Connect with us

የኢዜማ ዋና ጽሕፈት ቤት የሚገኘው ትልቁ የስብሰባ አዳራሽ «መስፍን ወልደማሪያም የስብሰባ አዳራሽ» ተብሎ ተሰየመ

የኢዜማ ዋና ጽሕፈት ቤት የሚገኘው ትልቁ የስብሰባ አዳራሽ «መስፍን ወልደማሪያም የስብሰባ አዳራሽ» ተብሎ ተሰየመ
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)

ዜና

የኢዜማ ዋና ጽሕፈት ቤት የሚገኘው ትልቁ የስብሰባ አዳራሽ «መስፍን ወልደማሪያም የስብሰባ አዳራሽ» ተብሎ ተሰየመ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አመራር እና አባላት የእውቁ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እና የአደባባይ ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ከዚህ ዓለም በሞት የመለየት ዜናን ስንሰማ ከፍተኛ የልብ ስብራት ፈጥሮብናል። ፕሮፌሰር መስፍን ኢትዮጵያ ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ የአደባባይ ምሁር ነበሩ። አገዛዞችን ሳይፈሩ ያመኑበትን በድፍረት በመናገር፣ የተበደሉ ሰዎች ድምፅ በመሆን እና ሁልጊዜም ከጭቁኖች ጎን በመቆም ለዜጎች አርዓያ የሆነ ሕይወት አሳልፈዋል።

ፕሮፌሰር መስፍን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባኤ (ኢሰመጉን) በማቋቋም ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው አገልግለዋል። ካርታ ሥራና ጂኦግራፊ ኢንስቲትዩትም ካገለገሉባቸው ተቋማት መኻከል የሚጠቀስ ነው። ከፖለቲከኛነታቸው፣ ከመምህርነታቸው እና ከሰብዓዊ መብት ተሟጋችነታቸው በተጨማሪ በጸሐፊነታቸው ይታወቃሉ። በተለያዩ ጆርናሎች ላይ ከታተሙት ብዛት ካላቸው የምርምር ሥራዎቻቸው በተጨማሪ በርካታ መጣጥፎችና መጻሐፍትን ለንባብ አብቅተዋል። ባሳለፍነው ዓመት መጠናቀቂያም «ዛሬም እንደ ትናንት?» የሚል የመጨረሻ የጽሑፍ ሥራቸውን ለንባብ አብቅተዋል።

ፕሮፌሰር መስፍን የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በተፈሪ መኮንን እና ጄኔራል ዊንጌት የተከታተሉ ሲሆን የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በቀድሞ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተከታትለዋል፡፡ ወደ ሕንድ ሀገር በማቅናት ፑንጃብ ዩኒቨርስቲ በፍልስፍና ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪ ያገኙ ሲሆን በሀገረ አሜሪካ ማሳቹሴትስ ከተማ የሚገኘው ክለርክ ዩኒቨርሲቲ በጂኦግራፊ የሁለተኛ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለረጅም ዓመታት በመምህርነት ያገለገሉ ሲሆን በማስተማር እና በተለያዩ ጆርናሎች ላይ በወጡ የምርምር ውጤታቸው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ አግኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ዜና እረፍት ከተሰማ በኋላ አስቸኳይ ስበሰባ አድርጎ በፓርቲው ዋና ጽሕፈት ቤት የሚገኘውን ትልቁን የስብሰባ አዳራሽ «መስፍን ወልደማሪያም የስብሰባ አዳራሽ» ተብሎ እንዲጠራ ውሳኔ አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አመራር እና አባላት በሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ፣ መምህሩ፣ ጸሐፊው እና የአደባባይ ምሁሩ መስፍን ወልደማርያም (ፕሮፌሰር) ሕልፈት የተሰማንን ጥልቅ ሐዘን እየገለጽን ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ልባዊ መጽናናትን እንመኛለን።

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top