Connect with us

ዋና ዓቃቤ ሕጉ ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲጠየቁ አቤቱታ ቀረበ

ዋና ዓቃቤ ሕጉ ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲጠየቁ አቤቱታ ቀረበ
Photo: Social Media

ህግና ስርዓት

ዋና ዓቃቤ ሕጉ ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲጠየቁ አቤቱታ ቀረበ

ዋና ዓቃቤ ሕጉ ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲጠየቁ አቤቱታ ቀረበ

የእርስ በርስ ጦርነት በማስነሳት፣ የሽብር ወንጀል ለመፈጸም በመሰናዳት፣ ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ይዞ በመገኘትና በቴሌኮም የማጭበርበር ወንጀሎች ክስ የተመሠረተባቸው እነ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ የፌዴራል ዋና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በፍርድ ቤት ቀርበው እንዲጠየቁላቸው አቤቱታ አቀረቡ፡፡

አቤቱታው የቀረበው አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ ሐምዛ አዳነና አቶ ሸምሰዲን ጠሃን ጨምሮ 24 ተከሳሾች የተካተቱበትን ክስ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሕገ መንግሥት ጉዳዮችና የሽብርተኝነት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት፣ በንባብ ለማሰማት በተሰየመበት መስከረም 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ነው፡፡

አቤቱታውን ያቀረቡት አቶ በቀለና አቶ ጃዋር ናቸው፡፡ ለችሎቱ እንዳስረዱት፣ የኢፌዴሪ ዋና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጌዴዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) እነሱን (ተከሳሾቹን) በሚመለከት ለውጭ አገር መገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ይኼ መግለጫ የተሰጠው እነሱ (ተከሳሾቹ) ራሳቸውን መከላከል ወይም ምላሽ መስጠት በማይችሉበት ሁኔታ ላይ ሆነው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከፍርድ በፊት ወይም በቀረበባቸው ክስ ላይ ክርክር አድርገውና በማስረጃ ተረጋግጦባቸው ‹‹ወንጀለኛ›› የሚል ፍርድ እስከሚሰጥባቸው ድረስ፣ እንደ ማንኛውም ሰው ንፁህ ሆነው የመገመት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን የጣሰ መግለጫ መስጠታቸውንም አስረድተዋል፡፡

አቶ በቀለ ነፃ ሆነው መገመት ሲገባቸው ዋና ዓቃቤ ሕጉ አክራሪዎች፣ ብሔርተኞች፣ ሁከትና ብጥብጥ ፈጣሪዎች መሆናቸውን እንዳረጋገጡ አድርገው የሰጡት መግለጫ፣ በተያዘው የፍርድ ቤት ሒደት ላይ ተፅዕኖ ከመፍጠሩም በተጨማሪ፣ መንግሥት ፍርድ ቤቱን የፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ ዋና ዓቃቤ ሕግጉ ከፍተኛ ዕውቀት ያላቸው መሆናቸቸውን እንደሚያውቁ የተናገሩት አቶ በቀለ፣ ሕጉን ጠብቀው መሥራት ሲገባቸው የፖለቲካ አመለካከታቸው በልጦባቸው እንደ ፈረጇቸው ወይም ፍርድ እንደሰጡባቸው ገልጸዋል፡፡

ዋና ዓቃቤ ሕጉ ያሉበት የሥልጣን ቦታ ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃርና የሕግ ባለሙያም ስለሆኑ፣ እነሱ (ተከሳሾቹ) መልስ መስጠት በማይችሉበትና በሕግ ተይዞ ዕልባት ባልተሰጠው ጉዳይ ላይ መግለጫ ሊሰጡ የቻሉበትን ጉዳይ በችሎት ቀርበው እንዲያስረዱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል፡፡ ‹‹እንደ እኔ አመለካከት ይኼንን ያደረጉት ዕውቀትና ችሎታ አጥተው ሳይሆን፣ የፖለቲካ ወገንተኝነታቸውን ለማሳየት በመሆኑ ይኼ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው፡፡ በመሆኑም ዋና ዓቃቤ ሕጉ ከኃላፊነታቸው መነሳት አለባቸው፤›› በማለት አቶ በቀለ ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል፡፡

