Connect with us

ህወሓቶች ያበቃላቸው የሰሜን እዝን የተተናኮሉ ቀን ነው

ህወሓቶች ያበቃላቸው የሰሜን እዝን የተተናኮሉ ቀን ነው
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ህወሓቶች ያበቃላቸው የሰሜን እዝን የተተናኮሉ ቀን ነው

ህወሓቶች ያበቃላቸው የሰሜን እዝን የተተናኮሉ ቀን ነው

(እሱባለው ካሳ)

ዶ/ር ዐብይ አህመድ እድለኛ ነው፡፡ ሁሌም ለወዳጆቼ የምናገረው ቃል ነው፡፡ አሁን ማን ይሙት ሕወሓት ተንቀልቅላ የሰሜን እዝ ጦር በተኛበት ግፍ ባትፈጽምበት ኖሮ ዶ/ር ዐብይ ህወሓት ላይ ጦር ለማዝመት ይቸገር እንደነበር ስንቶቻችን እናውቃለን?

ለምን? እንዴት?… የሚሉ ጥያቄዎች እንደሚጎርፉ እጠብቃለሁ፡፡ አዎ! የጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶ/ር ዐብይ ህወሓት የፖለቲካ ልዩነት በማንጸባረቋ እና አንዳንድ ሴራዎችን በህቡዕ ስትጎነጉን በመዋልዋ ብቻ ጦር ላዝምት ቢል እንደአሁኑ ሳር ቅጠሉ ሊደግፈው አይችልም ነበር፡፡ ምናልባትም በሀገር ውስጥ የተሟላ ድጋፍ አለማግኘት ከባድ ዋጋ ሊያስከፍለው ይችልም ነበር፡፡ ግን እሱ ዕድለኛ ነው፡፡ በእርግጥም እናቱም መርቃዋለች፡፡

ህወሓት በጥጋብ መንፈስ ውስጥ ሆና ከባድ ማኖ ነካች፡፡ የሰራችው የክህደት ወንጀል የኢትዮጽያ ሕዝብን በእሷ የቁልምጫ ቃል ብሔር ብሔረሰቦችን በአንድ አሰለፈባት፡፡ የክፋት እርምጃዋ አይጥ ለአመልዋ የድመት አፍንጫን ታሸታለች የሚለውን ሀገርኛ ብሂል የሚያስታውስ ነው፡፡

 እነዶ/ር ደብረጽዮን በአንድ በኩል “በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት አልፈጸምንም፣ የተቃጣብን ጥቃት መከትን፣ራሳችን ተከላከልን እንጂ” የሚል ወሬያቸው ከአየር ላይ ሳይተን የቀድሞ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ሴኮቱሬ ጌታቸው “መብረቃዊ እርምጃ” ወሰድን ብለው ወራሪነታቸውን አወጁ፡፡ ድንበር ጠባቂ ወታደርን በገዛ ወገኑ በተኛበት መውጋት እጅግ የከፋ ክህደትና ነውር በመሆኑ ዓለም ጭምር አዘነ፡፡

ይኸ በህወሓት አንደበት የተረጋገጠው የክህደት ወንጀል በመጀመሪያ ደረጃ ጦር ሰራዊቱን አስቆጣ፣ ቀጠለናም ሕዝቡን አስቆጣ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችንም በንዴት አንጨረጨረ፡፡ እናም የቁጭትና የተጠቃን ስሜት ከዳር እስከዳር ተቀጣጠለ፡፡ ወዳጄ ይህ ስሜት ሰሞኑን ለሰራዊቱ ክብር ለመስጠት በአርቲስቶች አነሳሽነት በተዘጋጀ አጭር ፕሮግራም ላይ ተንጸባርቆ ያየኸው ነው፤ የታዘብከው ነው፡፡ ምን ይኸ ብቻ፤ ሕዝቡ ከጥግ እስከጥግ የገንዘብና የአይነት (በሬና በጉ) በፍቃደኝነት ወደሰራዊቱ እያጎረፈ ያለው ቁጭቱ በፈጠረው ስሜት ተነሳስቶ ነው፡፡

ሌላም ልጨምርልህ፡፡ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ከእንዲህ ዓይነት አፈንጋጭና ከሀዲ ቡድን ጎን ቆሞ መታየትን አይፈልግም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የክህደት ወንጀል መንግስታት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እውቅና መስጠት አይፈልጉም፡፡ ለዚህም ነው፤ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታ ምክርቤት ሳይቀር በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ለመነጋገር ተሰብስቦ ምንም ማለት ሳይችል የቀረው፡፡

ህወሓቶች “ጦርነት ባህላዊ ጨዋታችን ነው” ብለው ያዙን ልቀቁን እንዳላሉ ዛሬ የፌዴራል መንግስቱን ጠንካራ ጡጫ ሲቀምሱ አማልዱኝ ለማለት ያልረገጡት ደጃፍ፣ ያላንኳኩት በር፣ ተሰልፈው ያልጮኹበት የሰው ሀገር የለም፡፡ የግፍ ጽዋ ሞልቷልና የሁሉንም ምላሽ እንደቴሌዋ ሴትዮ “ጥሪ አይቀበልም” ሆነ፡፡

እናም በአጭሩ የህወሓት ነገር የሙት ፋይል ሆኗል፡፡ ህወሓቶች ፈጥነው በለኮሱት እሳት እየተለበለቡ ወደተማሰላቸው ጉድጓድ ቀስ በቀስ እያዘገሙ ነው፡፡ ከወዲሁ ነፍስ ይማር እንበላቸው፡፡ ነፍስ ይማር!

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top