የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ፡- የአምባሳደር ዶ/ር ተስፋዬ ሐቢሶ ታሪካዊ ደብዳቤ እና ምስክርነት
በዲ/ን ተረፈ ወርቁ
- እንደ መንደርደሪያ
ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ለሕዝቦቿ ነጻነት ክቡር ደማቸውን በአንድነት ያፈሰሱት የትግራይና የአማራ ጀግኖች- ዘውግን/ቋንቋን መሠረት ያደረገው የክልል ወሰን ምክንያት የጋራ ታሪካቸውን አጨልሞባቸው፣ የተለያዩ ሕዝቦች አድርጎ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ባይተዋር እንዲሆኑ ፈርዶባቸዋል፡፡ የዚህ የልዩነት ጦስ ደግሞ በአማራና በትግራይ ክልል ወሰን መካከል የጠብና ቁርሾ ምክንያት ኾኗል፡፡
ይህ የወሰን ጠብና ቁርሾ መፍትሔ ሳያገኝም ከሰሞኑን የትግራይ ክልል ሠራዊት በመከላከያ ኃይል ላይ በወሰደው ተንኳሽና አሳፋሪ ርምጃ ምክንያት ጀግናው የኢፌዲሪ መከላከያ ኃይል እየወሰደ ባለው ፈጣን የመልሶ ማጥቃት ርምጃ፣ በአማራና በትግራይ ክልሎች አካባቢ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች እየተቀየሩ ነው፡፡
ከዚሁ የግጭትና ደም መፋሰስ ምክንያት ከሆኑት ከክልሎች ወሰኖች ጋር ተያይዞም እንደ ታሪክ እና የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ተማሪነቴ፣ በአንድ ወቅት በወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ በትግራይና በአማራ ክልል መካከል ውዝግቡ የተካረረ ሰሞን፣ በግሌ አንድ ኢ-መደበኛ ታሪካዊ ጥናት ለማድረግ መረጃ ለማሰባሰብ ሞክሬ ነበር፡፡
እናም በግሌ ካሰባሰብኳቸው የታሪክ ሰነዶች ባሻገር አሁን በሥራ ላይ የሚገኘውን የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥትን ከማርቀቅ እስከ ማጽደቅ ሂደት ድረስ የጎላ ድርሻ የነበራቸውን አንድ ትልቅ ሰው አግኝቼ ነበር፡፡
በሀገረ ደቡብ አፍሪካ፣ ዌስተርን ኬፕ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ላይ ሳለሁ የማውቃቸው እኚህ ኢትዮጵያዊ ምሁር፤ ከሦስት ዓመት በፊት ስለወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ የታሪክ እውነታን መሠረት ያደረገ አንድ መፍትሔ አመላካች ጽሑፋቸውን በኢሜይል አደርሰውኝ ነበር፡፡
እኚህ ሰው በወቅቱ የሃዲያ ሕዝቦችን ወክለው ምክር ቤት አባል የነበሩና (በኋላም በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ባለ ሙሉ ባለሥልጣን አምባሳደር የነበሩት) ዶ/ር ተስፋዬ ሐቢሶ ነበሩ፡፡ ይህን የዶ/ር ተስፋዬ ሐቢሶን፣ የወልቃይት ጠገዴን በተመለከተ፣ ታሪካዊ መረጃዎችን የግል ገጠመኛቸውን ያጣቀሰ ቆየት ያለ ጽሑፋቸውን (በእርሳቸው ፈቃድ) አጠር አድርጌ ላካፍላችሁ ወደድኹ፡፡
- የክቡር አምባሳደር ዶ/ር ተስፋዬ ሐቢሶ ታሪካዊ ደብዳቤ እና ምስክርነት
በ1962 ዓ.ም. ከቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ከተመረቅሁ በኋላ በመንግሥት ሠራተኛነት
የተቀጠርኩት በትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስቴር ስር ይተዳደር በነበረው የመንገድ ማመላለሻ
አስተዳደር መሥሪያ ቤት ነበር፡፡ በ1963/64 ዓ.ም. የተለያዩ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶችን በመላ አገሪቱ ስናቋቋም ለሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚያገለግል ቅርንጫፍ መ/ቤት የተቋቋመው በጎንደር ከተማ፣ ለትግራይ በመቀሌ፣ ለኤርትራ ደግሞ በአስመራ ከተማ ነበር፡፡
በ1963 ዓ.ም. በወልቃይት ጠገዴ በሚገኘው የሁመራ መሬት ጥጥ፣ ሰሊጥና ማሽላ በሰፊው የሚያመርት