አቶ ጃዋርም አቶ በቀለ ያቀረቡን አቤቱታ አጠናክሮ፣ መግለጫው በዋና ዓቃቤ ሕጉ ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ በአያያዛቸውም ላይ ለውጥ መደረጉን ጠቁሟል፡፡ በክሱ ላይ ጳጳሳትንና የሃይማኖት መሪዎችን ለማስገደል እንዳሴሩ ተደርጎ መጠቀሱና ሌላውም የክስ ዝርዝር ክስ ሳይሆን ስም ማጥፋት እንደሆነ ተናግሮ፣ ድርጊቱ ከእነሱም አልፎ በቤተሰቦቻቸውም ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩን አስረድቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ ፍትሕ ሊሰጥ ተቀምጦ እያለ ዋና ዓቃቤ ሕጉ ፍርድ ከሰጡ፣ የእነሱ ፍርድ ቤት መመላለስ ትርጉም እንደሌለውም ተናግሯል፡፡ የፍትሕ አካሉ ከወገንተኝነት በላይ ከሆነና እውነተኛ ፍትሕ ለመስጠት እየተሠራ ከሆነ፣ ዋና ዓቃቤ ሕጉ በችሎት ተጠርተው ሊጠየቁ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡ ያ ካልሆነ ግን ለሕይወታቸውም የሚያሠጋቸው መሆኑን ጠቁሞ፣ እዚያው ባሉበት የሚጣልባቸውን ቅጣት ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ ተከሳሾች ነፃ ሆነው የመገመት መብት እንዳላቸው ጠቁሞ፣ ማንም ቢሆን ሰብዓዊ መብቱ መጣስ አለበት ብሎ እንደማያምን አስረድቷል፡፡ ነገር ግን ስለመብቶቻቸው ሲያነሱ ችሎቱን የሚመጥንና ፍርድ ቤቱም ውሳኔ ሊሰጥበት በሚችለው ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲናገሩ እንጂ፣ ከመዝገቡ ውጪ መናገር ተገቢ አለመሆኑን ለፍርድ ቤቱ አሳስቧል፡፡

ፍርድ ቤቱም ተከሳሾች ድምፃቸውን ማሰማት እንደሚችሉ ጠቁሞ፣ ‹‹መንግሥት ስለከሰሳችሁ እናንተም እየተቃወማችሁ ነው፡፡ ከሥነ ሥርዓት ውጪ ስትናገሩ ችሎቱም ሆነ የችሎት ታዳሚ በሚታዘባችሁ ልክ መሆን የለበትም፡፡ በችሎት የተገኙ የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃንም እናንተ ያላችሁትን ብቻ ሳይሆን፣ የግራ ቀኙን ሰምተው እንዲዘግቡ በአግባቡና ሥነ ሥርዓቱን በተከተለ ሁኔታ መከራከር አለባችሁ፤›› በማለት ክሱን በተመለከተ ብቻ እንዲከራከሩ ነግሯቸዋል፡፡

የዕለቱ የፍርድ ቤት ሙግት የጀመረው ገና ችሎቱ እንደተሰየመ ነበር፡፡ አቶ ጃዋር፣ አቶ በቀለ፣ አቶ ሐምዛና ሌሎች ጥቂት ተከሳሾች የማረሚያ ቤቱን ቢጫ ዩኒፎርም ለብሰው (አብዛኞቹ አልለበሱም) ዳኞች ችሎቱን ለማስጀመር በዙፋናቸው ላይ እንደተቀመጡ፣ ሁሉም ተከሳሾች ተጣምረው የታሰሩበትን ካቴና ከፍ በማድረግ አቤቱታ እንዳላቸው መናገር ጀመሩ፡፡ ፍርድ ቤቱ ተቀምጠው አንድ ተከሳሽ እንዲያስረዳ አስታውቆ፣ ከዚያ በፊት ግን የታሰሩበት ካቴና እንዲፈታላቸው ለማረሚያ ቤቱ ፖሊስ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ አቶ ሐምዛ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ ከማረሚያ ቤት ወደ ፍርድ ቤት ለመምጣት ያስነሷቸው ከንጋቱ 12፡30 ሰዓት ነው፡፡ እጃቸው በካቴና የታሰረው ደግሞ አንድ ሰዓት ላይ ነው፡፡ ቁርስ ሳይበሉ ወደ ፍርድ ቤት ካመጧቸው ጀምሮ፣ ችሎቱ እስከ ተሰየመበት 5፡20 ሰዓት ድረስ እጃቸው በካቴና መታሰሩን አስረዳ፡፡ ለምን ታሰርን ብለው ሳይሆን ደጋግመው እንዲፈቷቸው ቢጠይቁም ሊፈቷቸው አለመቻላቸውንና ጫና እንዲሰማቸው እየተደረገ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አቤቱታቸውን አሰምቷል፡፡

