Connect with us

እርስ በርሱ የሚጓተት ሕብረተሰብ

እርስ በርሱ የሚጓተት ሕብረተሰብ
Photo: AP

ማህበራዊ

እርስ በርሱ የሚጓተት ሕብረተሰብ

ይኸ ታሪክ የዛሬይቱን ኢትዮጵያ በከፊል የሚያሳይ ሳይሆን አይቀርም
(ከዶ/ር እዮብ ማሞ መፅሐፍ የተቀነጨበ)
***
እርስ በርሱ የሚጓተት ሕብረተሰብ
“የአንድን ሰው እውነተኛ መለኪያው ማየት ከፈለክ የሚበልጡትን ሰዎች ሳይሆን አቻዎቹንና እንዲሁም የበታቾቹን ሰዎች በምን መልክ እንደሚቀርብ (እንደሚያስተናግድ) ተመልከት” – J. K. Rowling ቶም ራዝ (Tom Rath) እና ዶናልድ ኦ. ክሊፍተን (Donald O. Clifton) “ሃው ፉል ኢዝ ዩር በከት” (How Full Is Your Bucket?) በተሰኘው በጋራ በጻፉት መጽሐፋቸው ውስጥ በርካታ አስገራሚና አስተማሪ ታሪኮችን አስፍረዋል፡፡

ከእነዚህ ተቃሚ ታሪኮች መካከል የኮሪያንና የአሜሪካንን ጦርነት አስመልክቶ ለምሳሌነት የተጠቀሙበት ታሪክ ይገኝበታል፡፡ በኮሪያና በአሜሪካ መካከል የነበረው ጦርነት ከተጠናቀቀ በኋላ ዊልያም ሜጀር ኢ. ሜየር (Major William E. Mayer) የተሰኙ የአእምሮ ሃኪም (Psychiatrist) አንድ ሺህ በሚሆኑ በሰሜን ኮሪያ እስር ቤት በነበሩ አሜሪካዊ የጦር ምርኮኞች ላይ አንድን ጥናት አካሄዱ፡፡ ሃኪሙ በተለይም ለማወቅ የፈለጉት ኮሪያኖች በምርኮኞቻቸው በአሜሪካኖች ላይ በውጤታማነት የተጠቀሙበትን ስነ-ልቦናዊ የጦርነት ስልት ለማወቅ ነበር (How Full is Your Bucket, 2005, P. 7-9)፡፡

የአሜሪካ የጦር ምርኮኞች ታስረው የነበሩት የጦር ካምፕ እስር ቤት የአኗኗር ደረጃ ያን ያህል መጥፎ እንዳልነበረ ይታወቃል፡፡ ምርኮኞቹ በቂ ውኃና ምግብ፣ እንዲሁም መሰረታዊ ነገሮች ይሰጣቸው ነበር፡፡ ለምንም አይነት ግርፊያም ሆነ አካላዊ ስቃይ አልተዳረጉም ነበር፡፡ እንደውም በታሪክ ውስጥ እስካሁን ከሚታወቁት የጦር ምርኮ እስር ቤቶች እንደዚያን ጊዜው ያለ እስረኞቹ ምንም አካላዊ ስቃይ ያልደረሰባቸው እስር ቤት አይገኝም ይባላል፡፡

አንድ አንገብጋቢ ጥያቄ ግን የሰውን ሁሉ አእምሮ ወጥሮ ይዞት ነበር፡፡ ለምን ቁጥራቸው እጅግ ብዙ የሆኑ የአሜሪካ የጦር ምርኮኞች ካለምክንያት ሞቱ? እስር ቤቱ ምንም አይነት አደገኛ አጥር አልነበረውም፣ በወታደሮችም አልተከበበም ነበር፤ ሆኖም አንድም አሜሪካዊ እስረኛ የማምለጥ ሙከራ እንኳ አድርጎ አያውቅም፡፡ ነገር ግን እነዚህ ተማራኪ ወታደሮች ካለማቋረጥ የአለቃዎቻቸውን ትእዛዝ ይጥሱ ነበር፡፡ እርስ በርሳቸውም ከመጠን በላይ ይጣሉ ነበር፡፡ አንዳንዴ እንደውም ከራሳቸው ወገን ይልቅ ከማረኳቸው ከኮሪያ ወታደሮች ጋር የጠበቀ ወዳጅነትን በመመስረት እርስ በርሳቸው ይበዳደሉ ነበር፡፡

