Connect with us

“ድምፅ”

"ድምፅ" መሠረት ጀማነህ (የፓርላማ አባል)

ህግና ስርዓት

“ድምፅ”

“ድምፅ”

መሠረት ጀማነህ (የፓርላማ አባል)

በተሸራረፈ መንገድ ስራ ላይ እየዋለ ያለው ብሔር ተኮር ፌደራሊዝም ዜጎችን ዋጋ እያስከፈለ ቀጥሏል። ራስን በራስ ማስተዳደር ማለት ህዝቦች በአግባቡ የሚወከሉበት አስተዳደር እንጅ በየክልሉ  የሌላ ብሔር  አባላት የሚገለሉበት፣ የሚጠቁበተ አስተዳደር አይደለም። አንዳንድ የክልል መንግስታት አመራሮች ግን ይህን በውል የተገነዘቡ አይመስልም። በዚህም ምክናያት በየክልሉ የሚኖሩ የልዩ ልዩ ብሔር አባላት  በገዛ አገራቸው ባይተዋር የመሆን እድል ገጥሟቸዋል። በዚሁ ምክንያትም  ከለላ ያጡ  ዜጎች ሆነው ይታያሉ። በዚህ ደግሞ የአማራ ብሄር ተወላጆች የአንበሳውን ድርሻ የያዙ ተጠቂዎች ናቸው። ክልላዊ መንግስቱ አለ በሚል እምነት ራሳቸውን ለመጠበቅም ባለመዘጋጀታቸው ምንም ሳይከላከሉ  ጥቃት እየደረሰባቸው ነው።ነገር ግን ቀስ በቀስ ይስተካከላል በሚል እየተጠቁም፣እየሞቱም፣ እየተፈናቀሉም ቢሆን ትእግስትን  መርጠዋል።

በዚህ በላቀ አስተሳሰባቸው ምክናያት እየተጠቁ ላሉ የአማራና የሌሎችም መሰል ተጠቂ ዜጎች የክልል  መንግስታት ከለላ ሊሆኑላቸው ይገባል። ይህ ካልሆነማ የቆሰለ ነብር መቆጣጠር እስከማይቻል ድረስ ሊሄድ ይችላል ብሎ ማስብ አይከብድም። ቀደም ሲል ተፈጥረው የነበሩትን ችግሮች ከጉዳት በኋላም ቢሆን መንግስትና ህዝቡ መቆጣጠርና ማቋቋም እየቻለ መሆኑ ይበል የሚያሰኝ እየሆነ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ እንዲህ አይነት ችግር የማይታይባቸው ክልሎች ስላሉን  በጣም እንኮራለን፤ ከፍ ያለ ምስጋናም  ይገባቸዋል።

ቤንሻንጉል ጉምዝ  ክልል  ያለው ጉዳይ ግን ከዚህ ትምህርት የተወሰደበት አይመስልም። በመሆኑም በአማራ ብሄር ተወላጆች ላይ በክልሉ ውስጥ በተደጋጋሚ ጥቃት እየተፈፀመ እስካሁንም ቀጥሏል። ተቆርቋሪ የክልሉ መሪዎችና ሰፊው የቤንሻንጉል ጉምዝ ህዝብ በዚህ ጥቃት እጅግ ያዝናል እንጂ ደሰተኛ አይሆንም፡፡ ነገር ግን ለዚህ ጥፋት ሽፍቶችን የሚያሰማሩ፣ ይህን እያዩ ችላ የሚሉና የሚደግፉ ጥቂት አመራሮችና የፀጥታ አባላት የአማራ ህዝብ ጠላቶች ብቻ ሳይሆኑ የመላ የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላቶችም ናቸው። ክልሉ  ይህንን ቀድሞ የመቆጣጠር አቅም አልነበረውም ብሎ ማመን ግን  አይቻልም። ከጥቂት ወንበዴዎች ይልቅ  የክልሉ መንግስት በብዙ እጥፍ ይበልጣልና። ከአቅም በላይ ሆኖ ቢገኝ እንኳን መከላከያ ቀድሞ እንዲገባ ማድረግም ይቻል ነበር። ታዲያ ይህ ሁሉ ለምን አልተደረገም? የሚል ጥያቄ መልስ ይፈልጋል።