ጠበቆቻቸው ደግሞ ባቀረቡት አቤቱታ ጉዳዩ ውስብስብ እንደሆነ እንደሚረዱ ጠቁመው፣ የተፋጠነ ፍትሕ ለመስጠትና ለማግኘት ችሎቱ ቀደም ብሎ ሥራ እንዲጀምር (5፡20 ሰዓት ነው የጀመረው) ጠይቀዋል፡፡ አሁን የመስመር ልዩነት ቢፈጠርም ደንበኞቻቸው ለዚህ አገር የሰብዓዊ መብት መከበር መታገላቸውን ጠቁመው በተለይ አቶ ጃዋር፣ አቶ በቀለና አቶ ሐምዛ ከፍተኛ የፖለቲካ አመራር በመሆናቸው፣ እጃቸው በካቴና መታሰር እንደሌለበት ተናግረዋል፡፡ ከዓመታት በፊት መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) በተጠረጠሩበት ወንጀል ፍርድ ቤት ሲቀርቡ እጃቸው በካቴና መታሰሩን ያየው ፍርድ ቤት፣ ‹‹እሳቸው ከፍተኛ የፖለቲካ ሰው በመሆናቸው እጃቸው በካቴና መታሰር የለበትም፤›› ማለቱን በማስታወስ፣ እነ አቶ ጃዋርም በምርመራ ወቅት ሳይታሰሩ ክስ ከተመሠረተ በኋላ አስሮ ማቅረብ ለውጥ ስለማያመጣ፣ ሳይታሰሩ እንዲቀርቡ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠበቆቹ ጠይቀዋል፡፡

ሌላው ጠበቆቹ ያመለከቱት አቶ ሸምሰዲን ጠሃ በቁጥጥር ሥር በዋለበት ጊዜ በፖሊሶች በደረሰበት ድብደባ ጆሮው በመጎዳቱ፣ ፍርድ ቤት ሕክምና እንዲያገኝ የሰጠው ትዕዛዝ አለመከበሩን ነው፡፡ ሕመሙ እየበረታበት በመሆኑ ሕክምና እንዲያገኝ ጥብቅ ትዕዛዝ እንዲሰጥና ማረሚያ ቤቱ ለምን የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ እንዳላከበረ እንዲጠየቅላቸውም አመልክተዋል፡፡

አቶ ጃዋር በውጭ አገር ከሚገኙት ባለቤቱና ልጁ ጋር በሳምንት ሦስት ጊዜ በራሱ ወጪ በስልክ እንዲገናኝ የሥር ፍርድ ቤት ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት ማረሚያ ቤቱ ሁኔታዎችን እንዲያመቻችለት ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡ ትዳር ሊመሠርት ሁሉን ዝግጅት አጠናቆ ሁለት ሳምንት ሲቀረው የታሰረው መስተዋረድ ተማም የተባለው ተከሳሽ፣ ዕጮኛው ውጭ አገር ስለሆነች እሷንና እናቱን በስልክ እንዲያገኛቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸውም ጠበቆቻቸው አመልክተዋል፡፡

