አብርሃም ሊንከልን
(ኘሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም)
መስከረም 2013
ዛሬ ዓቢይ አህመድ ከገጠመው ችግር ያላነሰ አብርሃም ሊነከልንን እአአ በ1860 ግድም አጋጥሞት ነበር፤ የደቡቡ የአሜሪካ ክፍል የባርነት ሥርዓትን የሚደግፍ፣ የሰሜኑ የአሜሪካ ክፍል የባርነት ሥርዓትን የሚቃወም ነበር፤ ሊንከልን ሁለቱን ወገኖች ለማስማማት ሞከረ፤ ጦርነትን አልፈለገም፤ ግን አገሩም አንዲገነጠል አልፈለገም፤ መሠረቱ የተከፋፈለ ቤት አይቆምም፤ ስለዚህም ጦርነትን አልፈራም፤ ዛሬ በዓለም ሁሉ ገናና፣ ኃይለኛና ሀብታም አገርን ፈጠረ፡፡
ከሀጫሎ ሞት አስቀድሞ የሚታገዱ አፍራሽ ኃይሎች መረን ባይለቀቁ ሀጫሎም አይሞትም፤ የተከተለው ጥፋት ሁሉ ምንልባትም አይፈጸምም ነበር፤ የወያኔን ሹማምንት በጊዜ ዳር ማስያዝ ቢቻል ኖሮ የዛሬው ራስ ምታት አይደልቀንም ነበር፡፡
አውቃለሁ በቢሆን-ኖሮ አስተሳሰብ ታሪክ አይጻፍም! ከስሕተት ለመማር ግን ይረዳል፡፡
ትውልዶች
መስፍን ወልደ ማርያም
መስከረም 2013
አንድ ትውልድ ይወለዳል፤ በጊዜው እንደጊዜው ያድጋል፤ ያልፋል፤ በሌላ ትውልድ ይተካል፤ አዲሱም ትውልድ የተረከበውን ቅርስ ይዞ ይነሣና በራሱ ጥረት አዳዲስ ሥራዎችን ሠርቶ ይጨምርበትና ያድጋል፤ አዲስ ነገርን ትቶ ያልፋል፤ የቀደመው ትውልድ ተፈጥሮና ኑሮው ከሚያስገድደው በላይ ለሚቀጥለው ትውልድ መስዋእት መሆን አይችልም፤ አይጠበቅበትምም፤
በምጽዋትና በሞግዚት አስተዳደር የሚኖር ትውልድ ሊሚቀጥለው ትውልድ የሚያስተላልፈው ዕዳ ብቻ ነው፤ ዕዳን በውርስ ተሸክሞ የሚፈጠር ትውልድ ያለምርኩዝ መንቀሳቀስ አይችልም፤ ምርኩዝ ሊሆኑት የሚችሉት እነዚያው የዕዳው ባለቤቶች ናቸው፤ ስለዚህም ከዕዳና ከምጽዋት አዙሪት አይወጣም፤
ይህንን በትክክል መረዳት የፈለገ የኪዩባን የሸንኮራ አገዳ ታሪክና የአሜሪካንን ኩባንያዎች ታሪክ ያጥና፤ ለካስትሮና ጓደኞቹ መሸፈት ምክንያቱን ታገኛላችሁ፤ የኪዩባ መሬት የአሜሪካኖች የሸንኮራ አገዳ ማምረቻ ሆነ፤ ኪዩባውያን የሸንኮራ አገዳ ቆራጮች ሆኑ፤ የኪዩባ ከተሞች የኪዩባ ሴቶች የአሜሪካኖች መዝናኛዎች የእረፍት ቀን ማሳለፊያዎች ሆኑ፤
እኛ አልፈናል፤ ሴቶቻችንን ባሉበት እንልክላቸዋለን!ስንጋደል የሚከለክለን ወይም የሚገላግለን የለም!ቤቶቻችን ሲፈርሱና የሰው ልጅ በየመንገዱ በፕላስቲክ እየተጠለለ ሲኖር አቤት የሚባልበት የለም!ልጃገረዶች ታፍነው ተወስደው ወላጆች ሲጨነቁ አለሁላችሁ የሚል የለም! ጥቂት ወሮ-በሎች መቀሌ መሽገው የትግራይን ሕዘብ መያዣ አድርገው ሲያሰቃዩ አለሁላችሁ የሚላቸው የለም!