Connect with us

ትራምፕን ሳስባቸው

ትራምፕን ሳስባቸው (ጫሊ በላይነህ)
ፎቶ፡- ስታር ትሪቢዩን

ነፃ ሃሳብ

ትራምፕን ሳስባቸው

ትራምፕን ሳስባቸው

(ጫሊ በላይነህ)

 

ነገረ ሥራቸው እብደት የተሞላበት ነው፡፡ ንግግሮቻቸው ሁሌም አወዛጋቢና አስደንጋጭ  ነው፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ በተነሳበት ሰሞን ነገሩ ቀለል አድርገው “ቻይና ሰራሽ ቫይረስ” እያሉ ሲሳለቁ ዓለም በተደጋጋሚ ሰምቷል፡፡ ቆዩና በሚያደርጓቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች የኮሮና ቫይረስን ለማዳን ፀረ – ወባ መድኃኒቶች (ክሎሮኪንና ሃይድሮክሲክሎሮኪን ) ፍቱን መድሃኒት ነው አሉ፡፡

አጠገባቸው ያሉ ሳይንቲስቶች፣ የህክምና ባለሙያዎችና የአለም አቀፉ የጤና ድርጅት ኡኡ ብለው ቢንጫጩም በጀ ብለው ሊመለሱ አልቻሉም፡፡ ይግረማችሁ ብለው፤ ከጸረ ወባ መድሃኒት ከፍተኛ አምራቿ ሕንድ ጋር የቃላት ጦርነት ለመግጠም አቆበቆቡ፡፡ አንድ ዕለት ለህንዱ ጠ/ሚኒስትር ናሪንድራ ሞዲ ስልክ ደውለው ቀጭን ትዕዛዝ ሰጡ፡፡

“የምታመርቱን የጸረ ወባ መድሃኒት ለእኛ ለአሜሪካዊያን ካልሸጣችሁ ውርድ ከራሴ” አሉ፡፡ መና የወረደላቸው ህንዶች በልቦናቸው “ገበያ ተገኝቶ ነው” እያሉ “ሚስተር ፕሬዚደንት ትንሽ ጊዜ ይስጡን እንጂ ያሉትን እንፈጽማለን” አሉ፡፡ ትራምፕ ከሞዲ ጋር በፍቅር ጦፈው እርጥብ እናቃጥል ሲሉ ከረሙ፡፡

ነገርግን በህክምና ሳይንቲስቶች አብዝተው ስለተብጠለጠሉ ለታላቅ ስህተታቸው በይፋ ይቅርታ እንኳን ሳይጠይቁ ዝም ለማለት ተገደዱ፡፡ ይኸም ሆኖ ግን  እንደአፍሪካ ባሉ ታዳጊ አገራት መድሃኒቱ በባትሪ እንዲፈለግ በማድረግ ሰው ሰራሽ እጥረት ከመፍጠራቸውም በላይ እንደናይጄሪያ ባሉ አገራት ሰዎች መድሃኒቱን በመጠቀም ለከባድ የጤና ቀውስና ሞት እንዲዳረጉ ምክንያት ሆነዋል፡፡

ትራምፕ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ የሆነው የፊት ጭንብል ለማድረግም ብዙ አንገራግረው ነበር፡፡ የኋላ ኋላ አድርገው በአደባባይ የታዩት በስንትና ስንት ኢግዚኦታ ነበር፡፡ የፈጣሪ ነገር ግን ገራሚ ነው፤ አላጋጩን ዶናልድ ትራምፕን ኮሮና ጎበኛቸው፡፡ ለቀናትም ራሳቸውን አግልለው እንዲቀመጡ በማስገደድ ጡንቻው አሳይቷቸዋል፡፡

ወደኢትዮጵያ ስንመለስ በአምናው የጠ/ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የኖቤል ሽልማት በቅናት የተንጨረጨሩ የሚያስመስል አስተያየት በመሰንዘር ራሳቸውን ለትችት ዳርገዋል፡፡

ትራምፕ በአንድ የምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት፤ “ስለ የኖቤል የሰላም ሽልማት ልነግራችሁ እችላለሁ፤ ከስምምነት ደረስኩኝ፤ ሃገር አዳንኩኝ፤ እንደሰማሁት የዚያ ሃገር መሪ ‘ሃገሩን በመታደጉ’ የኖቤል ሽልማት ማግኘቱን ሰማሁ። እኔ በዚህ ላይ ተሳትፎ ነበረኝ? አዎ!.. ግን እኛ እውነታውን እስካወቅነው ድረስ ምንም አይደለም። ትልቅ ጦርነት ነው ያስቀረሁት። ሁለት ሃገሮችን ነው ያዳንኩት” ብለው ነበር፡፡

ትራምፕ ያወሩት ስለኢትዮጵያ እና ኤርትራ እርቀ ሰላም ነው፡፡ “አስታራቂው እኔ ነበርኩኝ” በማለት በገደምዳሜ “የኖቤል ሽልማቱ ለእኔ ይገባኝ ነበር” የሚል ግልጽ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ በዚህም ንግግራቸው ታረቁ የተባሉትን አገራት መሪዎች ጭምር ፈገግ አሰኝተዋል፡፡

ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ሰሞኑን በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሰጡት አስተያየት በርካታ ደግሞ በርካታ ኢትዮጵያዊያንን አሳዝኗል፤ አስቆጥቷልም፡፡

ትራምፕ በቅርቡ የሱዳንና እስራኤል ግንኙነታቸውን ለማደስ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተከትሎ በጽህፈት ቤታቸው ሁለቱን ጠቅላይ ሚኒስትሮች በስልክ ባነጋገሩበት ወቅት “ኢትዮጵያ የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ስምምነትን ጥላ መውጣት አልነበረባትም” ሲሉ አስተያየት ከመስጠት አልፈው “ግብጽ ግድቡን ታፈነዳዋለች” በማለት የሰነዘሩት አስተያየት በዓለም ዙረያ የበርካታ ኢትዮጵያውያንን ቁጣ ቀስቅሷል፡፡

የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በአጭሩ ገልጸዋቸዋል፡፡ “ትራምፕ የሚናገሩትን አያውቁም” በሚል፡፡

ፕሬዚደንት ትራምፕ አሁን በስልጣናቸው የመቆየታቸው ነገር ህልም እየሆነ ነው፡፡ የአሜሪካ ሕዝብ በምርጫ ካርዱ ታላቋን አገር ዳግም እንዳይመሩ የወሰነ መስሏል፡፡ ይህ ጽሑፍ እስከተጠናቀረበት ዛሬ ቀትር ድረስ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫን ዴሞክራቱ ጆ ባይደን ሰፋ ባለ ልዩነት እየመሩ ነው፡፡ አሸናፊ የመሆናቸው ነገርም በበርካታ ጋዜጠኞችና የፖለቲካ ተንታኞች የታመነ ሆኗል፡፡

ትራምፕ ከወዲሁ አንድ ጊዜ አሸንፌአለሁ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ምርጫው ተጭበርብሯል በማለት ሁከት ሊያስነሳ የሚችል ንግግሮችን በተደጋጋሚ እያሰሙ ነው፡፡ ይኸም ሆኖ ግን አወዛጋቢ ዶናልድ ትራምፕ ከሰዓታት በኋላ “የቀድሞ ፕሬዚደንት” ከሚለው የክብር ስም ጋር ወደቤታቸው የመሸኘታቸው ነገር አይቀሬ ሆኗል፡፡

(ፎቶ፡- ስታር ትሪቢዩን)

 

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top