ከአቶ በቀለ፣ ከአቶ ጃዋር፣ ከአቶ ሐምዛና አቶ ሸምሰዲን በስተቀር ሌሎቹ ተከሳሾች ተለያይተው በሦስት ቦታ መታሰራቸውን አስረድተው፣ ሁሉም የተከሰሱበት ክስ የሚያገናኛቸው ቢሆንም፣ ማረሚያ ቤቱ እንዲገናኙ ባለመፍቀዱ ስለክሱና ቀጣይ ስለሚደረገው ክርክር ማነጋገርና መወያየት አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ በአንድ ቦታ ላይ አግኝተው እንዲወያዩ ማረሚያ ቤቱ እንዲያመቻችላቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸውም ጠይቀዋል፡፡ አቶ አረፋት አቡበከር የተባለው ተከሳሽ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ተፈታኝ በመሆኑ አስፈላጊው የትምህርት ቁሳቁስና ማጥኛ ቦታ እንዲዘጋጅለት፣ እንዲሁም በአጃቢ ወጥቶ ፎርም እንዲሞላ እንዲፈቀድለት፣ የተከሳሾች ዘመዶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ጠበቆቻቸውና ጓደኞቻቸው ያለ ገደብ እንዲጎበኟቸው እንዲፈቀድላቸው አመልክተዋል፡፡ አቶ ጃዋር በግሉ እንዲታከም በሥር ፍርድ ቤት የተሰጠው ውሳኔ በማረሚያ ቤቱ እየተፈጸመ ባለመሆኑም፣ ተፈጻሚ እንዲሆን ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸውም ጠይቀዋል፡፡

አቶ ደጀኔ ጣፋም ባቀረቡት አቤቱታ በታሰሩበት ቦታ ምሽት ላይ እስር ቤቶች ከተዘጉ በኋላ አሰሳ የሚያደርጉ ሰዎች እንደሚመጡባቸው አስታውቀው፣ ለሕይወታቸው እየሠጉ መሆኑን በመጠቆም ፍርድ ቤቱ እንዲያውቅላቸው ተናግረዋል፡፡

ተከሳሾቹ በራሳቸውና በጠበቆቻቸው አማካይነት አቤቱታቸውን ለፍርድ ቤቱ ካሰሙ በኋላ፣ ፍርድ ቤቱ በተነሱት አቤቱታዎች ላይ ትዕዛዝ እንደሚሰጥ አሳውቆ፣ ከሳምንት በፊት በነበረ ችሎት ሳይቀርቡ የቀሩትን አቶ ደጀኔ ጉተማ፣ አቶ ብርሃነ መስቀል አበበና አቶ ፀጋዬ ረጋሳ የተባሉን ተከሳሾችን ፖሊስ አፈላልጎ እንዲያቀርብ ተሰጥቶት በነበረው ትዕዛዝ ላይ ምላሽ መስጠቱን አስታውቋል፡፡ በመሆኑም ፖሊስ ተከሳሾቹ በውጭ አገር የሚኖሩ መሆናቸውን እንዳረጋገጠ በደብዳቤ መግለጹን ጠቁሞ፣ በችሎት ለቀረቡ ተከሳሾች ክሱን በንባብ አሰምቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ ባሉበት ክሱን በንባብ አሰምቶ እንደ ጨረሰ ዘጠኝ ተከሳሾች አማርኛ እንደማይሰሙ በመግለጻቸው በአጭሩ የክሱ ይዘት በአስተርጓሚ እንዲነገራቸው ትዕዛዝ ቢሰጥም፣ እያንዳንዱ ዝርዝር ተተርጉሞ መስማት እንደሚፈልጉ በመግለጽ ተቃውመዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ መብታቸው መሆኑን አረጋግጦ ጊዜ ቢወስድም እንደሚተረጎምላቸው ሲገልጽ፣ ከጠበቆቻቸው ጋር ተመካክረው በአጠቃላይ ስለክሱ ሁኔታ ሊያስረዷቸው (ጠበቆቻቸው) በመስማማታቸው ተቃውሟቸውን አንስተዋል፡፡

