Connect with us

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለህወሃት ውሳኔ እውቅና መስጠቱ ይሆን?

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለህወሃት ውሳኔ እውቅና መስጠት ይሆን?
Photo: Social media

ትንታኔ

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለህወሃት ውሳኔ እውቅና መስጠቱ ይሆን?

አስቀድሞ ለፌዴራል መንግስቱ እውቅና አልሰጥም ግንኙነትን አይኖረኝም ያለው የትግራይ ክልል፤ ያንን ገልብጦ መግለጫ መስጠቱ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለህወሃት ውሳኔ እውቅና መስጠት ይሆን? | (ከስናፍቅሽ አዲስ)

በህወሃት እና በብልጽግና ሰዎች መካከል የሚደረጉ ሀታካራዎች ትርጉም አልባና እንካ ሰላንቲያ ከሆኑብን ሰንብተዋል፡፡ አንዳቸው በሌላቸው መንገድ ከመሄድ ውጪ የአንዱም የራሱ የምንለው አቋም አልታይ ብሎኛል፡፡

በቅርቡ የህወሃት ሰዎች ከመስከረም 25 በኋላ ህጋዊ መንግስት የለም ከዚያ በኋላ ለሚቀጥለው መንግስትም እውቅና አንሰጥም መመሪያ ካለመቀበል ጀምሮ አብረነውም አንሰራም ብለው መግለጫ አውጥተው ነበር፤ የትናንቱ የፌዴሬሽን ምክር ቤት መግለጫ “እኔም” የሚል ይመስላል፡፡

እነሱ ቀድመው አብረን አንሰራም ያሉትን በኋላ ተከትሎ የፌዴራል መንግስቱ ከትግራይ ጋር ግንኙነት እንዳያደርግስ ማለት ምን ማለት ነው? ቀድሞውኑስ ከፌዴራል መንግስቱ ጋር ግንኙነት አላደርግም ብሎ መግለጫ የሰጠውና አቋም የያዘው ህወሃት አይደለም?

እሰጥ አገባው ረዘመ እንጂ መሬት የወረደ ሀገር የሚያሳርፍ ውሳኔ ከየትኛውም ወገን ሲቀርብ አላየንም፡፡ የፌዴራሉ መንግስትም ቢሆን የህወሃትን ውሳኔ ገልብጦ እየወሰነ ከመግለጽ የተሻለ መፍትሔ መፈለግ ሳይሻለው አይቀርም፡፡ ህወሃትም ብትሆን ጉልበት መለካካቱ ውሎ አድሮ በህዝብ ስነ ልቦናና ጥቅም ላይ ተጽእኖ እንዳይፈጥር ኑ ግጠሙኝ ባይነቷን ብታቆም መልካም ነው፡፡

በብልጽግናና በህወሃት መካከል እንደ ፓርቲ ከተመለከትነው እንዲህ የሚያካርር ጉዳይ ያለ አይመስለኝም፡፡ እርግጥ ነው በቡድንና በግለሰብ ደረጃ ሚሳኤል የሚያታኩስ የጥቅም ግጭት ይኖር ይሆናል፡፡ 

መልሶና መላልሶ ማሰብ ግን ውጤቱ ለህዝብ ምን ይዞ ይመጣል የሚለውን ነው፡፡ ማመጽ፣ ማፈንገጥ አልፎም መገንጠልን ማሰብ ኪሱ ለዳበረ፣ ልጆቹን ደህና ሀገር ልኮ ቀድሞውኑ በሀገሩ ተስፋ ለቆረጠ ቡድን ብዙም አስቸጋሪ ላይሆን ይችላል፤ ለህዝቡ ምን ያመጣል ነው? ጥያቄው፤ የፌዴራሉም መንግስት እንዲህ ያለ ሀሳብ ያለው የመጣ ይምጣ ባይ ቡድን መኖሩን አጢኖ አሁንም ነገሩን በትእግስት ቢመለከተው መልካም ነው፡፡

የአንዱን መግለጫ ሌላው ቢደግመው ግን “የማን አባት ገደል ገባ?” ከመባባል ያለፈ ትርጉም የለውም፡፡

 

Click to comment

More in ትንታኔ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top