Connect with us

ከገንዘብ ኖት ቅያሪው ባሻገር

ከገንዘብ ኖት ቅያሪው ባሻገር
Photo: Ethiopian Reporter

ኢኮኖሚ

ከገንዘብ ኖት ቅያሪው ባሻገር

ከገንዘብ ኖት ቅያሪው ባሻገር
(ክቡር ገና)

የኢትዮጵያ መንግሥት በኢትዮጵያ ከሃያ ዓመታት በላይ ግልጋሎት ሲሰጥ የነበረውን የመገበያያ ገንዘብ (ብር) ለውጥ የማድረግ ሂደት ውስጥ ይገኛል፡፡ መንግሥት ለዚህ የብር ኖት ለውጥ የተለያዩ ምክንያቶችን ያስቀመጠ ሲሆን፣ በገበያ ውስጥ አለ የሚባለውን በሕገ-ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀስ ገንዘብ ማምከን ይገኝበታል፡፡

በበኩሌ የብር ኖት ለውጥ ማድረግ ብቻውን መንግሥት ያሰበውን ያህል ለውጥ ያመጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ምክንያቱም በሌሎች አገሮች ተሞክሮዎችም እንዳየነው ሕገ-ወጥ የተባለው ገንዘብ ባንክ ቤት ገብቶ ተመልሶ ሲመጣ ተመልክተናል፡፡ በሕገ-ወጥ መንገድ ገንዘብ አከማችቶ የያዘ ግለሰብ የተለያዩ አማራጮችን በንቃት የሚመለከት እና ማምለጫ ቀዳዳዎችንም ቀድሞ አዘጋጅቶ የሚቀመጥ ነው፡፡ ስለሆነም በሕገ-ወጥ መልኩ አከማችቶ ያስቀመጠውን ገንዘብ ወደ ሕጋዊ ሥርዓት የሚያስገባበት ሁኔታዎች ይፈጥራል እንጅ በቀላሉ የሚገኝ ወይም የሚያዝ አይሆንም፡፡

በሕገ-ወጥ መልኩ ገንዘብ ያከማቹ አካላትን ለመቆጣጠር መንግሥት የብር ኖት ለውጥ ከማድረግ የተሻሉ አማራጮች እንደነበሩት ይሰማኛል፡፡ ለምሳሌ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ግለሰቦች ሀብታቸውን እንዲያሳውቁ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ከአንድ ሰሞን የሚዲያ እና የፖለቲካ ፍጆታነት ባሻገር በቋሚነት ሥርዓት ባለው መልኩ አጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ እና የሚጠረጠሩ አካላት ካሉም ጠበቅ ያለ ምርመራ እንዲያደርግባቸው ማድረግ ግለሰቦች ምንጩ ያልታወቀ ገንዘብ ሲያገኙ መደረግ ያለባቸው ሕጋዊ ምርመራዎችን ማጠናከር ቢቻል ገንዘቡን ሰዎች በስጋት ወደ ባንክ የሚያመጡበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን መሰል ሥራዎች ካልተከናወኑ የገንዘብ ኖት ለውጥ ማድረጉ ብቻ ፋይዳ ይኖረዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ በገለልተኛነትና በዕውቀት ከተመራ ፀረ ሙስና ኮሚሽን በዚህ ረገድ ብዙ አገር የሚጠቅም ሥራ ማከናወን ይችላል፡፡ እስካሁን ብዙም አመርቂ ሥራ አልሠራም፡፡

በእኔ እይታ የገንዘብ ኖት ለውጡ ብዙ ችግር ያመጣል የሚል ግምት የለኝም፡፡ ለውጡ ያለ ምንም እንከን ይካሄዳል ብዬም አስባለሁ፡፡ ነገር ግን ቀድመው መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች ካልተወሰዱ እና የተቋማት አቅም ካልተጠናከረ የሚፈለገውን ዓላማ ለመምታት ይቻላል የሚል እምነት የለኝም፡፡

ከሁሉ አስቀድሞ ግን በኢመደበኛ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚሳተፉ የከተማ ነዋሪዎችን ወደ ሕጋዊነት ለመመለስ የተለያዩ አማራጭ መፍትሔዎችን መውሰድ ይገባል፡፡ በኢመደበኛው የንግድ ሥርዓት ውስጥ የሚገኘው የንግድ ማኅበረሰብ ወደ ሕጋዊ መስመር ሳይገባ የጥሬ ገንዘብ ኖት ለውጥ ቢደረግም እንኳን የተቀየረው ጥሬ ገንዘብ ዳግም ከባንክ ውጪ እንደማይሆን እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ከባንክ ውጪ የሆነ ጥሬ ገንዘብ የሚሽከረከረው በእንዲህ ዓይነት ገበያ ውስጥ ነው፡፡

እዚህ ጋር ለአብነት የሲንጋፖርን ልምድ መጥቀሱ አግባብነት ይኖረዋል፡፡ የሲንጋፖር መንግሥት እየሰፋ የመጣውን ኢመደበኛ የንግድ እንቅስቃሴ ለማስቆም በንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚሰጡት ደረሰኞች ዕጣ እንዲኖራቸው አደረገ፡፡ በዚህ ምክንያት እቃ የሚገዛው አካል በዕጣው ተሳታፊ ለመሆን ሲል ለሚገዛው እቃ ደረሰኝ የሚጠይቅ ሆነ፡፡ ይህን መንገድ በመጠቀም በሲንጋፖር ሕገ-ወጥ የሆነውን አካል ወደ ሕጋዊ ሥርዓት ማምጣት ተችሏል፡፡