ሌላው ተከሳሾች ያነሱት ጥያቄ፣ ፍርድ ቤቱ ክሱን በንባብ አሰምቶ እንደ ጨረሰ ዓቃቤ ሕግ በክሱ 146 ምስክሮች፣ 114 የሰነድ ማስረጃዎች፣ 70 የፎረንሲክ ምርመራ ማስረጃዎች፣ የተለያዩ የቴሌኮምና የሲዲ ማስረጃዎችን ማቅረቡንና በርካታ በኤግዚቢት የተመዘገቡ ማስረጃዎች እንዳቀረበ በመግለጹ፣ ሲዲ እንዳልደረሳቸውና አጠቃላይ ማስረጃው ከስልክ የተወሰደ ቢመስላቸውም፣ ምንጩን ስላላወቁት እንዲገለጽላቸው ነው፡፡ በሥር ፍርድ ቤት በቅድመ ምርመራ የተሰጠ ማስረጃም እንዳልደረሳቸው ጠቁመው፣ እንዲደርሳቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡

አቶ ሸምሰዲን ሌላው ያነሳው ጥያቄ ነፍስ ካወቀ ጀምሮ በኢሬቻ በዓል ላይ ቀርቶ ስለማያውቅ በአጃቢ ወጥቶ በበዓሉ አከባበር ላይ እንዲገኝ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ያመለከተ ቢሆንም፣ ምላሽ አለመሰጠቱን ነው፡፡ በዓሉን በማረሚያ ቤት ሆኖም ቢሆን የሥርዓቱን ልብስ ለብሰው እንዲያከብሩ፣ ማረሚያ ቤቱ ማክበሪያ ቦታ እንዲያዘጋጅላቸውና ልብሱም እንዲገባ እንዲፈቀድላቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቋል፡፡

ከክሱ እንደተረዱት ዓቃቤ ሕግ በክሶቹ ላይ የጠቀሳቸው የሕግ አንቀጾች ለጊዜው ዋስትና ስለሚከለክሉና በክስ መቃወሚያቸው ስለክሶቹ አጠቃላይ ይዘትና ሁኔታ በዝርዝር በሚያቀርቧቸው መቃወሚያ ነጥቦች፣ ክሱ ይሻሻላል የሚል እምነት ስላላቸው ለጊዜው የዋስትና መብት ጥያቄ እንደማያቀርቡ ጠበቆቹ ለፍርድ ቤቱ አሳውቀዋል፡፡ ሌላው ስለዋስትና መብት ማመልከት የማይፈልጉበት ምክንያት፣ የፌዴራል ፍርድ ቤት ዋስትና ቢፈቅድም የክልል ፖሊስ ስለሚያስር፣ በዋስትና ጉዳይ ላይ መከራከሩ ጥቅም እንደሌለው በማስረጃ በተጨባጭ ማስረዳት ስለሚችሉ መሆኑን ሲናገሩ፣ ዓቃቤ ሕግ ተቃውሞ አሰምቷል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው መቃወሚያ እንዳስረዳው፣ ችሎቱ ማከራከር ያለበት በቀረበው መዝገብ ላይ ብቻ ነው፡፡ ከችሎቱ ውጪ ያሉ ጉዳዮች ሲነሱም፣ መከራከሪያ ወይም ማነፃፀሪያ ሊሆኑ አይገባም፡፡ ፍርድ ቤት የፈታቸውን ፖሊስ አይፈታቸውም የሚለው መፈጸም ያለበት በፍርድ ቤቱ መሆን እንዳለበትና ፍርድ ቤቱ ራሱን ማስከበር እንዳለበትም ዓቃቤ ሕግ ተናግሯል፡፡

የሲዲ ማስረጃን በሚመለከት ኦሮሚኛ በመሆኑ በችሎት በአስተርጓሚ እንዲሰሙት ይደረጋል በሚል አለማያያዙን አስታውቋል፡፡ በአጠቃላይ ተከሳሾች የተጠቀሰባቸው የወንጀል ሕግ አንቀጽ ዋስትና እንደሚያስከለክል አውቀው ስለዋስትና መብት እንደማያነሱ በማረጋገጣቸው፣ በማረሚያ ቤት ሆነው ክሳቸውን እንዲከታተሉ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ዓቃቤ ሕግ ጠይቋል፡፡

