“ያኮረፋችሁ ሁሉ ልትደሰቱ ይገባል!”
~ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ የኦሮሚያ ቤተክህነት አደራጅ ኮምቴ ሰብሳቢ
(በድሬቲዩብ ሪፖርተር)
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ ቅዱስ ሲኖዶስ በትላንትናው ዕለት ራሱን የኦሮሚያ ቤ/ክ አደራጅ ተብሎ ከሚታወቀው ቡድን ጋር እርቀ ሰላም ማውረዱ የሚታወስ ነው። ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ አምስት አባላት ያሉት የሽማግሌ ቡድን ሰብሳቢ ላእከ ሰላም ላያብል ሙላቴ እና የኦሮሚያ ቤተክህነት አደራጅ ኮምቴ ሰብሳቢ ሊቀአእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ ቤተክርስቲያን አሸናፊ ሆናለች ብለዋል።
ላእከ ሰላም ላያብል በሁለቱ ወገኖች በኩል የነበረውን ችግር ለመፍታት ከስድስት ወራት በፊት መጀመሩን ተናግረው የእርቀ ሰላሙን ሀሳብ ሁለቱም ወገኖች ያለምንም ልዩነት እንደተቀበሉት አስታውቀዋል።
የነበሩት ጥያቄዎች በቋንቋ ስራ የማከናወን፣ ካህናት ከኦሮምያ እንዲመለመሉና እንዲሰለጥኑና የመሳሰሉ አስተዳደራዊ ጥያቄዎች መሆናቸውን ጠቅሰው በጥቅሉ የነበረው ልዩነት አስተዳደራዊ እንጅ ቀኖናዊ አይደለም ብለዋል። አለመግባባቱ የነበረው በችግሮቹ ላይ ሳይሆን በመፍትሄው ላይ ነበረ ያሉት ቀሲስ በላይ በአሁኑ ሰአት ችግሩ ሙሉ በሙሉ ተፈቷል በማለት ተናግረዋል። አያይዘውም “ሁላችንም አሸናፊ ነን፣ ያኮረፋችሁ ሁሉ ልትደሰቱ ይገባል” ብለዋል።
በስምምነቱ መሰረት ከኦሮምያ አደራጅ ኮምቴ፣ ከሊቃውንት፣ ከባለሙያዎች አንድ ኮምቴ ተዋቅሮ ጥናት በማካሄድ በሚያቀርቡት መፍትሄ መሰረት ተገቢው የማስተካከያ እርምጃ ይወሰዳል ተብሏል።