Connect with us

በነገራችን ላይ…

በነገራችን ላይ...
Photo: Social media

ህግና ስርዓት

በነገራችን ላይ…

በነገራችን ላይ…
(ታምራት ኪዳነማርያም)

ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ፤ አሁን ከገንዘብ ዝውውሩ ጋር በተያያዘ ብቻ ሳይሆን በአዘቦት ቀንም የሚደረገው የቤት ሽያጭ ውል ማዋዋልና መመዝገብ አነጋጋሪ ነው። ክፍተቶች አሉት። ሻጭ ካርታውን በእጁ ይዞ ገዢም ገንዘቡን በቼክ ይዞ ወይም በባንክ አስቀምጦ ውል አዋዋዩ ባለስልጣን ፊት ይቀርባሉ። አዋዋዩ ባለሥልጣንም ከማዋዋሉ በፊት ሻጭን ገንዘቡን ተቀብለሃል ወይ ሲለው ሳይቀበል ተቀብያለሁ ይለዋል። ገዢውንም ካርታና ሰነዶችና ቤቶቹን ተረክበሀል ወይ ሲለው ሳይረከብ ተረክቢያለሁ ይለዋል።

ከዛ ሻጭና ገዢ ውሉን ተፈራርመው ጨርሰው እያንዳንዳቸው የውላቸውን አንዳንድ ኮፒ ይዘው ውጪ ከወጡ በኋላ ተያይዘው ባንክ ይሄዳሉ። ገዢው ገንዘቡን ለሻጩ በባንክ ሲያስተላልፍለት ሻጩ ደግሞ ለገዢው ካርታውን ይሰጠዋል።

እዚህ ላይ ገዢው ተንኮል ካሰበ ገንዘቡን በባንክ ከማስተላለፉ በፊት አንዴ ካርታውን ልየው ብሎ አታሎ ከሻጩ ላይ ካርታውን ተቀብሎ ገንዘቡን ሳያስተላልፍ ቢሰወር ምን ይሆናል የሚለው አስጊ ነው። ቤቱን ገዝቻለሁ ገንዘቡንም ከፍያለሁ ብሎ ቢከስ ወይም ሲከሰስ የሸፍጥ ክርክር ቢከራከር አሳሳቢ ነው። በእርግጥ አብዛኛው ሰው እንደዚህ አያደርግም።

በተመሳሳይ ሻጩም ገንዘቡን ከተቀበለ ወይም በባንክ ከተላከለት በኋላ ካርታውን ሳይሰጥና ቤቱን ሳያስረክብ ቢሰወርና ገዢውን ቢያጉላላስ የሚለውም አሳሳቢ ነው። የተዋዋዮችን ጥቅም ለመጠበቅ ሲባል ይሄ ክፍተት አንድ መፍትሄ ይፈልጋል።

በውጪ ሀገር ጠበቆች የአደራ ሂሳብ አላቸው። የአደራ ሂሳባቸው የደንበኞች ገንዘብ የሚቀመጥበት ነው። የአደራ ሂሳባቸውን የጠበቆች ማህበር ይቆጣጠረዋል። ባንኩ የጠበቆችን የአደራ ሂሳባቸውን የባንክ ስቴትመንት ለማህበሩ የማሳወቅ ግዴታ አለበት።

ጠበቃው ከደንበኞች የአደራ ሂሳብ ውስጥ ቀጥታ ወጪ አድርጎ ለራሱ መውሰድ አይችልም። እንደዛ አድርጎ ቢገኝ ፈቃዱ ይነጠቃል። መጀመሪያ ባንኩም ላይፈቅድለት ይችላል። ጠበቃው ከደንበኞቹ የአደራ ሂሳቡ ላይ የደከመበትን የራሱን የክፍያ ገንዘብ ወጪ ማድረግ የሚችለው በቼክ ነው።

የገንዘብ መጠየቂያ ኢንቮይስና ደረሰኝ የመሳሰሉትንም መቁረጥ እና ለደንበኛው ማሳወቅ ይኖርበታል። ከዚህ መንገድ ውጪ ከደንበኛው በቀጥታ ገንዘብ መቀበል የተከለከለ ነው። ስለዚህ አንድ ሰው ቤት መሸጥም ሆነ መግዛት ሲፈልግ በመጀመሪያ ጠበቃ ይይዛል። ጠበቃውም ብሮከር ደላላ ይገናኝና ለደንበኛው ቤት ገዢ ወይም ሻጭ ይፈልጉለታል።

መጨረሻ የሚስማማው ቤት ሲገኝ የሻጭና የገዢ ጠበቆች በተሰጣቸው ውክልና መሠረት ደረጃውን የጠበቀ ውል ይዋዋላሉ። ከዛ ገዢው የራሱ ጠበቃ አደራ ሂሳቡ ውስጥ በቂ የመግዣ ገንዘብ ያስገባለታል። በመቀጠል የገዢው ጠበቃ የመግዣውን ገንዘብ ለሻጩ ጠበቃ ያስተላልፍለታል። የሚያስተላልፍለት ወደ ግል ሂሳቡ ሳይሆን ወደ ደንበኞች አደራ ሂሳብ ውስጥ ነው።

የሻጩ ደንበኛ ገንዘቡ የደንበኞቹ የአደራ ሂሳብ ውስጥ ከተላለፈለት በኋላ የራሱንና የደላላውን ክፍያ አስቀርቶ ሌላውን ወደ ደንበኛው ሂሳብ ያስተላልፋል። ከዛም የደላላውን ክፍያ ወደ ደላላው ሂሳብ ያስገባል። የራሱንም በኢንቮይስና በቼክ ወጪ አድርጎ ወደ ግል ሂሳቡ ገቢ ያደርግና ደረሰኙን ለደንበኛው ይልካል።

የገዢም ጠበቃ በተመሳሳይ የቤቱን የሽያጭ ገንዘብ ከአደራ ሂሳቡ ወደ ሻጩ ጠበቃ የደንበኞች አደራ ሂሳብ አዘዋውሮ ከከፈለ በኋላ የራሱንና የደላላውን ክፍያ በተመሳሳይ አይነት ያዘዋውራል። ሰነዱንም ይለዋወጣሉ። ቤቱንም ይረካከባሉ።ምንም ዓይነት ስጋት የለውም። ገንዘቡን ይዞ ቢጠፋስ ወይም ካርታውን ይዞ ቢሸበለልስ ወይም ቤቱን አላስረክብም ቢልስ የሚባል ነገር የለም። ምናለ በኛስ ሀገር ተመሳሳይ አሠራር ቢጀመር? ለጠበቆችም ጥሩ ሥራ ይፈጠራል። ዋናው ነገር ግን ሰዎች ደህንነቱ የተጠበቀ ውል መዋዋል የሚችሉበት ሁኔታ ይፈጠራል ማለት ነው።

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top