Connect with us

ዳኛው ማነው?  መልስ ያላገኘ ጥያቄ 

ዳኛው ማነው ? መልስ ያላገኘ ጥያቄ
Photo: Social media

ማህበራዊ

ዳኛው ማነው?  መልስ ያላገኘ ጥያቄ 

ዳኛው ማነው?   መልስ ያላገኘ ጥያቄ 

ደራሲ —–ታደለች ኃ/ሚካኤል 

የገጽ ብዛት—– 442

የታተመበት አመት — 2012 

ዋጋ —–255

የመጽሐፍ ዳሰሳ—- በጀማልአህመድ 

በታደለች ኃ/ ሚካኤል የተጻፈው ‹ ዳኛው ማነው ?› መጽሐፍ ትኩረቱ የብርሃነ መስቀልንና የታደለችን ህይወት በኢሕአፓ ትግል ታሪክ ውስጥ ምን እንደነበር በዝርዝር የሚያስቃኝ ነው ፡፡

‹ዳኛው ማነው? › የኢሕአፓ መሪ የነበረውን የብርሃነ መስቀልን የትግል ፣ የፍቅር፣የፖለቲካና  የመከራ ህይወቱን አጋርቶን  በአሳዛኝ አማሟቱ ያጠቃልላል ፡፡ 

‹ማነው ዳኛው ?› የታደለች ኃይለ ሚካኤልንና  መሰል የወቅቱ ወጣት የለወጥ ፈላጊዎችን  ያለፍርድ ዓመታትን በእስር ያሳለፉበትንና እንደዘበት ወጥተው የቀሩበት ያንን ክፉ  የመከራ ዘመን ያስታውሳል  ፡፡ 

የአካዳሚክ ነጻነቱ ከደርግም ይሁን ከኢህአዴግ የተሻለ እንደነበረ የመሰከረችለ  ያ ዘመን ኢህአፓ ወጣቱን ለትግል አነሳስቶ በመምራት የፈጠረው ተቀባይነትና ትግሉን በስልት ዳር ለማድረስ የገጠመውን ፈተና እናያለን ፡፡ የእርስ በእርስ መጠላለፍ ፣ ለህዝብ ልእልናና ለሀገር እድገት ቆሚያለው የሚሉ የለውጥ ኃይሎች የስልጣን ፈትጊያ ፣ ዙፋኑን የፈነገሉት ደርጎች በሥልጣን ሰክረው ህዝቡ ሲያደሙና ሲያስነቡ  ዘመኑን  በስቃይ ማሳለፋቸውን  በምሬት እናነባለን ፡፡ 

በተለይ የብረሃነ መስቀል የመጨረሻ ሰዓትና  በማእከላዊና በደርግ ጽህፈት ቤት የታጎሩ እሰረኞች ስቃይ እያነበብን  እናነባለን ፣ እያነባን እናነባለን ፡፡  በእስር ላይ የሚደርስባቸው ስቃይ ፣ግርፋትና ርሃብ  ራሳን   በእስረኞች ቦታ ወይም አንድ ቤተሰብ እንደዚህ አይነት ተመሳሳይ ስቃይ አሳልፎ መሞቱን ማወቅ ያማል፣ የሐዘን ቁስልን ያመረቅዛል ፡፡ 

የታደለችና እናትና የአስር ሳንቲም ዳቦ በምሳ እቃ ይዘው ልጃቸውን ለመጠየቅ እስር ቤት ሲደርሱ የልጃቸውን ሞት ሲነገራቸው በድንጋጤ ራሳቸውን የሳቱት  እናት የብዙ ኢትዮጵያዊያን እናቶች ሰቆቃና ጽናት ማሳያ ናቸው ፡፡ 

‹‹በዳኛው ማነው ›› መጽሐፍ በርካታ ጉዳዮችን አንስቶ መዳስ ቢቻልም ከዘመናችን ለለውጥ ከሚደረጉ ትግሎች አንጻር መታየት አለባቸው የምላቸውን የተወሰኑ ነጥቦችን ብቻ ልምዘዝ፡፡ 

