Connect with us

የእነ አቶ ጃዋር ጠበቆች ማስፈራሪያና ጫና እየደረሰብን ነው አሉ

የእነ አቶ ጃዋር ጠበቆች ማስፈራሪያና ጫና እየደረሰብን ነው አሉ
በድሬቲዩብ ሪፖርተር

ህግና ስርዓት

የእነ አቶ ጃዋር ጠበቆች ማስፈራሪያና ጫና እየደረሰብን ነው አሉ

ከሦስት ወራት በፊት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኘው የእነ አቶ ጃዋር መሐመድ ጠበቆች ጫናና ማስፈራሪያ ከተለያዩ አካላት እየደረሰብን ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ይህንን የተናገሩት ከድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ ከተከሰተው ሁከት ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉትን የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ አባላት እንዲሁም ሌሎች ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ በተለያዩ ፍርድ ቤቶች እየተከታተሉ የሚገኙት 13 አባላት ያሉት የሕግ ባለሙያዎች ቡድን ተወካይ የሆኑት አቶ ምስጋን ሙለታ ናቸው።

እሳቸው እንደሚሉት ከጠበቆቹ መካከል በተወሰኑት ላይ በተለያዩ አጋጣሚዎች እየገጠማቸው ያለው ጫናና ማስፈራሪያና እየበረታ መምጣቱን ምሳሌዎች በመጥቀስ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የጠበቆቹ ቡድን ተወካይ በእራሳቸውና በባልደረቦቻቸው ላይ እየደረሰ ነው ያሉትን ችግር በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጡ ቢቢሲ ያነጋርናቸው የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጽህፈት ቤት ምክትል ጠቃላይ ዐቃቤ ሕግ የሆኑት አቶ ፍቃዱ ፀጋ፤ ጠበቆቹ እየደረሰብን ነው ያሉትን ተጽዕኖ አስመልክቶ ጽህፈት ቤታቸው የደረሰው መረጃው እንደሌለ ገልፀዋል።

 “የተባለውን ነገር በተመለከተ መረጃ የለኝም። እነርሱ የሕግ ባለሙያዎች ናቸው፤ የሕግ ባለሙያ ስለሆኑ እንዲህ አይነት ችግር ሲገጥማቸው ለየትኛው አካላት ማሳወቅ እንዳለባቸው ያውቃሉ። እስከ አሁን በዚህ ረገድ አንድም የደረሰን ቅሬታ የለም” ብለዋል።

አቶ ጃዋር መሐመድ እና በቀለ ገርባን ጨምሮ በሌሎቹ ተከሳሾች ጉዳይ ላይ በቡድን በመሆን ፍርድ ቤት በመቅረብ ጉዳያቸውን እየተከታተሉ የሚገኙት እነዚህ ጠበቆች፤ “በሙያችን ለደንበኞቻችን ቆመን በመከራከራችን ምክንያት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚደርስብን ማስፈራሪያ እና ችግር እየበረታ መጥቷል” ሲሉ ተወካያቸው አቶ ምስጋን ተናግረዋል።

አቶ ምስጋን ሙለታ እንደአብነትም በእራሳቸው ላይ ደረሰ ያሉትን አጋጣሚ ሲያስረዱ “አንድ ቀን በቡራዩ ከተማ ፍርድ ቤት ለአንድ ተከሳሽ ተከራክሬ ስወጣ በፖሊስ ተጠራሁ። ከዚያም ወደ ቢሮ እንደገባሁ ያስጠራኝ ሰው ዘለፋና ተገቢ ያልሆኑ ቃላትን በመጠቀም ስልኬን ተቀብለው መፈተሽ ጀመሩ። ሸኔ ነህ ብለውም አስረው አጉላልተውኛል” ይላሉ።

ከዚህ በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ የአራዳ ፖሊስ ጣቢያ የተገኙት ሌላ የጠበቆቹ ቡድን አባል የሆኑት አንድ የሕግ ባለሙያ ላይ በጦር መሳሪያ ማስፈራራት እንደተፈጸመባቸው ጠቅሰዋል።

እንዲሁም ባልታወቁ ሰዎች ከጠበቆቹ መካከል መኪና ተሰብሮ የተለያዩ ሰነዶች እንደተወሰደባቸው በማንሳት ጫናው የተለያየ መሆኑን አቶ ምስጋናው ጨምረው ገልፀዋል።

በዚህም ሳቢያ “ጠበቆች በሚደርስባቸው የመታሰር፣ ዘለፋ፣ ማንጓጠጥ እና ማስፈራራት የተነሳ የመኖሪያ አካባቢያቸውን ለቅቀው እስከመሄድ የደረሱም አሉ። ስለዚህ የሚታይ ተጽዕኖና የሥነ ልቦና ጫና እየደረሰብን ይገኛል” በማለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ምክትል ጠቃላይ ዐቃቤ ሕጉ አቶ ፍቃዱ ፀጋ በበኩላቸው “እስካሁን ጠበቆች ፍርድ ቤት ቀርበው በነጻነት ለደንበኞቻቸው ሲከራከሩ እያየን ነው” በማለት “ነገር ግን እንዲህ አይነት ቅሬታ ካላቸው ደግሞ እዚያው ፍርድ ቤት ላይ እየገጠመን ነው የሚሉትን ጉዳይ በማንሳት እንዲስተካከልላቸው መጠየቅ ይችላሉ” ሲሉ ለቢቢሲ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

አቶ ፍቃዱ እንደሚሉት የተጠቀሱት አይነት ችግሮች አጋጥመው ከሆነ “በጠበቆች ላይ የሚፈፀም ተጽዕኖ በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት የለውም” ብለዋል።

 “ግለሰብ ይህንን ድርጊት ሊፈጽም ይችላል። በቢሮ ደረጃ እንዲህ አይነት ነገር ይፈፀማል ብዬ አላስብም። ተደርጎ ከሆነ ደግሞ ትልቅ ወንጀል ነው” ሲሉም አክለዋል።

 ጨምረውም ጠበቆቹ በሙያቸው በሕግ ፊት ለተከሳሾች መብት ተከራካሪ መሆናቸው አመልክተው፤ ይሁን እንጂ “በቀረበው ቅሬታ እውነትነት ላይ ጥርጣሬ አለኝ” ሲሉ ተናግረዋል።

 ነገር ግን የትኛውም ጠበቃ ደረሰብኝ ለሚለው የትኛውም አይነት ተጽዕኖ ተጨባጭ መረጃ ካለው ወደ ፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመውሰድ ቅሬታውን ማቅረብ እንደሚችል አቶ ፍቃዱ ገልፀዋል።

 ከወራት በፊት በአዲስ አበባና በአንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች ተከስቶ ለበርካታ ሰዎች ህይወት መጥፋትና በቢሊዮን ብሮች ለሚገመት ንብረት ውድመት መከሰት ምክንያት ከሆነው ሁከት ጋር በተያያዘ በርካቶች ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ነው።

 ከዚሁ ጋር በተያያዘ ክስ ለተመሰረተባቸው የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና የሌሎችንም ጉዳይ በተመለከተ በፍርድ ቤት ተጠርጣሪዎች በመወከል ጉዳያቸውን የሚከታተሉ ከአስር በላይ የሚሆኑ ጠበቆች ያሉበት አንድ የሕግ ባለሙያዎች ቡድን ጥብቅና መቆሙ ይታወቃል።(BBC)

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top