አሁን ትልቁ ጉዳይ መሆን ያለበት በገበያ ውስጥ ያለው ገንዘብ ወደ ባንክ ገባ ወይስ አልገባም? የሚለው አይደለም፡፡ ከዚህ በኋላ የገንዘብ ዝውውሩ ምን መምሰል አለበት? የሚለው ነው ሊያስጨንቀን እና ልንነጋገርበት የሚገባው ጉዳይ፡፡ ጥያቄ መሆን ያለበትም የኢመደበኛው የንግድ እንቅስቃሴ ለምንድን ነው ወደ መደበኛው መግባት ያልቻለው? የሚለው ነው፡፡ አሁን በዓለም ሁኔታም የኢመደበኛው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መጨመር እንጅ መቀነስ እያሳየ አይደለም፡፡

ሌላው መነሳት ያለበት፣ አሁን የመንግሥት ሐሳብ በሕገ-ወጥ መልኩ የተቀመጠውን ገንዘብ ማምከን ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ገንዘብ ሲመክንስ በኢኮኖሚው ላይ ምን ሊፈጠር ይችላል? የሚለው ጉዳይ በአግባቡ የታሰበበት አይመስለኝም፡፡ ተከማቸ የተባለው ገንዘብ መከነ ማለት ሲንቀሳቀስ የነበረ ገንዘብ እንቅስቃሴውን አቆመ ማለት ነው፡፡ ያ ማለት በገበያ ውስጥ ያለው ገንዘብ አነስተኛ ይሆናል፡፡ ይህ በቀጣይ የራሱ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ጫና መፍጠሩ አይቀርም፡፡ በገበያው ውስጥ ያለው የገንዘብ መጠን በመቀነሱ ምክንያት የዋጋ ንረት፣ እንዲሁም በአነስተኛ ካፒታል በሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ህልውናም አደጋ ውስጥ የሚገባበት ዕድል ይፈጠራል፡፡ ይህን ችግር በምን መልኩ ለመፍታት እንደታሰበ የተቀመጠ አቅጣጫ ከመንግሥት አካል ሲነገር አንሰማም፡፡

መንግሥት የገንዘብ ኖት ለውጥ ለማድረጉ የሰጠው ሌላኛው ምክንያት የዋጋ ንረትን ለማስተካከል የሚል ነው፡፡ በእኔ እምነት ግን በገንዘብ ምክንያት ለሚፈጠረው የዋጋ ንረት የመጀመሪያው ተጠያቂ መንግሥት ነው፡፡ ይህን የምልበትም ምክንያቶች አሉኝ፡፡ መንግሥት ባለፉት ዓመታት ሲገጥመው ለቆየው የበጀት ጉድለት ገንዘብ እያተመ ወደ ገበያው ሲረጭ እንደከረመ በግልጽ ይታወቃል፡፡ በቅርቡ እንኳን ባንኮች ለገጠማቸው የጥሬ ገንዘብ እጥረት መንግሥት 30 ቢሊዮን ብር አትሞ ለባንኮቹ አበድሯል፡፡

ይህ ጥሬ ገንዘብ ተሠርቶ የመጣ አይደለም፤ ታትሞ የመጣ ጥሬ ገንዘብ ነው፡፡ አሁን ያለው ችግር መንግሥት ጥሬ ገንዘብ አትሞ ወደ ገበያው ሲያስገባ ሕጋዊ፤ ግለሰብ ሲያስገባው ደግሞ ሕገ-ወጥ እየሆነ ነው፡፡ መንግሥት የብር ኖት ለውጥ አድርጎም ይህን አካሄዱን ካልቀየረ ችግሩ ይፈታል የሚል እምነት የለኝም፡፡

መንግሥት የፋይናንስ ዘርፉን ወደ ዲጂታል ሥርዓት ለመቀየር ሙከራዎችን እያደረገ ነው፡፡ ይህ እንቅስቃሴ በጎ ቢሆንም፣ አብረው መሠራት ያለባቸው ሥራዎች ግን አብረው እየተሠሩ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመፍጠር የኤሌክትሪክ ተደራሽት መኖር መቻል አለበት፡፡ የቴሌኮም አገልግሎት ጠንካራ እና ርካሽ መሆን መቻል አለበት፡፡ የሕዝብ ተቀባይነት እንዲኖረው ማድረግም ያስፈልጋል፡፡ ይሁን እንጅ በአገራችን እስከዚህ ዓመት ድረስ የፋይናንስ ዘርፉን እዚህ ቦታ ላይ አደርሰዋለሁ በሚል የወጡ ዕቅዶችን አናይም፡፡ በጥቅሉ ተያያዥነት ያላቸው በርካታ ሥራዎች አብረው እየተመጋገቡ እስካልሄዱ ድረስ አንዱ እርምጃ ብቻውን አመርቂ ለውጥ ሊያመጣ አይችልም፡፡ የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት የግድ አስፈላጊና መሠረታዊ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን ለማሟላት ጠንካራ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡(ሲራራ ጋዜጣ)

Click to comment

More in ኢኮኖሚ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top