የኢትዮጵያ የፖለቲካ አዙሪት ተመሳስሎ በዳኛው ማነው? እንደተገለጸው ሶሰት ዋና ዋና የተማሪዎች ጥያቄዎች ነበሩ ፡፡ ዴሞክራሲያዊ መብት፣መሬት ላራሹና የብሄር ጥያቄ ፡፡ የብሄር ጥያቄ በአብዛኛው ተማሪ የሚቀነቀን ባይሆንም ኋላ በአንዳንድ የተማሪ መሪዎች የማታገያ ስልት ሆኖ ቀርቧል ፡፡በእርግጥ በኤርትራ ተወላጆች  የለውጥ ፈላጊ ወጣቶች ከቋንቋንና ከብሄር አንጻር ያላቸው አቋም የተለየ እንደነበር መገንዘብ ይቻላል ፡፡ 

በዳኛው ማነው ውስጥ ከብሄር ጥያቄ አንጻር ትግሉ ላይ ያሉ ወጣቶችን ስሜት ለመረዳት ጥረት ሳደረግ ከፍሉ ታደስ በ #ያ ትውልድ  የብሄር ጥያቄን አስመልክቶ ያሰፈረው ይታወሰኛል ፡፡ 

“…የተማሪዎች ንቅንቃ ከተፈጠረ ከአስር አመት በላይ ቢሆነውም ፣ የብሄር ጥያቄ  አደባባይ ሳይወጣ የቆየበት ምክንያትም ግልጽ ነበር ፡፡ በአፍሪካውያንና በኢትዮጵያዊያንኖች ጭምር አንድ ብሔረሰብ መብቱን ሊያስከብር ሲነሳ በጥላቻ ዓይን ይታያል ፡፡ ኢትዮጵያ የተለያየ ብሄርሰብ የሚኖርባት ሀገር መሆኗን መቀበል ጎሰኝነትትን ያበረታታል ብለው ስለሚገምቱ የተማሪ መሪ ጥያቄውን ሳያምኑበትና ሳይቀበሉት ኑረዋል ፡፡ ይህ ዝንባሌ የብሔረሰብን ጉዳይ ማንሳት አይፈልግ ከነበረው ከመንግስቱ ፖሊሲ ጋር የተጣጣመ ነበር ፡፡ 

በተማሪዎቹ አካባቢም ሆነ በሌላ አማርኛ ሌሎቹን ቋንቋዎች እየተካ መሄድ በሌሎች ብሔረሰቦችም እተናቁ መሄዳቸውን ማንሳት የሚሻ አልነበረም ፡፡ ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ብቻ አይደለችም ብሎ የሚከራከርም አልነበረም ፡፡ “ገጽ 85 

የብሄር ጥያቄ ማንሳቱ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል የሚልስጋት የነበራቸው ወጣቶችና የመንግሰት ኃይላት አሁን ያስከተለውን ፈተና ስናይ ትክክል ናቸው ያስብላል፡፡ ታደለች ኃ/ሚካኤል በመጽሀፏ እንዳለቸውም ይህ  ‹‹የብሄር ጥያቄ ልሂቃን መሬት በመሸጥና በመለወጥ ዋንኛ የሀብት ማፍሬያ አድርገውታል›› ፡፡ለዚህ ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ ምስክ ነው ፡፡ በብሄር ጥያቄ ማነው እየተጠቀመ ያለው ?

