መተከል-የግብጽ ሌላኛዋ ካርታ፤
የግብጽ ቅጥረኞች የሴራ እርስት፤
****
ከስናፍቅሽ አዲስ በድሬቲዩብ
በመተከል የሆነውን ሁሉ አየነው፡፡ ብዙ ሰዎች የመተከልን ጅምላ እልቂትና ጭፍጨፋ እንዲሁም የንጹሃንን ሞት ተራ የወንጀል ድርጊት አድርገው ቆጥረውታል፡፡ መንግስትም ምናልባት ከዚህ የዘለለ ዕይታ ላይኖረው ይችላል፡፡ መተከል ግን የሌላውና ቀጣዮ የእልቂት ድራማ መድረክ ሆና ተመርጣለች፡፡
ዛሬም እንደ ትናንትናው በህዳሴው ግድብ ሳቢያ የመከራ ቀንበር ጫንቃው ላይ የተጫነው አማራ ህዝብ ኢትዮጵያ ለማድቀቅ መድቀቅ ያለበት ተብሎ ስቃዮን እንደሚበላ ማሳያው መተከል ነው፡፡
መተከል ቀድሞ ጎጃም ግዛትና ርስት ነበር፡፡ ይሄ አባባል የዘር ፖለቲካ ያሰከራቸው ጎጃም ምድሩ እንጂ ሰው ስለማይመስላቸው መተከል የጎጃም ነው ሲባል ጉምዝ ሀገር አልባ ነው የተባለ ይመስላቸዋል፡፡ ጉምዝ የጎጃም አንዱ ነባር ህዝብ ነው፡፡
መተከልን ከጎጃም የመነጠሉ ሴራ ቀዳሚው አላማ ጠንካራውንና ሰፊውን የአፍቃሪ ኢትዮጵያ ግዛት ቦጫጭቆ ለማሳነስና አልፎም አማራው በክልል ደረጃ እንደ መተከል ያሉ ግዛቶችን ይዞ ቢዋቀር በሀብት ይበለጽጋል ከሚል ተንኮል የተጸነሰና የተወለደ ፌዴራሊዝም ነው፡፡
ባለፉት መቶ አመታት ቀኝ የመቀራመት ምኞት የነበረው ገዢ ሁሉ የምኞቴ ሳንካ አማራው ነው ብሎ በአማራው ሲያልፍም በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ላይ ቂምና ጥላቻ ጥፋትና ሴራ ሲፈጽም ኖሯል፡፡ ግብጻውያን ምክንያት ከዚሁ ከሀገር ልጅ በሴራ ይሰጣቸው ወይም ራሳቸው ያስቡት ባይታወቅም ግድቡን ከአማራው ጋር በማገናኘት አማራውን አድቅቆ ግድቡን ማሰናከል የሚለውን ሙከራ ደጋግመውታል፡፡
በመተከል ዞን የሚገኘው ጉባ ወረዳን ለህልመኛ የግዛት ተስፋፊ ፖለቲከኞች ስጦታ በመስጠት እነሱን ደግፎ ግድቡን በማጨናገፍ አማራን ከነባር ርስቱ አስወግዶ ኢትዮጵያን የማፍረሱ ሴራ ውጤት የንጹሃን ሞት ቀዳሚው ምክንያት ነው፡፡
በመተከል ዞን የተደራጀ የታጠቀ በገንዘብ የሚደገፍና ግቡ ንጹሃንን አስጨንቆ ነጻ የሽብር ቀጠና ግዛት ባለቤት መሆን የሆነ ሃይል አለ፡፡ ይህ ሃይል ቃል ተገብቶለታል፡፡ በገንዘብ ሲደገፍ ከኢትዮጵያ የምትነጠል አማራ የኔ የማይላት ታላቁን የአባይ እጣ ፈንታ ይዛ ራስ ገዝ የምትሆን የጥፋት ቀጠና መፍጠር ነው፡፡ ብዙ ምልክቶች ግዙፍ ስዕል ይሰጡናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ግድብና የሀገር ፍቅር የሚል ቀድሞ ምድሩና ርስቱ በመሆኑ ከወንድሙ ከጉምዝ ጋር በሰላም የሚኖረውን ንጹህ ህዝብ መግደል፣ ማረድ፣ ማሳደድና ማጥፋት ነው፡፡
አማራን ከመተከል ምድር ማጥፋት ያስፈለገው ግዛት ማስፋፋት ለፈለገ አክራሪ ብሔርተኛ ተጨማሪ ርስት በመለገስ በምላሹ ለውለታው ታላቅ የውሃ ፖለቲካ ሴራን በድል መወጣት ነው፡፡ በዚህ ቁማር ውስጥ ጥቂት ጉምዞች ቢሳተፉም ውጤቱ ለጉምዝ ምንምና መጨረሻው ግዛቱን መነጠቅ ዛሬ በአማራው የሆነው በእሱ እንዲደገም ማድረግ ነው፡፡ እርግጥ ነው እዚያ አይደርስም፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ጠንካራ ስራዎችን መስራት ይጠበቅበታል፡፡ ሀገር የማፍረሱ ቅዠት አሁን ጓዙን ጠቅሎ መተከል ገብቷል፡፡ ሙከራዎች ሁሉ በግድቡ ዙሪያ በሚገኙ ወረዳዎች ተደጋግመዋል፡፡ ይህንን ፈጥኖ ማስቆም የመንግስት ድርሻ ነው፡፡ ይህ መንግስትን የመጣል ሌላው የሙከራ ሜዳም ነውና፤