የሞቱት ሞተው የተረፉት ሰዎች ጃፓን የሚገኘው የቀይ መስቀል ጣቢያ ሲረከባቸውና ቤተሰቦቻቸው ጋር ስልክ እንዲደውሉ እድሉ ሲሰጣቸው አንዳቸውም እንኳ ስልክን የመደወል ፍላጎት አልነበራቸውም፡፡ ምንም እንኳን በነበሩበት እስር ቤት ምንም አይነት የከፋ አካላዊ ስቃይ ባይደርስባቸው፣ 38 በመቶው እስረኛ እንዲሁ ካለምንም አካላዊ ምክንያት እንደሞተ ይነገራል፡፡

ምክንያቱ ሲመረመር ኮሪያኖቹ የተጠቀሙበትን የመጨረሻና የከፋ የጦር ስልትና መሳሪያ ደረሱበት፡፡ ይህ የመጨረሻ የጦር ስልትና መሳሪያ “አንዱ ከሌላው ጋር ከነበረው የእርስ በርስ ትስስርና ግንኘኙነት የተነሳ ሊያገኝ የሚችለውን የስሜት ድጋፍ መንፈግ” ነበር፡፡ ይህንን ለማድረግ የተጠቀሙባቸው ስልቶች አራት ናቸው፡፡

አንዱ በሌላው ላይ መረጃን የማቀበል ስልት
አንድ የአሜሪካ ምርኮኛ የፈጸመውን ጥፋት የራሱ አገር ሰው ለኮሪያኖቹ ሲያሳብቅበት፣ ለአሳባቂው ምርኮኛ እንደ ሲጃራና የመሳሰሉትን ነገሮች በመስጠት ኮሪያኖቹ ያበረታቱት ነበር፡፡

አሳባቂውም ለምን ይህንን የሰው ነገር አሳበክ ተብሎ አይጠየቅም፣ የተሳበቀበትም አሜሪካዊ ለምን ይህንን አደረክ ተብሎ አይቀጣም፡፡ ኮሪያኖቹ ይህንን ያደረጉበት ምክንያት ምርኮኞቹ እርስ በርሳቸው አንዲናናቁ፣ እንዲባሉና ወዳጅነታቸው እንዲበላሽ ለማድረግ ነው፡፡

ራስን የመውቀስ ስልት
ይህንን ስልት ለመጠቀም ኮሪያኖቹ ከአስር እስከ አስራ ሁለት የሚሆኑ ምርኮኞችን በአንድ ላይ በማድረግ እያንዳንዱ ምርኮኛ በሌሎቹ የራሱ ሃገሩ ሰው ፊት እየቆመ፣ ከዚህ በፊት ስላደረጋቸው ክፉ ነገሮች፣ እንዲሁም ከዚህ በፊት ማድረግ ሲገባው ስላላደረጋቸው መልካም ስራዎች እንዲናገር ያደርጉት ነበር፡፡

የዚህ ስልት ዋነኛ አላማ ምርኮኞቹ ለኮሪያኖቹ እንዲናገሩ ሳይሆን የራሳቸው ሃገር ሰዎች ክፉ ክፉውን ብቻ እንዲሰሙባቸውና እርስ በርስ እንዲናናቁ፣ ግንኙነታቸው እንዲበላሽና አንዱ በሌላው ላይ ያለው ግምት እንዲወርድ ማድረግ ነው፡፡

ለመሪዎቻቸውና ለሃገራቸው ያላቸውን ታማኝነት የማፍረስ ስልት
ይህንን ስልት ተግባራዊ ለማድረግ ኮሪያዎቹ ካለማቋረጥ አንድ የአሜሪካ ምርኮኛ ወታደር አብሮት ለተማረከው አዛዡ ያለውን መታዘዝና አክብሮት የመሸርሸር ዘይቤ ተጠቅመዋል፡፡ ይህ ስልት ስኬታማ እንደነበር የሚያሳዩ በርካታ ሁኔታዎች ተከስተዋል፡፡

