ኢዜማ ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም በኋላ መንግሥት የለም፣ ሕዝብ እና የመንግሥት መዋቅር ለፌደራል እና የክልል መንግሥታት ሊታዘዙ አይገባም» በሚል ቅስቀሳ በሚያደርጉ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ጠየቀ፡፡
ኢዜማ ባወጣው መግለጫ «ሥልጣን ለማራዘም የተሄደበት መንገድ ሕገ መንግሥታዊ አይደለም፣ በዚህም ምክንያት ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም በኋላ መንግሥት የለም፣ ሕዝብ እና የመንግሥት መዋቅር ለፌደራል እና የክልል መንግሥታት ሊታዘዙ አይገባም» በሚል ቅስቀሳ ሲደረግ መቆየቱን እና አሁንም እየተደረገ እንደሚገኝ ለማስተዋል ችለናል።
ይህ ቅስቀሳ የሀገራችንን ሰላም እና መረጋጋት ከማወክ እና የዜጎችን ሕይወት አደጋ ላይ ከመጣል በዘለለ ፋይዳ እንደሌለው የኢትዮጵያ ሕዝብ በደንብ እንደሚገነዘብ እናውቃለን። ይህንን ቅስቀሳ እያደረጉ ያሉ አካላትም ከዚህ ተግባራቸው ተቆጥበው የጋራ ሀገራችን ሰላም እና የዜጎች ደህንነት ተጠብቆ በሰላማዊ መንገድ ችግሮቻችንን መፍታት ወደምንችልበት የውይይት መድረክ ከመምጣት ውጪ በሁከት እና በጉልበት ወደሥልጣን ለመውጣት የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ለራሳቸውም ቢሆን የማይጠቅም አደገኛ መንገድ መሆኑን ሊረዱ ይገባል። መንግሥትም እነዚህን ቅስቀሳዎች በንቃት እየተከታተለ አደጋ ከመድረሱ በፊት የመከላከል እና አደጋ ለማድረስ የሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ የሀገር ሰላምን እና የዜጎችን ደህንነት የማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣ እናሳስባለን ብሏል፡፡ (የመግለጫው ሙሉ ቃል እነሆ)
“ሰላማችንን በማስጠበቅ እና ቀጣዩ ምርጫ ላይ በንቃት በመሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሰረት እንጣል!”
ከ ኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ
6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሊካሄድ የግዜ ሰሌዳ ወጥቶለት ሁሉም ባለድርሻ አካላት እንቅስቃሴ ከጀመሩ በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመታወጁ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያወጣውን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ እንዲሰርዝ መገደዱ ይታወሳል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በታወጀበት እና የምርጫ ሰሌዳው በተሰረዘበት ወቅት ወረርሺኙ በሌሎች የዓለማችን ሀገራት የጤና ሥርዓት ላይ ያስከተለውን ከፍተኛ ጫና እና በሰው ሕይወት ላይ ሲያደርስ የነበረውን ጉዳት በተጨባጭ በማየት የተለያዩ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ገደብ መደረጉ እና በዚህ ምክንያት ምርጫው መራዘሙ ተገቢ ነበር ብለን አምነናል።
ምርጫው አለመካሄዱን ተከትሎ የመንግሥት ቀጣይነትን ለማረጋገጥ በተለያዩ ወገኖች የተለያዩ አማራጮች መቅረባቸው የሚታወስ ነው። የተለያዩ ፖለቲካ ፖርቲዎችም ከሕገ መንግሥት ውጪ ያሉ አማራጮችን አቅርበው ነበር። ኢዜማ የመንግሥት ቀጣይነትን በሕጋዊ ማዕቀፍ ውስጥ መፍታት እንደሚቻል ጠቅሶ፣ አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ከሚሰጣቸው የመፍትሄ አማራጮች ውስጥ ደግሞ የመንግሥትን የሥልጣን ጊዜ እና ምርጫ የሚደረግበትን ጊዜ የሚደነግገውን የሕገ መንግሥት አንቀጽ ከአቅም በላይ እና በድንገተኛ ምክንያት ምርጫ ማድረግ የማይቻልበት ሁኔታ ሲፈጠር የመንግሥትን ሥልጣን ከአንድ ዓመት ላልበለጠ ጊዜ ማራዘም እንዲያስችል አድርጎ ማሻሻል የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ማቅረቡ ይታወሳል። ማሻሻያው ሥልጣን ላይ የሚቆየው መንግሥት የሥልጣን ጊዜ ገደብ ያስቀመጠ እና ውሳኔ የሚሰጥባቸው ጉዳዮች በቀጣይ ምርጫ አሸንፎ ሥልጣን የሚይዘው መንግሥት ላይ ግዴታ የማይጥሉ መሆናቸውን ባረጋገጠ መልኩ መሆን እንዳለበትም ምክረ ሀሳብ አቅርበን ነበር።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ክፍተቱን በሕገ መንግሥት ትርጉም ለመሙላት ወስኖ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ባቀረበው የውሳኔ ሀሳብ እና በፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ምርጫውን የኮቪድ-19 ወረርሺኝ ስጋት አለመሆኑ በጤና ሚኒስቴር እና የኅብረተሰብ ጤና ተቋም እስኪረጋገጥ ድረስ አራዝሞ የፌደራል እና የክልል መንግሥታት እና ምክር ቤቶችን የሥራ ጊዜ ያለገደብ እንዲቀጥል መወሰኑ ይታወሳል።
