ባንዲራ ለማውረድ የሚሰሩ አክቲቪስቶች
ባለፉት ጥቂት አመታት በጥቂት አክቲቪስቶች ነን በሚሉ የማህበራዊ ሚዲያ ዘዋሪዎች በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ የከፈቱት ስምና ዝና የማጠልሸት እንዲሁም ከግለሰብ አናት ላይ ያልወረደ ዘመቻ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከመሻሻል ይልቅ እየዘቀጠ ሀገርና ህዝብ ከማዳን ይልቅ ማዋረድን እና ድርጅት ማፍረስን ተያይዘውታል።
ሰሞኑን ደግሞ የአየር መንገዱን ባንዲራ ካላወረድን ብለው ያዙን ልቀቁን ፉከራ ጀምረዋል።
በአቪዬሽን ሀሁ መሰረት አንድ አውሮፕላን ተመርቶ ወደ ስራ ከመግባቱ በፊት አምራቹ ኩባንያ ከዲዛይን ጀምሮ እስከ አመራረት ሂደትና ከሽያጭ በኃላም በሥራ ላይ የሚከታተል የሚቆጣጠር እና ፍቃድ የሚሰጥና ተግባራዊነቱን የሚከታተል በየሀገሩ የተቋቋመ ህጋዊ አካል ይኖራል።
አሜሪካን ሀገር ለሚሰሩ አውሮፕላኖች ደግሞ FAA የተባለ ተቋም ይህንኑ ይፈጽማል። የደህንነት እና የአደጋ ስጋት እንዳይኖር የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና የእርምት ብሎም የማስተካከያ እርምጃዎች ይወስዳል ።ይህን ሲያደርግ አምራቹ ብቻ ሳይሆን ተጠቃሚ አየር መንገዶች እንዲያውቁት ያደርጋል።
ከነዚህም መልእክቶች አንዱ በሰሞኑ አክቲቪስቶች እጃችን ገባ ይሉናል ። ምኑ ብሎ አጥብቆ የሚጠይቅ ቢኖር ዱቂት የሆነ መልሳቸው ይነሰንሳሉ ። የአደባባዪን በጆሮአችን ያሰሙናል።
ጎማ በተነፈሰና ብሎን በተፈታ ቁጥር መግለጫ እንዲሰጣቸው የሚወተዉቱት አክቲቪስቶች አደጋ ደርሶ ነበር ይሉናል። እውነታው ግን ከፍ ብሎ የተሰቀለውን ባንዲራ የማውረድ ሴራ ነው።
የአሜሪካው ፌዴራል አቪዬሽን ባለስልጣን ለሁሉም ባለድርሻዎች በየጊዜው የሚልከውንና ሰሞኑን የላከውን AD /air worthiness directive /ወይም ለቦይንግ ሰራሽ አውርፕላኖች የበረራ ደህነት ሲባል የተሰጠውን መመሪያ እውነተኛ የመረጃውን ሊንክ ከታች አቅርቤያለሁ ። ማንም ወደ ድረ ገጹ በመግባት ለማረጋገጥ ይችላል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድም እንደ ማንኛውም አየር መንገድ የደረሰውን የአተገባበር መመርያ በድርጅቱ የውስጥ ማስታወቂያ ለሰራተኞቹ ይገልጻል ። እንደወትሮው ሁሉ በሰሞኑ ለአውሮፕለን ጥገና ባለሙያዎች የተለጠፈው የውስጥ ማስታወቂያ ሰራተኞች በስራ ላይ ሊወስዱ ስለሚገባቸው የጥንቃቄ እርምጃዎች ከመግለጽ ባለፈ አደጋ ስለመድረሱ አይገልጽም። አየር መንገዱም በበረራ ደህንነት የተመሰከረለት መሆኑ ይታወቃል ።
በአማርኛ የምትጽፉ ‘ግብጻውያን’ የሀገሬ ባንዲራ እናንተ ከማትደርሱበት ስፍራ ራቅ ብሎ የተሰቀለ መሆኑን አውቃችሁ አጉል አትንጠላጠሉ።
ድህረ ገጹን ማንበብ ለምትፈልጉ ይህንን ሊንክ ይጫኑ
አስራት በጋሻው
ከኤርፖርት ሲቲ
ቦሌ ቡልቡላ