ለውጥ ባልተጠበቅ መንገድ እንደሚመጣ 

በኃይለ ሥላሴ ጊዜ የነበሩ የለውጥ አቀንቃኞች የንጉሱ ስርዓት በቀላሉ ተገርስሶ ይወድቃል ብለው አልገመቱም ፡፡ ብርሃነ መስቀልና ኃይሌ ፊዳ አልጄሪያ ላይ ተገናኘተው ሲወያዩ ኃይሌ ፊዳ በኢትዮጵያ ለውጥ ለማምጣት ሃያ አመታትን እንደሚፈጅ ገምቶ ነበር ፡፡ ለውጡ ግን ብርሃነ መስቀልም ከገመተው በላይ ፈጥኖ እጃቸው ገባ ፡፡ በኋላ ሊያጡት ፡፡ የደርግ ወደ ሥልጣን መምጣት ያልተጠበቀ ነው ፡፡ 

የኢህአዴግ ወደ ሥልጣን መምጣት ያልተጠበቀነው ፡፡ የታሪክ አዙሪቱ አሁንም ተሸከርክሮ የኢህአዴግ መሽቀንጠርና አሁን ያለው ለውጥም ያልተገመተ ነው ፡፡ 

ታደለች ያልተጠበቁ ለውጦችና የህዝብን ጥያቄ በወቅቱ ካለመመለስ የሚመነጭ ከመንግስታቱ ድንዛዜም ጭምር እንደሆነ  በንጉሱ ስርዓት ምሳሌነት ትግልጽልናለች ፡፡ እንቢተኝነታቸውን በስድብና በእርግማን በማሳረግ ለማመዛዘን እንኳን ሳይችሉ ፍጻሚያቸው ይሆናል ፡፡የለውጡ ዘዋሪዎች ሳይለማመዱና ሳይዘጋጁ እጃቸው የገባውን መሪ ወዴት እንደሚዘውሩት ይቸግራቸዋል ፡፡

“ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ንጉሳዊው አገዛዝ  ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት ‹‹ አገር ማለት ንጉሱ ነው ›› በሚል በፈላጭ ቆራጭነት መቀጠልን መረጠ፡፡ ‹ምን ይሆን ያደነዘዛቸው ?› እስኪባል አሳሳቢ ሆነ ፡፡

ውድቀታችንና  ሽፈታችንም የጋራ ነው 

በኢትዮጵያ ለለውጥ የሚደረግ የትግል ታሪክ  እንደሚያመለክተው አሸናፊው አይታይም ተሸናፊዎቹ ግን  ኢትዮጵያዊያን ነን  ፡፡ በጉዞ መደረሻው ላይ ሳንለያይ በአካሄዳችን ላይ በእኔ ይሻላል የአቋራጭ መንገድ ፍለጋ ጸብ እርስ በርሳችን ተላለቅን ፡፡ ማንም አላሸነፈም ፡፡ የተሸነፍንስ ሁላችን ፡፡ ባለችበት እየረገጠች ቀና ማለት የተሳናተስ ሀገራችን ፡፡ እስከመቼ ይሁን እንዲሁ የምንቀጥለው  ‹‹ማነው ዳኛው ?› ጥያቄ የሚጭርብን ለመመለስ ግን  የሚቸግረን  ፡፡

እርስ በእርሳችን የተጨካከንን፣ የህግ ዳኝነቱ ቀርቶ የህሊና ዳኝነት ያለበገረን ፡፡ በኢትዮጵያ የትግል ታሪክ  ሀገራችንን አንድ ጋት ፈቅ ያለደረጋት የመበላላት ትግል ፡፡ሀገርን ህዝብን ያልጠቀመ የኪሳራ እልቂት ፡፡ ተጸጽተን ላለመድገም ያልወሰንበት ተመሳሳይ የትግል አዙሪት ፡፡

ልዩነቶች ለዘላለም ይኑሩ! (viva la difference) መቼ ይሆን እውን የሚሆነው ?

