Connect with us

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የክልሉን የአስተዳደር መዋቅሮች እንደሚለውጥ አስታወቀ

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የክልሉን የአስተዳደር መዋቅሮች እንደሚለውጥ አስታወቀ
ሪፖርተር

ዜና

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የክልሉን የአስተዳደር መዋቅሮች እንደሚለውጥ አስታወቀ

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የክልሉን የአስተዳደር መዋቅሮች እንደሚለውጥ አስታወቀ

በትግራይ ክልል የተጀመረውንና መንግሥት ‹‹የሕግ ማስከበር ተግባር›› ያለውን ዘመቻ ተከትሎ፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የተቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉ ነጋ (ዶ/ር)፣ በትግራይ ክልል በየደረጃው ያሉ የሕግ አውጪና አስፈጻሚ አካላትን፣ እንዲሁም የዞኖችን የአስተዳደር መዋቅሮች እንደሚለውጡ አስታወቁ፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት የመረጃ ፍሰት ቃል አቀባይ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) ጋር፣ ኅዳር 10 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፣ አሁን ያሉት የክልሉ ሥራ አስፈጻሚ፣ የክልል ምክር ቤት አካላትና የዞን የሥራ አስፈጻሚና ምክር ቤቶችን ሙሉ ለሙሉ በአዲስ የመተካት ዕቅድ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

 በዚህም መሠረት፣ ለጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚሾሙ ሰዎችና በተለያዩ ዘርፎች የሚያገለግሉ ባለሙያዎች፣ ‹‹ብቁና የሕዝብ ድጋፍ ያላቸው እንዲሆኑ ይደረጋል›› ያሉት ሙሉ (ዶ/ር)፣ ሥራውን ውጤታማ ለማድረግም ከሕዝቡ ጋር ምክክር ይደረጋል ብለዋል፡፡

‹‹ምንም እንኳን ይኼ ጊዜያዊ አስተዳደር በሕዝብ ያልተመረጠ ቢሆንም፣ ለሕዝቡ እንደምንሠራ በመናገር ሳይሆን በማሳየትም ጭምር የሕዝቡን እምነት ለማግኘት እንጥራለን፤›› ብለውዋል፡፡

‹‹እኛ የተቋቋምነው ለዓመታት የምንቆይ አይሆንም፣ ሰላማዊ ሽግግር እንዲኖርና የሥልጣን ክፍተት እንዳይፈጠር ነው፤›› ብለዋል፡፡

በዚህም አግባብ በምርጫ ቦርድ ሕጎች መሠረት ዴሞክራሲያዊ፣ አሳታፊ፣ ፍትሐዊና ነፃ ምርጫ እንዲደረግ እንደሚሠሩና ለውጥ በተለያዩ ዘርፎች ማምጣት እንደሚቻል ለማሳየትም እንደሚሹ ጊዜያዊ ዋና አስተዳደሩ ተናግረዋል፡፡

‹‹በመናገር ብቻ ሳይሆን ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከሕዝቡ ጎን እንደሆነ ካሳየ ከትግራይ ሕዝብ ድጋፍ ማግኘት ይችላል፤›› በማለትም አክለዋል፡፡

ጊዜያዊ አስተዳደሩ የክልሉን አስፈጻሚ መሾም፣ ሕግና ሥርዓት ማስፈን፣ የስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ክንውን ማስተባበር፣ እንዲሁም በፌዴራል መንግሥት የሚሰጠውን ተግባራት የመፈጸም ሚናዎች እንደሚኖሩትና ለዚህም ማስፈጸሚያ የሚሆን ረቂቅ ቻርተር ማዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ቻርተር መሠረት የሚደለደለው የሥራ አስፈጻሚ አካል ገለልተኛ ባለሙያዎችን እንደሚያቅፍና የሕዝብ ተቀባይነታቸው ላይ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ጠቁመዋል፡፡

በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ማብራሪያ የሰጡት ሬድዋን (አምባሳደር) በጦርነቱ ቀጣና ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብ ከዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ዕርዳታ አስተባባሪ፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ አስተባባሪ፣ እንዲሁም ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮ ጋር እየሠራ እንደሆነ በመግለጽ፣ ጦርነቱን በመሸሽ ወደ ሱዳን የተሰደዱ ኢትዮጵያውያንን መልሶ ወደ አገር ቤት ለማምጣት በማቀድ፣ ለመጠለያዎች ዕድሳትና ማሻሻያ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡ 

ለዚሁም ሥራ እንዲሆን በፌዴራል መንግሥት በተያዙ ሥፍራዎች መንግሥት ዕርዳታዎችን እንዲያደርስ፣ መንግሥት ያልደረሰባቸው አካባቢዎች ደግሞ ለሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢዎች ደኅንነቱ የተጠበቀ መተላለፊያ ለመፍጠር እየተሠራ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡(ብሩክ አብዱ – ሪፖርተር)

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top