Connect with us

በትግራይ የፌዴራል ፖሊስ ጥበቃ ያደርግላቸው የነበሩ 22 ተቋማት ተጠቁ

በትግራይ የፌዴራል ፖሊስ ጥበቃ ያደርግላቸው የነበሩ 22 ተቋማት ተጠቁ
the reporter

ህግና ስርዓት

በትግራይ የፌዴራል ፖሊስ ጥበቃ ያደርግላቸው የነበሩ 22 ተቋማት ተጠቁ

 የፌዴራል ፖሊስ ጥበቃ ያደርግላቸው የነበሩ 22 ተቋማት ተጠቁ

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል እንደሻው ጣሰው አዲስ ከተዋቀረው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረ ኃይል ቃል አቀባይ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) ጋር በመሆን፣ ዓርብ ጥቅምት 27 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በትግራይ ክልል በሚገኙና የፌዴራል ፖሊስ ጥበቃ ሲያደርግላቸው የነበሩ 22 የተለያዩ ተቋማት መጠቃታቸውንና መዘረፋቸውን ተናገሩ፡፡

ኮሚሽነር ጄኔራሉ የፌዴራል መንግሥት አካል እንደ መሆናቸውና ለፌዴራል መንግሥት ተቋማት ጥበቃ ማድረግ ለፌዴራል ፖሊስ የተሰጠ ኃላፊነት እንደሆነ በመጠቆም፣ በዚሁ ተግባር ላይ ተሰማርተው የነበሩ አባላት ይጠብቋቸው የነበሩ ተቋማት፣ በሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል ብለዋል፡፡ እነዚህ የተጠቁና የተዘረፉ ተቋማት የአሉላ አባ ነጋ ኤርፖርት፣ የተለያዩ ዴፖዎች፣ የኃይል ማስተላለፊያና የማከፋፈያ ጣቢያዎች፣ ቴሌኮም፣ የተለያዩ ኬላዎች፣ እንዲሁም ቤተ መንግሥት እንደሚያካትት ተናግረዋል፡፡

በዚህም ሒደት የሠራዊቱ አባላት ላይ ጉዳት መድረሱን የጠቆሙት ኮሚሽነር ጄኔራሉ፣ የደረሰው ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ምን ያህል እንደሆነ ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ ይሁንና በትግራይ ክልል በሚሠሩ ማንኛውም የልማት ሥራዎች ውስጥ ተሳታፊ የነበረው የፌዴራል ፖሊስ ኃይል ላይ ጥቃት ተፈጽሞ የንብረት ዝርፊያ መከናወኑን አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች ሠራዊቱ (የፌዴራል ፖሊስ) ከትግራይ ክልል ነዋሪዎች ጋር ተባብረው ጉዳቱን መቀነስ መቻሉን የጠቆሙት ኮሚሽነር ጄኔራል እንደሻው፣ የፖሊስ አባላቱ ከሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት ጋር በመተባበር ጥቃቱን በመመከት፣ የራሱን ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል፡፡ ሠራዊት ለጥበቃ በተሰማራበት ለውጊያ በተሰናዳ ኃይል ጥቃት መፈጸም ያሳፍራልም ብለዋል፡፡

በትግራይ ክልላዊ መንግሥት የሕግ ማስከበር ሚና እየተወጣ ነው ብለው፣ ጦርነት ስለተቃጣ ያንን ለመመከት እየተሠራ ይገኛልም ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ሐሙስ ጥቅምት 26 ቀን 2013 ዓ.ም. መግለጫ የሰጡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ ‹‹ሰሜን ዕዝ በገዛ ወገኑ የትግራይ ልዩ ኃይል ጥቃት ተፈጽሞበታል የሚለው በርካታ ጥያቄዎችን ያስነሳል፤›› ብለዋል፡፡

ይኼ ሠራዊቱ በራሱ መደበኛ አሠራር በትግራይ፣ ከዚያም ውጪ ባለፉት ጊዜያት የተለያዩ ሥምሪቶች ለማድረግ ሲሞክር፣ ‹‹እኛን ትታችሁ የት ትሄዳላችሁ በማለት ሕፃናትንም መንገድ ላይ በማስተኛት ሠራዊቱ ከዚያ እንዳይንቀሳቀስ ደጀን ሆኖ እንደቆየለት ይታወቃል፤›› ብለው፣ ደጀን ሆኖ እንዲቆይ የተፈለገና ለረዥም ዓመታት በተግባር ደጀን ሆኖ የክብር መግለጫ የሆነ ኃይል በገዛ ወገኑ ጥቃት ሲፈጸም ምን ይሉታል የሚለው መታየት የሚገባው ነው ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ዓርብ ጥቅምት 27 ቀን 2013 ዓ.ም. በቴሌቪዥን ባሠራጩት መልዕክት የመጀመርያ ዙር ዘመቻ መቶ በመቶ መሳካቱን ገልጸው፣ ከተለያዩ አካባቢዎች ሠራዊት አንቀሳቅሰው የሰው ኃይልና የሎጂስቲክስ ዝግጅት ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ ግንባሮች ያሉ የመከላከያ ሠራዊት አባላትና ትጥቃቸው፣ ሙሉ ለሙሉ ‹‹ከጠላት ፍላጎት›› ውጪ ሆኖ የጥቃት ሥጋት እንዳይኖር ለማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡ አክለውም የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች ሠራዊቱን ለማጥቃት እንዳይውሉ መደረጋቸውንና በዳንሻ ጥቃት ሲፈጽም የነበረው ኃይል ሙሉ ለሙሉ መደምሰሱንም አስታውቀዋል፡፡ (ብሩክ አብዱ ~ ሪፖርተር)

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top