የአማራ ህዝብ ከጎረቤቱና አብሮ ከሚኖረው ወገኑ  ቤንሻንጉል ጉምዝ  ህዝብ ጋር ደም መቃባት  ፈልጎ አያውቅም፤ ወደፊትም አይፈልግም። ሽፍቶቹና ሀላፊነት የጎደላቸው ጥቂት አመራሮችና የጸጥታ ሀይል አባላት ግን ሊያጋጩት በመፈለግ ይህን እያረጉ ነው። እንግድህ  የአማራ ህዝብ ይህንን ሁሉ እያስተናገደ ትግስቱን አሳይቷል ብለን መደምደም እንችላለን። የነዚህ የሽፍቶች፣ጥቂት ሴረኛ መሪዎችና የፀጥታ አባላት፣እነድሁም ስምሪት ሰጪዎቹ ሴራ በህዝቡ፣ በጤነኛ የክልሉ አመራሮች ፣የፀጥታ ሀይሎች እንድሁም በመከላከያ ሀኃይላችን የተባበረ ስራ   ይከሽፋል እንጂ የጥፋት ሀይሎቹ አላማ  አሸናፊ እንደማይሆን ይታመናል። ነገር ግን እነዚህ ኃላፊነት የጎደላቸው የጥፋት ሀይሎች ከተጠያቂነት በፍፁም አያመልጡም፣ ሊያመልጡም አይገባም። መንግስት ይህንን እንደሚያረጋግጥ ይጠበቃል።

የአገራችን ህገ መንግስት አንቀፅ 38 ከንኡስ አንቀፅ 1 እስከ 4 እንደተደነገገው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በየትኛውም ክልል  የመኖር፣ የመደራጀት፣ የመምረጥ፣ የመመረጥና በየአስተዳደር እርከኑ የመወከልን መብት ሰጥቷል። የአማራ ክልላዊ መንግስት ይህንን መብት በደንብ ተግባራዊ አድርጎታል። በክልሉ የሚገኙ ብሔረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ ነው። የአማራ ህዝብም ለዚህ ሙሉ እውቅና የሰጠ ኩሩ ህዝብ ነው።

የአማራ ህዝብ በክልሉ ማነህ? ምንድነህ? ከየት መጣህ? ለምን መጣህ? የሚል ጥያቄ አንስቶ አያውቅም። ተቀላቅለው ሲያስተዳድሩትም ቢሆን  በስራቸው ነው የሚመዝናቸው እንጂ በማንነታቸው ፈፅሞ አያውቃቸውም፣ በዚህ  ሊያውቃቸውም አይፈልግም። በተለያዩ አንዳንድ ክልሎች የሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች ግን ይህን ህገመንግስታዊ መብታቸውን የሚያስከብርላቸው የክልል አስተዳደር እያጡ ሰባአዊና ዴሞክራሳዊ መብቶቻቸው እየተጣሰ ጥቃት   እያስተናገዱ ቀጠለዋል። እናም እንግዲህ  ትክክለኛው አቃፊ ለሆነው የአማራ  ህዝብ ውለታ ምላሹ ይህ ከሆነ ፍርዱ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ይሆናል። አሁንም ጥቃቱ እንዳይቀጥል  በሽፍቶቹ ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ፣ በጥቃቱ ላይ እጃቸውን ያስገቡ አመራሮችና የፀጥታ ኃይል አባላት ሁሉ የእጃቸውን ማግኘት ይኖርባቸዋል። በዚህ ረገድ ክልሉ የጀመረው የማጣራትና ተጠያቂ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።

ከዚህ በላይ ግን የኔ ዋናው ሀሳብ  ዘላቂ መፍትሄ መፈለጉ ላይ ያተኮረ ነው። ይህም የህገመንግስቱን ድንጋጌ ተግባራዊ ማድረግ ላይ ይሆናል የሚል ነው። እናም የየትኛውም ብሄር ተወላጅ በየትኛውም ከልል መብቱን መጠበቅና ማስጠበቅ የግድ መሆን አለበት። ስለሆነም የአማራ ክልላዊ መንግስት የብሄረሰቦችን የመደራጀት፣ የመመረጥንና ውክልናን  የማረጋገጥ መብት በአማራ ክልል ተግባራዊ እንዳደረገ ሁሉ ሌሎች ክልሎች ላይም እንዲሁ መደረግ ያለበት ሲሆን በሌሎች  ክልሎች የሚኖሩ የአማራ ብሀሔር ተወላጆችና የሌሎችም የተለያዩ ብሔር ተወላጆች ሁሉ በያሉበት የክልል መንግስታት የመደራጀት፣ የመመረጥና በየአስተዳደር እርከኑ የመወከል ህገመንግስታዊ መብታቸው ተግባራዊ እንድሆን  ይፈቀድ ነው ሀሳቤ።

ለዚህ የፍትህ ጥያቄ በዋናነት መሪው ፓርቲና መንግስት  የአንበሳውን ድርሻ ይይዛሉ። እንዲሁም ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎችና ህዝቡ ይህንን ጥሪ እንዲደግፉ ይኸው የግሌን ድምፅ  አሰምቻለሁ። በመጨረሻም ሁሉም ፈተናዎች ታልፈው ከመናቆር ወጥተን በመከባበር፣ በፍቅር፣ በመተቃቀፍ  ወደ ልማትና የሰላም ጊዜ ውስጥ እንገባለንና ሁላችንም ለዚህ እንስራ።

     

ጥቃትይቁም! 

መሠረት ጀማነህ (የፓርላማ አባል)                                                                                                                      

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top