የወልቃይት ጠገዴ ሁለገብ የገበሬዎች ማኅበር ነበር፤ በማኅበሩ ውስጥ አባል ሆነው ለመሰማራት የሚሹ ሁሉ ከኮሎኔል ታምራት ይገዙ ከጎንደር የድጋፍ ደብዳቤ እየተፃፈላቸው ነበር የሚመዘገቡት፡፡ ማኅበሩ ከዓለም ባንክ ዕርዳታ የሚያገኝ ነበር፡፡ ምርታቸውን በተመለከተ ማሽላውን ወደከረንና አስመራ የሚያስጭኑ ሲሆን ጥጡንና ሰሊጡን በምጽዋ ወደብ በኩል ወደውጭ አገሮች ነበር ኤክስፖርት የሚያደርጉት፡፡
እነዚህን ምርቶች ወደምፅዋ የሚጭኑት የቀይ ባሕር ኤርትራ የጭነት ማመላለሻ ማኅበር ነበር፡፡ እኛም
የመንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ቡድን በ1963 ዓ.ም. ወደሁመራ የሄድነው ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱ
ማኅበራት በጭነት ታሪፍ የተነሳ ስላልተስማሙ ለማስታረቅ ነበር፡፡ የሁለቱን ማኅበራት መሪዎች በማወያየት በኩንታል 3 ብር የነበረው ወደ 4 ብር ከፍ እንዲል በማስማማት ወደጎንደር ተመለስን፡፡ ያንጊዜ ማለትም የዛሬ 46 ዓመት ሁመራ (ወልቃይት ጠገዴ) የቤጌምድርና ስሜን (የዛሬው ጎንደር) አካል ነበር፡፡
የቤጌምድርና ስሜን እና የትግራይ ጠቅላይ ግዛቶች የድንበር ወሰን የተከዜ ወንዝ ነበር፡፡ ከሁመራ
የሚጫነውም ምርት ተከዜ ሰቲትን ተሻግሮ ከኦምሀጀር (ኤርትራ) ወደምፅዋ ወደብ ድረስ ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ አንስቶ እስከደርግ ውድቀት ድረስ ወልቃይት ጠገዴ የጎንደር ጠቅላይ ግዛት ክልል ነበር፡፡ በእነዚያ ዓመታት አማራ የሚባል ክልል አልነበረም፡፡ አማራ የሚባል ክልል የተዋቀረው ከ25 ዓመታት በኋላ በ1987 ዓ.ም. የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት ከፀደቀ በኋላ ከሌሎች 8 ስምንት ክልሎች ጋር ነበር፡፡
ክልሎቹም የተዋቀሩት በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 46 መሠረት፤ ‘‘በሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነት እና
ፈቃድ ላይ በመመስረት’’ ስለነበር ከ46 ዓመታት በኋላ በመሬት ላይ የተከሰቱትን ማኅበራዊ ለውጦች
አላውቅም፤ ሆኖም የክልሎች አከላለል በሰላማዊ መንገድ የተዋቀረ ሣይሆን በተለያዩ ክልሎች ደም አፋሳሽ ሁኔታዎች ተከስተዋል፣ የሰዎች ሕይወት ሳይቀጠፍ የተከናወነ የክልል አወቃቀር ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ፣ የወልቃይቶችንም ሆነ የማንኛውንም ዘውግ ማንነት የሚወስኑት ራሱ ማኅበረሰቡ እንጂ ማንም ሌላ አካል እንደቦሎ አይለጥፍላቸውም ማንነትን (identity)፡፡
በሌላ አንፃር፣ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 48 መሠረት፤ ‘‘የአከላከል ለውጥ ወይም የክልል ወሰን
የሚመለከት ጥያቄ ከተነሳ ደግሞ ጉዳዩ በሚመለከታቸው ክልሎች ስምምነት፣ እነዚህ ለመስማማት ካልቻሉ የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት የሕዝብ አሰፋፈርንና ፍላጎት መሰረት በማድረግ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሰጥ’’፣ በሕገ-መንግሥቱ ተደንግጓል፡፡ ይህ ጉዳይ ዛሬ የዚህን ያህል ውዝግብ ካስከተለ በታዛቢዎች ዘንድ ጭምር ጉዳዩ ቀድሞም ተድበስብሶና ተሸፋፍኖ የተዘጋ ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ ስለሚያሳድር ከላይ የተጠቀሱት የመንግሥት አካላት ኃላፊነታቸውን አሁንም በአግባቡ ለመወጣት በአስቸኳይ መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል፡፡
ይህ የማይሆን ከሆነ ደግሞ ተአማኒነት ያለው የድንበር ኮሚሽን በማቋቋምና የትግራይና የአማራ ክልሎች ሽማግሌዎች በሚገኙበት ኮሚሽን እንደገና ተጠንቶ የመጨረሻ ውሳኔ ሊሰጠው ይቻላል፡፡ የፌዴራል አባላት ክልሎችን ወሰን በተመለከተ በየጊዜው መከለስና ለሕዝቦች መስተጋብር በሚያመች ሁኔታ ጂዎግራፊን፣ የማኅበረሰብ አሰፋፈር፣ የሚመለከታቸው ወገኖች ፍላጎት፣ የክልሎች እኩልነት ወይም ተመጣጣኝነት… ወዘተ
