Connect with us

የአዳማው ደመራ መከልከልና አቀባበሉ ገራሚ ፓራዶክስ ነው

የአዳማው ደመራ መከልከልና አቀባበሉ ገራሚ ፓራዶክስ ነው
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

የአዳማው ደመራ መከልከልና አቀባበሉ ገራሚ ፓራዶክስ ነው

የልጅቷን ማሸነፍ የሙዚቃ ዳኞች ይጨነቁበት፤ የካህናቱን ዘፋኝ መቀበል የእምነት ሰዎች ይገምግሙት፤ ኮሮና ምክንያት ሆኖ ያነጋገረባት አዳማ በደመራው ማግስት ግን?
****
ከስናፍቅሽ አዲስ፤
ፋና ላምሮት የሙዚቃ ዳኛ ገበና የታየበት የመሰላቸው ብዙ ናቸው፡፡ እኔ ግን ያየሁት የከንቲባ ገመና የፍትህ መዛባትና የእውነት መጨፍለቅ ነው፡፡ አዳማ በደመራው ማግስት የደመራ ዋዜማ ትሆን የነበረውን የአደባባይ እውነት እረስታ ራሷን አጋለጠች፡፡

የፋና ላምሮት ኩነት መጨረሻው አነታራኪ ሆነ፤ የሙዚቃን ክህሎት ውድድር በዚህ ደረጃ ጫፍና ጫፍ እንቆምበታለን ብዬ አላሰብኩም ነበር፡፡ በዳኝነት አሰጣጡ በፍጻሜው ነጥብ በአሸናፊው ጉዳይ ብዙ ንትርኮች ሰምተናል፡፡ እንዲህ ያለውን አጀንዳ እወጣዋለሁ ለሚለው ስለምሰጠው ብዙም አሳስቦኝ አልገባበትም፡፡ ልጅቷን ስላሸነፈች ያው የጾታ ውግንና ነውና እኔም ደስ ብሎኛል፡፡

ከደመራው በፊት የአዳማ አመራር በጋር ደመራ አናበራም፤ ቁጥሩ ምንም ያህል ቢሆን ለከተማዋ ህዝብ ደህንነት ሲባል የማይፈቀድ ነው ብሎ ሀገር ተነጋግሮበት ነበር፡፡ መጀመሪያውኑ ውሳኔ የቤተ እምነት አባቶችን ምክክር ውስጥ ያላስገባ አብረው ያልመከሩበትና ባለ ስልጣን ነን ከሚሉ ጉልበተኞች የመጣ ቀጭን ትዕዛዝ ነበር፡፡

ምክንያቱ ኮሮና ነው የተባለበት የአዳማው የህብረት ደመራ ሥርዓት መታገድ ምስጢሩ የተጋለጠው በማግስቱ ነበር፡፡ የአዳማዋ ሙዚቀኛ የፋና ላምሮት ውድድር አሸናፊ ሆና አዳማ ስትገባ የተደረገላት አቀባበል ደመራው ለምን እንደቀረ በአደባባይ አጋለጠ፡፡

በአቀባበሉ ላይ የተገኙት ካህናት ጉዳይ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች አስተያየታቸውን ይስጡበት፡፡ አቀባበሉ በራሱ ችግር ነበረበት የሚል እምነትም የለኝም፡፡ ሲቀበሏት የተሰጣት የገንዘብ ስጦታም መልካም ነው፤ የኔ ጥያቄ ኮሮና ፈርታ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ያገደችው ከተማ ክትባቱን አግኝታ ነው ወይ እንደዛ የሆነችው? የሚለው ነው፡፡

አሸናፊዋን ድምጻዊት ለመቀበል የወጣው ህዝብ ሆታውና ግርግሩ ሊያውም ማስክ አልባ በሆነ ሁኔታ ሲታይ ከደመራው ማግስት የሆነው ከደመራው በፊት የተወሰነው ውሳኔ እውነተኛነትና ለህዝብ አሳቢነት መነሻ መሆኑ ያጠራጥራል፡፡ ሃይማኖታዊ ሥርዓትን በኮሮና ሰበብ ያፈነው አመራርም ሁሉን ረስቶ አደባባይ ሆ ሲባል ስፖንሰር አድራጊና ኩነት አድማቂ ሆኗል፡፡ ውጤቱ በደመራው ማግስት የቀድሞው ውሳኔ ምን እንደሆነ አሳይቶናል፡፡

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top