አቶ በቀለ ስለክሱ ያልገባቸው ነገር እንዳለ በመግለጽ እንዲናገሩ ሲጠይቁ ፍርድ ቤቱ፣ በክስ መቃወሚያቸው ላይ ማቅረብ ከሚፈቀድላቸው በስተቀር በችሎት ማስረዳት እንደማይችሉ ነግሯቸዋል፡፡ ነገር ግን እሳቸው ‹‹ለምን ድምፃችን ይታፈናል? የመናገር መብት ይሰጠን›› በማለታቸው፣ ፍርድ ቤቱ ‹‹ድምፃችሁን ማሰማት ትችላላችሁ፡፡ ነገር ግን እናንተንም ትዝብት ውስጥ የሚጥላችሁና ፍርድ ቤቱን የማይመጥን መሆን የለበትም፤›› ብሎ ፈቅዶላቸዋል፡፡

አቶ በቀለ ሲፈቀድላቸው እንደገለጹት፣ የሚናገሩት የመናገር አባዜ ይዟቸው ወይም ጥፋታቸው ተሸፋፍኖ እንዲቀር ሳይሆን፣ ሕዝብም ጥፋታቸውን አውቆ ከቅጣታቸው እንዲማርበት ነው፡፡ የቀረበባቸው ክስ ከድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ ሁከትና ብጥብጥ ተነስቷል የሚልና ግልጽ መሆኑን ጠቁመው፣ ይኼ ዓይነት ክስተት በሌሎችም አገሮች እንደሚያጋጥም ተናግረዋል፡፡ የሁከትና የብጥብጡ ምክንያት ግን እነሱ ሳይሆኑ ሕዝቡ ብሦት ስላለበት መሆኑን ጠቁመው፣ መንግሥት ፖለቲከኞችን ሰብስቦ ከማሰሩ በፊት ንፁህ መሆን አለመሆናቸውን ማረጋገጥ እንዳለበትም አክለዋል፡፡ ንፁህ ካልሆኑ ደግሞ ያንን እስከሚያረጋግጥ ድረስ፣ ንፁህ ሆነው የመገመት መብታቸውን እንዲያረጋግጥላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ነፍጠኛ፣ አማራ፣ ኦርቶዶክስ እያለ ደበላልቆ ያቀረበው ግልጽ ያልሆነ ክስ መሆኑን ጠቁመው፣ ክሱ እንጂ እነሱ አገር አጥፊ አለመሆናቸውንም አቶ በቀለ ገልጸዋል፡፡

ሕዝብ በመንግሥት ላይ እንዳነሳሱ ዓቃቤ ሕግ በክሱ መግለጹን የጠቆሙት አቶ በቀለ እንዳስረዱት፣ በፖለቲካ ድርጅት ተሰባስበው የፓርቲ ፈቃድ የወሰዱት፣ የተበደለ ሕዝብ በመንግሥና አስተዳደሩ ላይ ለማነሳሳትና ለውጥ ለማምጣት ነው፡፡ ይህ ሥራቸው መሆኑንና በተጻፈ ሕግ የሚመራ አገር ላይ በመሆናቸው፣ መንግሥት ሕጋዊነቱን አክብሮ እንዲሠራ ማድረግ፣ ያ ካልሆነ ደግሞ ሕዝብን በማነሳሳት ለውጥ እንዲመጣ የማድረግ የፖለቲካ ሒደት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ሙግታችን የፖለቲካ በመሆኑ ዳኞች በእኛና (ኦፌኮ) በብልፅግና ፓርቲ መካከል ሆናችሁ ዳኙን፤›› ብለዋል፡፡

የግራ ቀኙን አቤቱታ የሰማው ፍርድ ቤት በሰጠው ትዕዛዝ፣ ማረሚያ ቤቱ ተከሳሾችን በካቴና ለረዥም ሰዓታት እንዲታሰሩ ያደረገው ለምን እንደሆነ በጽሑፍ እንዲገልጽ፣ በጠዋት የሚመጡበት አግባብ ካለም በቀጣይ ቀጠሮዎች ቁርስ አዘጋጅቶ እንዲያቀርብ አሳስቧል፡፡

