንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙኃን ታቦተ ጽዮንን ለማየት ዕድል ይፈጥራል እያሉ ማውራት ጀምረዋል፡፡

ይህ ሁሉ የተዛባ ዘገባ የአክሱም ጽዮንን እና የአክሱም ሕዝብን ጠባይ ካለማወቅ የመነጨ ይመስለኛል፡፡ በዘመናዊ ታሪካችን የአኩስም ጽዮን ከነበረችበት መቅደስ ስትንቀሳቀስ ይህ የመጀመርያዋ አይደለም፡፡ በዐፄ ፋሲል ዘመን ከተሠራው ማረፊያዋ እቴጌ መነን ወዳሠሩት ማረፊያ ከሃምሳ ዓመታት በፊት ተንቀሳቅሳለች፡፡ አንዳንድ ሚዲያዎች እንዳሉት ያን ጊዜ ለመታየት አልቻለችም፡፡

የአክሱም ጽዮን አቀማመጥ፣ አጠባበቅ እና አነዋወር እጅግ ጥልቅ ጥናት የሚጠይቅ ምሥጢራዊ ሕግ እና ሥነ ሥርዓት አለው፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት ለአንድ ጉዳይ ወደ አኩስም ጽዮን በሄድኩ ጊዜ እዚያ ካሉት ሽማግሌዎች ጋር በአፈ ንቡረ ዕዱ በኩል የመነጋገር ዕድል ነበረኝ፡፡ እኔ ታቦተ ጽዮንን በተመለከተ ልዩ ስሜት የተሰማኝ፣ እግዚአብሔርንም ያመሰገንኩት ያኔ ነው፡፡

አፈ ንቡረ ዕደ እንደነገሩኝ የታተ ጽዮንን ጉዳይ የሚከታተል ራሱን የቻለ ጉባኤ አለ፡፡ የዚህ ጉባኤ አባላት ከትውልድ ወደ ትውልድ በሚተላለፍ ሥርዓት የሚመጠሩ ናቸው፡፡ ሃይማተኞች፣ በሥነ ምግባር የታነጹ፣ ምሥጢር ጠባቂዎች፣ ቤተሰቦቻቸው ከቤተ ክርስቲያን ጋር በተያያዘ አገልግሎት የሰጡ፣ በምንም ነገር የማይታለሉ እና በእድሜ የጠኑ አረጋውያን ያሉበት ነው ጉባኤው፡፡

ይህ ጉባኤ ታቦተ ጽዮንን በተመለከተ ይወያያል፣ ይወስናል፡፡ ለምሳሌ በ1982 ዓም በኢሕአዴግ እና በደርግ መካከል በነበረው ውጊያ ጊዜ ማንም ሳያይ እና ሳይሰማ ታቦተ ጽዮንን እጅግ ጥብቅ ወደሆነ ቦታ ወስዶ ያስቀመጣት፤ በኋላም አገር ሲረጋጋ ወደ መንበርዋ የመለሳት ይህ ጉባኤ ነው፡፡

አፈ ንቡረ ዕድ እንደሚሉት ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜም ቢሆን ጣልያን ታቦቷን ሊተናኮል ይችላል ብለው በማሰብ (አንዳንደች እንደሚሉት እንዳ አባ ገሪማ ወደሚባል አካባቢ) ወስደው ከጠባቂዋ ጋር በአንድ ዋሻ በማስቀመጥ እዚያ ሀገር ሰላም ሲሆን እንድትመለስ አድርገዋል፡፡ ይህ ሲወሰን እና ሲተገበር ግን ከዚህ ጉባኤ አባላት ውጭ ማንም አያውቅም፡፡ ጣልያንም አልደረሰበትም፡፡

ታቦቷን የሚጠብቁት አና የሚያጥኑት ሰው ሲደክሙ ወይንም ሲያርፉ ተተኪውን ፈልጎ፣ መዝኖ እና ፈትኖ በቦታው የሚተካው ይህ ጉባኤ ነው፡፡ ያንን ተተኪ ለማምጣት በድብቅ በጉባኤው አባላት ዘንድ ሱባኤ ይያዛል፡፡ ጸሎተ ዕጣን ይደርሳል፡፡ በመጨረሻም ለአንዳቸው በራእይ ተገቢው ሰው ይገለጣል፡፡ ከዚያም በቦታው እንዲያገለግል ይደረጋል፡፡