በ‹‹ማነው ዳኛ  ?››ያሉ የዘመኑ እውነተኛ ገጸባህሪያት በልዩነት ማመን እንደሚገባ የሚሰብኩ  እንጂ በተግባር መሆን አቅቷቸው ተያይዘው የጠፉ ናቸው ፡፡ ኢህአፓ፣መኢሶን፣ ደርግና ሌሎች የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ የነበሩ ብርሃነ መስቀል፣ ጌታቸው ማሩን ፣ ኃይሌ ፊዳን ፣ አጥናፉ አባተን ፣ ተፈሪ ባንቲንና ሌሎችንም የተለየ አመለካከታቸው ሳይከበር ተዛንፋቹሃል ተብለው ተቀጥፈው የተጣሉ ናቸው ፡፡ ካልተጠፋፋን በስተቀር ልዩነታችንን አክብረን ፣ መስመራችንን ጠብቀን እነሆ እከዛሬ መቀጠል ያለመቻላችን እዛው ተመሳሳይ  አዙሪት ውስጥ መሆናችንን አመላካች ነው ፡፡

በማነው ዳኛው የእነዚህ ሰዎች መጨረሻ ሳላውቅ በመጠናቀቁ  አጉድሎብኛል

ታደለች የዘመኑን ፖለቲካዊ ክስተት እንደነበረበችበት ሁኔታና አቋም ያየችውንና የተረዳቸውን እንደወረደ ከፍ ዝቅ ሳይል ማቅረቧ እሷን፣ ብርሃነመስቀልና በዙሪያው የነበሩ የትግል ጓዶቹን እነተስፋዬ ደበሳይንና ጌታቸው ማሩን እንድናውቃቸው አድርጋናለች ፡፡  

የታደለች ከስዊዘርላንድ ጀምሮ የረጅም ጊዜ ጓደኛዋና በኋላም የወንድሟ የጸጋ የትግል ጓድ የነበረው አክሊሉ መጨረሻው ምን ሆነ ? ብርሃነመስቀልና ታደለች ለትግል መርሃቤቴ በነበሩበት ጊዜ አብሯቸው የነበረውና እናቱንና እህቱን ያጣው  ያ የጭቁን ጭቁን አርሶ አደር በልሁ ወልዴ የት ደርሶ ይሆን?(አይ በልሁ የእሱ ታሪክ ብቻውን መጽሐፍ ይወጣዋል )  ፣ ከብርሃነ መስቀል  ጋር ከተማ ውስጥ አብሮት ሲንከራተት የነበረውን  የጌታቸው ማሩ መጨረሻ ደራሲዋ  ለምን አልቋጨችልንም ? ( በእርግጥ  በራሱ በኢህአፓ  በአሳዛኝ ሁኔታ መገደሉ  ቢታወቅም) የእነዚህን ሰዎች መጨረሻ ብታካትትልን ሙሉ ያደርገው ነበር ፡፡ 

ዳኛው ማነው ?  ያንን ዘመን በተመለከተ  ካነበብናቸው መጽሐፍት በተለየ መልኩ የኢህአፓ መሪውን የብርሃነመስቀልን ታሪክ ሙሉ ያደርግልናል ፡፡ በትግል ጓዶቹ መካከል የነበረው ልዩነት በደንብ ፈርጦ ባይወጣም ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ቀርቧል ፡፡ የታደለችና የብረሃነ የፍቅር ታሪክ ለመጽሐፉ ማጣፈጫ ቅመም ሆኖአል ፡፡ እንደ ተስፋዬ ደበሳይ የመሳሰሉ የኢህአፓ መሪዎች እንደ ሰው በቅርብ  እንድናቃቸው አስችሎናል ፡፡ 

አሁን ያለው ወጣቱ ትውልድ ከዚያ ዘመን የትግል ስልት ብዙ የሚማረውን መጽሐፉ ይዟል ፡፡ ትግሉን በመድገም ሳይሆን በማረም ፣ የዚያ ዘመን ወጣት ያነሳውን ጥያቄ   በአስተውሎት ምላሽ በመስጠትና በንቃት በማስተዋል  አዲስ የብርሃን መንገድ መያዝ እንዳለበት ዳኛው ማነው? ያመላክተናል ፡፡

 

Click to comment

More in ማህበራዊ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top