የኦኤምኤን ተወካይ አቶ ቦና ቲቢሌ የተባሉ ተከሳሽ በአጃቢ ወጥተው ውክልናቸውን በሌላ አካል እንዲሰጡ እንዲያደርግ፣ አቶ ሸምሰዲን ሕክምና እንዳያገኙ ያደረገበትን ምክንያት በጽሑፍ እንዲገልጽና በአፋጣኝ ሕክምና እንዲያገኙ እንዲያደርግም ለማረሚያ ቤት ጥብቅ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ጠቅላይ ዋና ዓቃቤ ሕጉ የሰጡትን መግለጫ በሚመለከት በጽሑፍ ምላሽ እንዲሰጡም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

የዋስትና መብትን በሚመለከት ዓቃቤ ሕግ በክሱ ላይ የጠቀሳቸው የሕግ አንቀጾች ከ15 ዓመታት በላይ የሚያስቀጡ ከመሆናቸውም በተጨማሪ የሰው ሕይወትም የጠፋበት በመሆኑ፣ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 63 ድንጋጌ መሠረት የዋስትና መብትን ስለሚከለክል፣ ተከሳሾች በማረሚያ ቤት ሆነው ክሳቸውን እንዲከታተሉ ብይን ሰጥቷል፡፡

የኢሬቻን በዓል አከባበር በሚመለከት በሰጠው ትዕዛዝ፣ በወንጀል የተከሰሰ ሰው ከማረሚያ ቤት ውጪ ያለው መብቱ ለጊዜው ስለሚገደብ፣ አቶ ሸምሰዲን በአጃቢ ወጥተው እንዲያከብሩ ያቀረቡትን ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን ገልጿል፡፡ ነገር ግን ማረሚያ ቤቱ የሌሎች እስረኞችን ሃይማኖትና በዓላት በሚያከብርበት አግባብ፣ የእነሱንም እንዲያመቻች ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ጠበቆች በሦስት ቦታ ተለያይተው የታሰሩትን ደንበኞቻቸውን በአንድ ላይ እንዲያነጋግሩ ማረሚያ ቤቱ ሁኔታዎችን እንዲያመቻችላቸው፣ ተከሳሾች ጠበቆቻቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውን፣ የሃይማኖት አባቶቻቸውን፣ ሕክምናና ሌሎች መብቶቻቸውን በማክበር እንዲፈጽም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

አረፋት የተባለው ተከሳሽ ለ12ኛ መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ እንዲዘጋጅለት፣ አቶ ደጀኔ ጣፋ ‹‹ለሕይወቴ ያሠጋኛል›› ስላሉ ማረሚያ ቤቱ በጽሑፍ ስለአያያዛቸውና ስላለው ጥበቃ እንዲያስረዳ፣ እንዲሁም በሌላ መዝገብ የተመሠረተባቸው ክስ መቋረጡን አስታውቋል፡፡ ጠበቆች በሥር ፍርድ ቤት የተሰማው የቀዳሚ ምርመራ ማስረጃ እንዲደርሳቸው ያቀረቡት ጥያቄ፣ ሕጉ እንዲያያዝ ስለማያዝ ጥያቄውን እንዳልተቀበለው፣ የሲዲውን ማስረጃ ግን ዓቃቤ ሕግ እንዲሰጥ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ሌሎች ማስረጃዎችንና የማስረጃዎቹን ምንጭ በሚመለከት ዓቃቤ ሕግ ሒደቱን ጠብቆ በጽሑፍ ምላሽ እንደሚሰጥ አስታውቆ፣ ክሱ ግልጽ አለመሆኑን በሚመለከት ተከሳሾች መቃወሚያቸውን ጥቅምት 23 ቀን 213 ዓ.ም. በሬጂስትራር በኩል ካቀረቡ በኋላ፣ ዓቃቤ ሕግ ኅዳር 18 ቀን 2013 ዓ.ም. በችሎት ምላሹን ይዞ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በችሎት ያልቀረቡ ተከሳሾች በጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግላቸው ትዕዛዝ በመስጠት የችሎት ውሎውን አጠናቋል፡፡ (ታምሩ ፅጌ ~ ሪፖርተር)

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top