መስፈርቶች በመጠቀም ማካለል አዲስ ክስተት አይደለም፤ ከናይጄሪያ እስከ ህንድ፣ ከደቡብ አፍሪካ እስከ ካናዳ፣ ከስዊትዘርላንድ እስከ አውስትራልያ ያሉት የፌዴራል አገሮች በየጊዜው የአባል ክልሎቻቸውን ወሰኖች
ይከልሳሉ፣ ያሻሽላሉ፣ ይለውጣሉ፡፡ የወልቃይት ጠገዴ ጥያቄም በተመሳሳይ ሁኔታ ሊፈፀም ይገባል፡፡ ከዚህ ውጭ የሁለቱን ክልሎች ወንድማማች ሕዝቦች ለማጋጨት የሚደረገው እንቅስቃሴ ወይም ሤራ ሁሉ በጽኑ መወገዝ አለበት፡፡
ከዚህ ከአምባሳደር ዶ/ር ተስፋዬ ሐቢሶ ታሪካዊ ደብዳቤና ምስክር ባሻገር፣ የወልቃይት ጠገዴን ጉዳይ በተመለከተ ሳደርገው ለነበርኩት ኢ-መደበኛ የታሪክ ጥናት ጋር በተያያዘ አንድ የቆየ መጽሐፍ ላካፍላችሁ ወደድኹ፡፡ ይህ መጽሐፍ ከ150 ዓመታት በፊት በትግራይና በበጌምድር፣ በሰሜን/በአሁኑ ጎንደር ያሉ ግዛቶችን ዝርዝር የሚያሳይ ነው፡፡ መጽሐፉ ከ140 ዓመታት በፊት ለሐበሻ/ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ማስተማሪያ ታስቦ፤ ‘‘Amharic Geography (የምድር ትምህርት)’’ በሚል በሀገረ እንግሊዝ የታተመ ነው፡፡
- እንደ ማጠቃለያ
‘‘አንድን ፖለቲካዊ ማኅበረሰብ ለመፍጠር…’’ የሚለው የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ወደ መሬት ሲወርድ ግን በቋንቋና በዘውግ የተከፋፈሉ ለጠብና ለጦርነት የሚፈላለጉ ሕዝቦችን እዚህም እዛም ፈጥሯል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ከማንኛውም ዓይነት የዜጐች ማንነቶች መገለጫዎች መካከል ብሔርን (በተለይም ቋንቋን) መርጦ የተለየ ትኩረት በመስጠት ዜጐች የሚከፋፈሉበት ዋና መስፈርት እንዲሆን አድርጐታል፡፡ በዚህም ምክንያት ብሔር (በተለይም ቋንቋ) በማኅበራዊውም ሆነ በፖለቲካዊው የአገሪቱ ሕይወት ውስጥ ግንባር ቀደም ትኩረት አግኝቷል፡፡ ይህም ኢሕአዴግ ሥልጣን በያዘባቸው ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ዜጐች ለብሔር (ለቋንቋ) ልዩነታቸው ትልቅ ቦታ እንዲሰጡ ገፋፍቷል፡፡
የኢሕአዴግ መንግሥት በሕይወት በቆየበት ሁለት ዐሠርት ዕድሜው “የማንነት ጥያቄ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ተፈቷል፤ ሕገ መንግሥቱ ብሔር፣ ብሔረሰቦች ተቻችለው እንዲኖሩ ያስቻለ የቃል ኪዳን ሰነድ ነው” ብሎ ቢገልጽም በአገሪቱ በርካታ አካባቢዎች የማንነት ጥያቄዎች እና ዘርን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች ተንከባለካይ ዕዳ ኾነው ሀገሩን ሲያውኩ እያየን ነው፡፡ ጉዳዩ ተከታታይ የደም ሚንዳዎች እያስከፈለ መኾኑም ማስረጃ በገፍ የሚቀርብበት ጉዳይ ነው፡፡
ዶ/ር ፍሥሐ አስፋው ከሦስት ዓመት በፊት “ሰንደቅ” ከተሰኘ የሀገር ውስጥ ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ በኢትዮጵያ ከ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት መጽደቅ በኋላ የተተገበረው ፌዴራላዊ አወቃቀር “ቋንቋን መሠረት ያደረገ መኾኑ በሕዝቦች መካከል መለያየትንና መጠራጠርን አስፍኗል፤” ሲሉ ሞግተው ነበር፡፡ በአማራና በትግራይ፣ በኦሮሚያና በአማራ፣ በደቡብና በኦሮሚያ፣ በአፋርና በሱማሌ፣ በሶማሌና በኦሮሚያ፣ በአማራና በቤኒሻጉል ጉሙዝ አዋሳኝ የተከሰቱ ግጭቶች ሕገ መንግሥቱና ሕገ
መንግሥታዊው ሥርዓቱ የወለዳቸውና ከማንነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም የጠብና ግጭት፣ የደም መፋሰስና እልቂት መንስኤ የሆነውን ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና የተቸረውን የክልል
ወሰን ጉዳዮችን መንግሥት በአስቸኳይ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል፡፡
ሰላም!!