ከኢፌዴሪ የሰላም ሚኒስቴር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ መግለጫ
ሃገራችን ኢትዮጵያ አሁን የምትገኝበት የለውጥ ጉዞ በህዝቦች መስዕዋትነት የተገኘና ለቀጣይነቱም ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ይሁንታን ያገኘ መሆኑ ለአፍታም የሚዘነጋ አይደለም፡፡ የህዝቡ ፍላጎት ገንፍሎ ያመጣውን ለውጥ ከመቀበል ይልቅ ለውጡን ለማደናቀፍ ባለፉት ሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ መጠነ ሰፊ ጸረ ለውጥ እንቅስቃሴዎች ሲካሄዱ ቆይተዋል፡፡
በዚህም የንጹሃን ዜጎች ሕይወት ተቀጥፏል፤ የህዝብና የሃገር ሃብት እንዲወድም ተደርጓል፡፡
በዚህ እኩይ ተግባር ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የህወሓት ጽንፈኛ ቡድን እጅ በመኖሩ ዜጎች በመንግስት ላይ ያላቸውን እምነት እንዲያጡ በማድረግ ሃገራችን አሁን ያለችበትን የለውጥ ጉዞ በማደናቀፍና ወደ ማያባራ የዕርስ በእርስ ጦርነት እንድትገባና በመጨረሻም እንድትፈራርስ እና ዜጎቿም በድህነትና በጦርት ውስጥ እንዲኖሩ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡
የዚህ ችግር ዋንኛ ማሳያ በትግራይ ህዝብ ጉያ የመሸገው ቡድን የሃገርን ዳር ድንበር በተለይም የትግራይን ህዝብ በመጠበቅ ላይ ያለውን እንዲሁም የሀገር ክብርና ኩራት በሆነው በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በማድረስ በራስ ወገን ላይ ታሪክ የማይረሳው አሳፋሪ የሀገር ክህደት ፈጽሟል፡፡
በመሆኑም መንግስት የተጣለበትን ሕግ የማስከበርና አገራዊ አንድነትን የማስጠበቅ ሕዝባዊና አገራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት እርምጃዎችን በተጠናከረ መንገድ መውሰድ ጀምሯል፡፡
ሃገራችን ኢትዮጵያ በተያያዘችው የለውጥ ሂደት ውስጥ ዘርፈ ብዙ ተግዳራቶችን በትዕግስትና በጽናት ለመፍታት አያሌ ጥረቶችን እያደረገች ያለች መሆኗን መላው የትግራይ ሕዝብ በውል ተገንዝቦ ከሌሎች ኢትዮያዊያን ወገኖቹ ጎን በመቆም ጥቂት ሰላም ጠል ቡድኖች ሃገርን በማፈራረስ ለውጭ ጠላት አሳልፎ ለመስጠት እያደረጉት ያለውን አፍራሽ ተግባር በመረዳት ለመግታትና ሀገርን እንደ ሀገር ለማስቀጠል በሚደረገው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የራሱን አዎንታዊ ድርሻ ሊወጣ ይገባል፡፡
መላው የሀገራችን ህዝብም መንግስት ለሚወስደው ማንኛውም እርምጃ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ አብሮነታችንንና ሰላማችንን በጋራ ለመጠበቅ ከምንግዜውም በላይ በጽናት በመቆም የሀገር ሰላምና የህዝቦችን ደህንነት ለማስጠበቅና በሀገራችን ህልውና ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመከላከል ከመንግስት ጎን እንዲቆም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
በመጨረሻም ሀገራችን የተደቀነባትን የህልውና አደጋ በአግባቡ በመረዳት ችግሮች በቁጥጥር ስር እስኪውሉ ድረስ ህዝቡ አካባቢውን ከወትሮው በተለየ ንቃትና ትኩረት በመጠበቅ የዜግነት ኃላፊነቱን እንዲወጣ እንጠይቃለን፡፡
የሰላም ባለቤት እርስዎ ነዎት!
ጥቅምት 26 ቀን 2013 ዓም
የሰላም ሚኒስቴር
(EBC)