ለመሆኑ የቅርቡ ይቅርና በግራኝ አሕመድ ወረራ ጊዜ ታቦቷ የት ነበረች? ብዬ ሽማግሌዎቹን ጠይቄያቸው ነበር፡፡ በግራኝ ወረራ ጊዜ በወቅቱ የነበረው ጉባኤ በወሰነው መሠረት ታቦቷን ይዘው ወደ ኤርትራ ምዕራባዊ ክልል ነበር የሄዱት፡፡ በዚያ ቦታ አሥራ ሰባት ዓመት ቆይታለች፡፡ ወደ ቦታው ሲኬድ ከፊሉ የጉባኤው አባላትም አብረው ሄደው ነበር፡፡

አሥራ ሰባት ዓመት እዚያ ስትቆይ ታቦቷን ያገለግሏት የነበሩት አባት ዐረፉ፡፡ ጉባኤውም ሌላ ሰው ተካ፡፡ ሀገር ተረጋግቶ ሰላም ሲሆን ታቦቷ ትመለስ ዘንድ ጉባኤው ወሰነ፡፡ ነገር ግን ታቦቷ ልትንቀሳቀስ አልቻለችም፡፡ በኋላም ሱባኤ ተያዘ፡፡ በመጨረሻም ለአንድ አባት «ታቦቷን ያገለገሉትን አባት ዐጽም እንዴት ትታችሁ ትሄዳላችሁ?» ስትል እመቤታችን ተናገረቻቸው፡፡ እነርሱም ዐጽማቸውን አፍልሰው በሳጥን ሲያደርጉት ታቦቷ ተነሣችላቸው፡፡ እርሳቸውንም አምጥተው በቀድሞው ቤተ ክርስቲያን መግቢያ በር አጠገብ ቀበሯቸው፡፡ ብለውኛል፡፡

ታቦተ ጽዮን በሁለት መልኩ ነው የምትጠበቀው፡፡ አንደኛው በማይመረመር ጥበቡ እግዚአብሔር ባዘዘላት ጠባቂዎች ነው፡፡ ሽማግሌዎቹ እንደነገሩኝ ለአንዳንዶቹ ብቻ የሚታዩ ሰማያውያን መላእክት ጠባቂዎች አሏት፡፡ በሥውር ከገዳማት ታዝዘው መጥተው የሚያጥኗት እና የሚጠብቋት ቅዱሳንም አሉ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝቡ በልዩ ልዩ መንገድ ይጠብቃል፡፡ አንዳንዱ ነዳይ መስሎ፣ ሌላው ተሸካሚ መስሎ፣ ሌላው የቡና ቤት አስተናጋጅ መስሎ፣ ሌላው ካህን መስሎ፣ ሌላው ተሳላሚ መስሎ፣ ሌላውም ጠላ ሻጭ መስሎ ይጠብቃል፡፡ እነዚሀን ሰዎች ከሽማግሌዎቹ በቀር ማንም አያውቃቸውም፡፡ በዚያ አካባቢ የሚደረገው እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በእነዚህ ጠባቂዎች ዓይን ሥር ነው፡፡ ቱሪስቶችን ከሚያስተናግዱ እና ከሚያስጎበኙ መካከል መረጃ የሚሰበስቡ እና ጥበቃ የሚያደርጉ አያሌ ናቸው፡የአኩስም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ሌሊት እና ቀን ስብሐተ እግዚአብሔር የማይቋረጥባት ናት፡፡ እንደ አንዳንዶቹ አብያተ ክርስቲያናት አገልግሎት የማይኖርበት ጊዜ የለም፡፡ በዚህም የተነሣ አካባቢው በካህናቱ እና አገልጋዮቹ እይታ ቁጥጥር ሥር ይውላል፡፡ ይኼ በግቢው ውስጥ እና ዙርያ ጥግ ይዞ ሸለብ ያደረገው ምስኪን እንዲሁ ምስኪን እንዳይመስላችሁ፡፡ ሳታዩት ጋቢውን ገለጥ እያደረገ አካሄዳችሁን ያያል፡፡ ምናልባት ቸግር የምትፈጥሩ ከመሰለውም በምሥጢራዊ የድምጽ ምልክት ጥሪ ያቀርባል፡፡

አንዳንድ ጊዜ ነገሮችን በምዕራባውያን ዓይን ብቻ እያየን እንዳንሳሳት መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ምዕራባውያን ስለ ታቦት ያላቸው አመለካከት ከእኛ ጋር በእጅጉ ይለያል፡፡ ኢትዮጵያ ከዛሬው የባሱ አስቸጋሪ ዘመናትን አሳልፋለች፡፡ እንዲህ እንዳሁኑ መረጃ እንደልብ በሌለበት ዘመን ኖራለች፡፡