ይህን ውሳኔ ተከትሎ ኢዜማ የጊዜ እና ውሳኔ የሚያሳልፍባቸው ጉዳዮች ላይ ወሰን ሳይደረግ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሥራ ዘመን መራዘሙ ላይ ያለውን ተቃውሞ ገልፆ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ በገለፀው መሰረት አስፈላጊው ጥንቃቄ ተደርጎ ምርጫው መደረግ በሚችልበት ቅርብ ጊዜ እንዲደረግ ጠይቋል።
በቅርቡ የጤና ሚኒስትር አስፈላጊው ጥንቃቄ እየተደረገ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ እንደሚቻል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባሳወቀው መሰረት 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በያዝነው ዓመት እንዲካሄድ ውሳኔ ተላልፏል።
ይህ በእንዲህ እያለ «ሥልጣን ለማራዘም የተሄደበት መንገድ ሕገ መንግሥታዊ አይደለም፣ በዚህም ምክንያት ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም በኋላ መንግሥት የለም፣ ሕዝብ እና የመንግሥት መዋቅር ለፌደራል እና የክልል መንግሥታት ሊታዘዙ አይገባም» በሚል ቅስቀሳ ሲደረግ መቆየቱን እና አሁንም እየተደረገ እንደሚገኝ ለማስተዋል ችለናል።
ይህ ቅስቀሳ የሀገራችንን ሰላም እና መረጋጋት ከማወክ እና የዜጎችን ሕይወት አደጋ ላይ ከመጣል በዘለለ ፋይዳ እንደሌለው የኢትዮጵያ ሕዝብ በደንብ እንደሚገነዘብ እናውቃለን። ይህንን ቅስቀሳ እያደረጉ ያሉ አካላትም ከዚህ ተግባራቸው ተቆጥበው የጋራ ሀገራችን ሰላም እና የዜጎች ደህንነት ተጠብቆ በሰላማዊ መንገድ ችግሮቻችንን መፍታት ወደምንችልበት የውይይት መድረክ ከመምጣት ውጪ በሁከት እና በጉልበት ወደሥልጣን ለመውጣት የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ለራሳቸውም ቢሆን የማይጠቅም አደገኛ መንገድ መሆኑን ሊረዱ ይገባል። መንግሥትም እነዚህን ቅስቀሳዎች በንቃት እየተከታተለ አደጋ ከመድረሱ በፊት የመከላከል እና አደጋ ለማድረስ የሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ የሀገር ሰላምን እና የዜጎችን ደህንነት የማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣ እናሳስባለን።
ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ዘንድሮ እንዲካሄድ የተወሰነውን 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃ እና ፍትሃዊ ማድረግን ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባው እና ምርጫው እስከሚካሄድ እና የህዝብ ድምፅ ያገኘው ተለይቶ እስከሚታወቅ ድረስ የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ፣ የሀገር ሉዓላዊነትን ማስከበር እና ምርጫውን ነፃ እና ፍትሃዊ ከማድረግ ጋር በቀጥታ ግንኙነት የሌላቸውን በተለይም በምርጫው የሚወዳደሩ ፓርቲዎች የተለያየ ፖሊሲ አቅርበው የሕዝብን ቅቡልነት ለማግኘት በሚወዳደሩባቸው ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ከማሳለፍ እና ከመተግበር እንዲቆጠብ እናሳስባለን።
እኛንም ጨምሮ በሀገራችን የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ በነፃነት ተንቀሳቅሰው ሃሳባቸውን መግለፅ እንዲችሉ ከዚህ ቀደም በተስማማንበት የፖለቲካ ፓርቲዎች የቃል ኪዳን ሰነድ መሰረት የምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሰላማዊ፣ ሕጋዊ እና የሌሎችን መብት ያከበረ መሆኑን እያረጋገጥን 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃ እና ፍትሃዊ እንዲሆን የሚጠበቅብንን ሁሉ እንድናደርግ እንጠይቃለን። በሀገራችን የምትንቀሳቀሱ የሲቪክ ተቋማትም የፖለቲካ ፓርቲዎች የተስማሙበትን የቃልኪዳን ሰነድ እንዲያከብሩ ግፊት እንድታደርጉ እና በጋራ ሊሠሯቸው እና ሊስማሙባቸው በሚገቡ ተጨማሪ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረግ የሚችሉበት መድረክ እንድታዘጋጁ የአደራ ጥሪያችንን እያስተላለፍን በመድረኮቹ ላይ በንቃት ለመሳተፍ ያለንን ፍላጎት ከወዲሁ ለመግለጽ እንወዳለን።
መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በሀገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለምንገነባው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መደላድል የምንጥልበት ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን በመገንዘብ የምርጫውን ሂደት ከአሁን ጀምሮ በንቃት እንዲከታተል እና ምርጫው ሰላማዊ፣ ነፃ እና ፍትሃዊ መሆኑን ለማረጋገጥ የሚጠበቅባችሁን ሁሉ እንድታደርጉ የአደራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
መስከረም 26 ቀን 2013 ዓ.ም