እናንተ የቀድሞ በሉት እኛ የመሪያችን ስም አይጠፋንም፡፡ አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትራችን አብይ ነው፡፡
****
ከፍቅሩ ምስጋናው
የተፎከረበት ቀን ደርሶ መስከረም 25ን አይተናታል፡፡ መስከረም 25 ከሌሎቹ ቀኖች የተለየች የምትሆንበት አንዳች ምክንያት እንደማይኖር ቀድሞም እናውቅ ነበር፡፡ ከመስከረም 25 በኋላ ተአምር ይሆናል ብለው የጠበቁት ወገኖች ብዙ መክረውናል፡፡
የመጀመሪያ ምክራቸው ሆ ብለን ቤተ መንግስት እንድንገባና እነሱን ባባረርንበት መንገድ አብይን እንድናስወጣ ነው፡፡ ቀኑ ሲቃረብ ያ እንደማይሆን ሲያውቁ ሌላ ስልት ነድፈው የጥላቻን በመስበክ ተጠመዱ፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሉ አዲስ ስም አወጡ፡፡ እኛ የመሪያችን ስም አይጠፋንም ጠቅላይ ሚኒስትራችን አብይ ነው፡፡
የአብይ መንግስት ችግር ቢኖርበት እንኳን የኢትዮጵያ ህዝብ በህወሃት ሊቀይረው ይሞክራል ብሎ ማሰብ ሃያ ሰባት አመት የመሩትን ዜጋ አለማወቅ ነው፡፡ ሲዳማ እኮ ክልል ልሁን ብሎ አደባባይ ሳር ይዞ ሲወጣ በጥይት ያለቀው በህወሃት ነው፡፡ ወላይታ እኮ ክልል ልሁን ያለው የአክሱም ሐውልት ምንህ ነው ባለው መሪ ጊዜ አይደለም፡፡ ዛሬ ደቡብ የራስ አስተዳደር ጥያቄ ያነሳው መልሱ ጥይት እንደማይሆን አውቆ ነው፡፡
ዛሬ አፋርና ሱማሌ ቢያንስ ገዢ ፓርቲ ናቸው፡፡ ዛሬ ቢያንስ እሬቻ ላከብር ብሄድ በአስለቃሽ ጭስ አልቃለሁ ብሎ የማይሳቀቅ ኦሮሞ የኦነግን ባንዲራ ለብሶ አደባባይ የሚሄድ ግንቦት ሰባት መሆን የማያስኮላሸው ዜጋ በምን ስልት ህወሃትን ይናፍቃል?
ኢህአዴግን ወደነው አንድም ቀን አድረን አናውቅም፤ ከደርግ የከፋ ሰው በላ ሥርዓት መሆኑንም ጠንቅቀን የምንረዳ ያየን እና ዛሬ በየቦታው እየፈነዳ ያለውን ቦንብ የቀበረ መሆኑን የምናምን ህዝቦች ነን፡፡ ታዲያ እንዴት ከዶክተር አብይ ህወሃትን እንመርጣለን? ምን ችግር ቢኖርበት በምን አግባብ ከተመስገን ጥሩነህ አዲሱ ለገሰ ይመረጣል? በምን ሞራል ከርስቱ ይርዳው ካሱ ኢላላ ይሻላል እንላለን፤ እንዴት አያውቁንም?
የለውጥ ሃይሉ ብዙ ሺህ ችግሮች ሊኖሩበት ይችላሉ፤ ትሪሊየን ከደረሰውና ሀገር ሊገድል ሞክሮ አልሞት ብላው ከሚሰቃየው ጥቂት ከትግራይ አልፎ ህወሃት ውስጥ የመሸገ ወንበዴ ጋር የለውጥ ሃይሉ አይነጻጸርም፡፡
ዛሬ መስከረም 25 ነው፡፡ ምኞት እዚያው ውስኪ የሚጠጣበት ጠረጴዛ ላይ ይቀራል እንጂ የሚቀየር አንዳች ነገር የለም፡፡ ህወሃት ቆዳዋንም ስሟንም ግብሯንም ብትቀይር በኢትዮጵያውያን እጣ ፈንታ አንዳች ድርሻ አይኖራትም፡፡ የህወሃት ምክር ልክ ቢሆን እንኳን ልክ አይደለም፡፡ እናም መሪያችን የሰላም ኖቤል አሸናፊው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ነው፡፡