በአንድ አካባቢ የሚደረገውን ነገር በሌላው አካባቢ የሚገኙ ሰዎች ለመረዳት በማይችሉበት ዘመን ኖራለች፡፡ በእነዚህ ዘመን ያልጠፋች ታቦተ ጽዮን በዚህ ዘመን የትም አትሄድም፡፡ እግዚአብሔር ፈጽሞ ተጣልቶን ካልሆነ በቀር፡፡

ኢሕአዴግ ታቦተ ጽዮንን ከሀገር ያወጣል ብዬ ፈጽሞ ጥርጣሬ የለኝም፡፡ ይህ ቢሆን ኖሮ ከዚህ ዘመን ይልቅ ትግራይን ነጻ ባወጣበት እና በአካባቢው የሚደረጉት ነገሮች ሁሉ ለመገናኛ ብዙኃን ቅርብ ባልሆ ኑበት በ1982 ዓም ማድረግ ይችል ነበር፡፡ ግን አላደረገውም፡፡ ሰውን በሚያደርገው ነገር መውቀስ እንዲታረም ያደርገዋል፡፡ ባላደረገው ነገር መውቀስ ግን እንዲያደርገው መገፋፋት ነው፡፡ አቶ መለስ «እንኳን ለሰው ለሰይጣንም ቢሆን የድርሻውን መስጠት ይገባል» እንዳሉት፡፡

አቡነ ጳውሎስ ሮም ተገኝተው ታቦተ ጽዮንን በተመለከተ መግለጫ ሲሰጡ በአጋጣሚ እኔም ለጉባኤ ሄጄ ሮም ነበርኩ፡፡ «ታቦተ ጽዮንን በሙዝየም እናሳያታለን» ፈጽሞ አላሉም፡፡ «ስለ ታቦተ ጽዮን ዓለም የተሻለ መረጃ የሚያይበት ዘመን ይመጣል» ነበር ያሉት፡፡ ጋዜጠኛው ግን በዚያ መልኩ ተረጎመውና ዓለምን አነቃነቀው፡፡

ፓትርያርኩ ታቦተ ጽዮንን በተመለከተ ሥርዓቱ የሚያዝዘውን እንጂ እርሳቸው የፈለጉትን የማድረግ መብት የላቸውም፡፡ ያ ቢሆን ኖሮ እስከዛሬ ገብቼ ልይ ባሉ ነበር፡፡ የአኩስም ጽዮን ሥርዓት ጥብቅነት ለፓትር ያርክ እንኳን የማይመለስ መሆኑን ያውቁታል፡፡ ለምሳሌ በአኩስም በንግሥ ጊዜ ታቦት አይወጣም፡፡ ሥዕል እና መስቀል እንጂ፡፡ የአኩስም ሽማግሌዎች ታቦት ከመንበሩ፣ ሰው ከሀገሩ የሚወጣው ችግር ሲኖር ብቻ ነው ብለውኛል፡፡ ለዚህ ነው ታቦቱን ከመንበሩ ሰውንም ከሀገሩ አታውጣው ብለን የምን ጸልየው ነው ያሉት፡፡ በየወሩ የመጀመርያው ሰባት ጠዋት ጠዋት ምሕላ እየደረሰ ታቦት ተይዞ ከተማው ይዞራል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ታቦቷን በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ያለው በየዘመናቱ በሚቀያየሩት ንቡራነ ዕድ እጅ አይደለም፡፡ ሕዝቡ በፈጣሪ ርዳታ በምሥጢራዊው ሥርዓት በመረጣቸው የሽማግሌዎቹ ጉባኤ እጅ እንጂ፡፡

አይመጣምን ትተሽ ይመጣልን ባሰብሽ ነውና ተረቱ ነገሮችን በጥንቃቄ ማየቱ መልካም ነው፡፡ ፈረንጆቹ የሚሉትን ብቻ እየሰሙ እግዚአብሔር የለለ አድርጎ መቁጠሩ ግን ደግም አይደል፡፡

ይልቅስ መፍራት ያለብን ታቦተ ጽዮንን ከእሥራኤል ወደ ኢትዮጵያ እንድትመጣ ያደረጋት የእሥራኤል ዐመጽ እና በደል በእኛ ዘንድ እንዳይገኝ ነው፡፡ ያ ከሆነ አምላክም ጥበቃውን ያነሣል፤ እኛም ጠብቀን አናድናትም፡፡

(ከአዘጋጁ:- ይኸ መጣጥፍ ከሁለት ዓመት በፊት ለንባብ የበቃ ነው)

 

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top