ለምሳሌ፣ አንድ ጊዜ አንድ ኮሎኔል ለወታደሮቹ ሩዝ በሚያድግበት ረግረግ መሬት ላይ ያለው ውኃ አደገኛ ባክቴሪያ እንዳለው በመጥቀስ ከዚያ እንዳይጠጡ አዘዛቸው፡፡ አንዱ ወታደር እንዲህ ሲል መለሰለት፣ “ወዳጄ ሆይ፣ አንተ እኮ አሁን ኮሎኔል አይደለህም፣ እንደ እኔው ተራ እስረኛ ነህ፡፡ አንተ ለራስህ ተጠንቀቅ እኔ ደግሞ ለራሴ አውቅበታለሁ”፡፡ ይህንን ብሎ ውኃውን በጠጣ በጥቂት ቀናት ውስጥ በተባለው ባክቴሪያ ተመርዞ ሞተ፡፡

አንድ ጊዜ ደግሞ 40 የሚሆኑ ምርኮኞች በራሳቸው ጓዶች ከጎጇቸው ተገፍተው ውጪ እንዲሞቱ ሲጣሉ ማንም ምርኮኛ ምንም ነገር ለማድረግ አልሞከረም፣ ምክንያቱም የእርስ በርስ ግንኙነት ተበላሽቶ መናናቅ ስለነገሰ፣ “እኔን አያገባኝም” በሚል ስሜት ተይዘው ስለነበር ነው፡፡

አዎንታዊ ስሜትን የሚሰጥን ማንኛውንም ነገር መከልከል
ይህንን ስልት ለመጠቀም ኮሪያዎቹ ያደረጉት ከምርኮኞቹ ምንም አይነት አዎንታዊ ዜናን በመንፈግና አሉታዊውን ብቻ እየመረጡ በማሰማት ነው፡፡ ጥሩ ዜና የያዘ ደብዳቤ ከአገራቸው ሲላክላቸው በፍጹም አይሰጧቸውም ነበር፡፡

የሞተን ዘመድ፣ እሱን ከመጠበቅ ተስፋ ቆርጣ የተወችው የፍቅረኛ ደብዳቤ፣ ያልተከፈለ እዳን አስመልክቶ የሕግ ጥያቄና የመሳሰሉት ተስፋ አስቆራጭ መልእክቶች ግን በፍጥነት እንዲደርሳቸው ይደረግ ነበር፡፡ ምርኮኞቹ ምንም አይነት ተስፋ እስኪያጡ ከመድረሳቸው የተነሳ አንዳንዶቹ ብርድ ልብሳቸውን ተከናንበውና አቀርቅረው በመቀመጥ በዚያው ይሞቱ እንደነበር ይነገራል፡፡

እነዚህ የአሜሪካ ምርኮኞች ያለቀላቸው እርስ በርሳቸው የተናናቁ ጊዜ ነው፡፡ ምንም እንኳ የነበሩበት ሁኔታ ተስፋ አስቆራጭ ቢሆንም፣ እርስ በርስ ከመናናቅና ከመጨካከን አንድነታቸውን፣ መከባበራቸውንና መደጋገፋቸውን የበለጠ ሊያጠናክሩ የሚገባቸው ሁኔታ ውስጥ ነበር ያሉት፡፡

በማንኛው ጊዜ፣ ከመለያየት አብሮ መሆን፣ ከመናናቅ መከባበር፣ ከመጨካከን ደግሞ መደጋገፍ ይመረጣልና፡፡ ሆኖም፣ እርስ በርሳቸው ከመናናቃቸው በፊት ሁሉም በመጀመሪያ ራሳቸውን መናቃቸው ግልጽ የሆነ ጉዳይ ነው፡፡ በራሴ ላይ ያለኝ አመለካከት ሲወድቅ በሃገሬ ሰው ላይ ያለኝ አመለካከትም አብሮ ይወርዳል፡፡ ራሴን ያየሁበት እይታዬ ወገኔን በዚያው መልክ እንዳይ የማስገደድ ባህሪይ አለው፡፡

“የማንነትህ መለኪያ” ከተሰኘው የዶ/ር ኢዮብ መጽሐፍ የተወሰደ

Click to comment

More in ማህበራዊ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top