Connect with us

የኢ.ጠ/ዐ/ሕግ ተቋማት ለሚያዘጋጇቸው መመሪያዎች አገር አቀፍ ቁጥር እየሰጠ ነዉ

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተቋማት ለሚያዘጋጇቸው መመሪያዎች አገር አቀፍ ቁጥር እየሰጠ ነዉ
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ

ዜና

የኢ.ጠ/ዐ/ሕግ ተቋማት ለሚያዘጋጇቸው መመሪያዎች አገር አቀፍ ቁጥር እየሰጠ ነዉ

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የመንግስት ተቋማት ለሚያወጧቸዉ መመሪያዎች አገር አቀፍ ብሄራዊ ቁጥር እየሰጠ መሆኑን በተቋሙ የህግ ጥናት፣ ማርቀቅና ማጠቃለል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ በላይሁን ይርጋ ገለፁ፡፡

አቶ በላይሁን ባለፈዉ አመት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካወጣቸዉ አዋጆች መካከል አንዱ የአስተዳደር ስነ ስርአት ህግ ቁጥር 1183/2012 መሆኑን አስታዉሰዉ አዋጁ በዋናነት ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮችን የያዘ መሆኑንና አንደኛዉ የመመሪያ አወጣጥ ስርአት ምን መሆን አለበት የሚለዉን የሚመለከት ሲሆን ሁለተኛዉ ደግሞ የዉሳኔ አሰጣጥ ስርዓትን የሚመለከት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

መመሪያ አወጣጥ ስርአትን በተመለከተ ካስቀመጣቸዉ የአስተዳደር ስርአቶች ዉስጥ ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ተለይተዉ የተሰጡ ሀላፊነቶች ሲሆኑ እነዚህም የሚረቀቁ ህጎች ላይ አስተያየት መስጠትና ህጉን ተከትለዉ የወጡ መመሪያዎች ሲኖሩ አገር አቀፍ ቁጥር መስጠት ዋነኞቹ መሆናቸዉን የገለፁት ዳይሬክተር ጀነራሉ በየ ተቋማቱ የሚወጡ መመሪያዎች የአወጣጥ ስርአታቸዉ ግልፅ ስለማይሆንና የፀደቁና ያልፀደቁ መመሪያዎችን እንዲሁም ምን ያህል መመሪያዎች እንዳሉ ለመለየት የህግ ስርአት ያልነበረ በመሆኑ ምክኒያት መመሪያዎች የመልካም አስተዳደር ችግር ሲፈጥሩ እንደነበር አዉስተዋል፡፡ 

መመሪያ በሰዎች መብቶችና ነፃነቶች ላይ ቀጥተኛ የሆነ ዉጤት እንዳላቸዉ ገልፀዉ በተቋሙ በኩል አዋጁ ከወጣ በኋላ በየተቋማቱ የሚወጡ መመሪያዎች አዋጁን የተከተሉ መሆን እንደሚገባቸዉ ከወጡ በኋላም በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አገር አቀፍ ቁጥር ሊሰጣቸዉ እንደሚገባና በየተቋማት ድረ-ገጽ ላይ መጫን እንዳለባቸዉ አዋጁ የሚደነግግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚሁ መሰረትም ብዙ ተቋማት የሚያወጧቸዉን መመሪያዎች እንዲመዘገብላቸዉ ጥረት ማድረጋቸዉን የገለፁት ዳይሬክተር ጀነራሉ በሀርድ ኮፒ( በወረቀት) እና በፒዲኤፍ የተላኩ መመሪያዎች ላይ ቁጥር መስጠት አስቸጋሪ እንደሆነና አንዳንድ ተቋማት የዉስጥ አሰራር መመሪያዎችን ወደተቋሙ የማምጣት ክፍተቶች መስተዋሉን ገልጸዉ የአስተዳደር ስነ ስርአት ህጉ በዋናነት የሚመለከተዉ ከዉጭ ባለ ጉዳይ ጋር የሚገናኙትን መሆኑንና መመሪያቸዉን ሲያቀርቡም በፅሁፍ ቀይረዉ በሶፍት ኮፒ (word) መሆን እንደሚገባዉ በማሳወቅ እነዚህን ክፍተቶች እንዲያስተካክሉ ለተቋማቱ የማሳወቅ ስራ መሰራቱን ገልፀዋል፡፡

አዋጁ ከወጣ በኋላ በርካታ ተቋማት ከጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ጋር እየተነጋገሩ መመሪያዎችን እያዘጋጁ እንደሆነ የገለፁት አቶ በላይሁን እስካሁን የተመዘገቡ መመሪያዎችም በቁጥር 31 መድረሳቸዉንና ለአብነትም በዚህ ሁለት ቀን ዉስጥ የተመዘገቡ ኮቪድ 19 ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚስችል በኢትዮጵያ ጤና ኢንስቲትዩትና በጤና ሚኒስቴር የወጣ መመሪያ ቁጥር 30/ 2013 እና በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት የተዘጋጀ መመሪያ ቁጥር 31/ 2013ን ጠቅሰዋል፡፡

መመሪያዎችን በማስመዝገብ በኩል አዋጁ ከወጣ በኋላ ያለዉ እንቅስቃሴ መልካም መሆኑን የገለፁት ሀላፊዉ የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጁ ከመዉጣቱ በፊት ወጥተው የነበሩትን መመሪያዎች በ90 ቀናት መመዝገብ አለባቸዉ የሚለዉ በአዋጁ የተቀመጠዉ መመሪያ መተግበር ላይ ክፍተት መኖሩንና ተቋማት አዋጁ ከመዉጣቱ በፊት አዉጥተዋቸዉ የነበሩ መመሪያዎችን ልከዉ እንዲያስመዘግቡ በደብዳቤ ማሳወቃቸዉ አስታዉሰዉ ይህ ሳይሆን ቀርቶ መመሪያዎችን ልከዉ የሚያስመዘግቡ ካልሆነ ግን መመሪያዎቹ የህግ ዉጤት እንዳይኖራቸዉ የሚደረጉ መሆኑን ማወቅ እንደሚገባቸዉ አሳስበዋል፡፡

በመጨረሻም መመሪያዎችን እያረቀቁ ያሉ ተቋማት የአስተዳደር ስነ ስርአት ህጉን በጥንቃቄ እንዲያዩትና መመሪያ ሲዘጋጅ መከተል የሚገባዉን መስፈርቶች አይተዉ ማዘጋጀት እንዳለባቸዉ የገለፁት አቶ በላይሁን መስፈርቱ ተሟልቶ ከተገኘና አገር አቀፍ ቁጥር ከተሰጠዉ በኋላ በጠቅላይ ዐቃቤ ህግና በየተቋማቱ ድረ-ገጾች ተጭኖ ለህብረተሰቡ ተደራሽ መሆን እንዳለበት በመግለፅ ይህ መሆኑም በተለይም በዋናነት በተገልጋዩ ማህበረሰብ ዘንድ መልካም አስተዳደርን በማስፈን በኩል የማይተካ ሚና እንዳለዉ አክለዉ ገልፀዋል፡፡(የኢፌ/ጠ/ዐ/ሕግ)

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top