አትሌት አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ ሮጦ ያሸነፈበትን የማራቶን ውድድር በማስመልከት ትናንት በሮም የመታሰቢያ ሩጫ ውድድር ተካሄዷል።
አትሌት አበበ ቢቂላ በ1952 ዓ.ም በጣልያን መዲና ሮም በተካሄደ 17 ኛው የኦሊምፒክ ማራቶን ውድድር በባዶ እግሩ በመሮጥ 2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከ16 ሴኮንድ በመግባት ታሪካዊ ድል ማስመዝገቡ የሚታወስ ነው።
አትሌቱ በውድድሩ ያገኘው የወርቅ ሜዳሊያ አፍሪካ በኦሊምፒክ ውድድር ታሪክ ያገኝቸው የመጀመሪያ መሆኑን ድሉን ይበልጥ ደማቅ እንዳረገውም የሚዘነ አይደለም።
የተመዘገበውን ድል አስመልክቶ የመታሰቢያ የሩጫ ውድድር ከስድሳ ዓመት በፊት አትሌት አበበ ቢቂላ በሮጠበት ተመሳሳይ ቀን፣ ቦታ እና ስዓት በሮም “ተርሜ ዲ ካራካላ” ስቴዲየም የድሉ መታሰቢያ የሩጫ ውድድር መካሄዱን በሮም ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ውድድሩ “ACSI Italia Atletica” የአትሌቲክስ ክለብና የአትሌቲክስ እና በሮም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ትብብር የተዘጋጀ ነው።
በመታሰቢያ ማራቶን ውድድሩ 106 ሯጮች የተሳተፉ ሲሆን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በአንድ ላይ ሯጮችን መልቀቅ ባለመቻሉ የመጀመሪያው ሯጭ 195 ሜትር እንዲሁም ሌሎች ቀሪ 105 ሯጮች እያንዳንዳቸው 400 ሜትር እንዲሸፍኑ ሆኗል።
በሮም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተቀዳሚ ጉዳይ ፈፃሚ/ ቻርጅ ዲ አፌር/ አቶ ሸጋው አባተ የመታሰቢያ በዓሉን በትብብር እና በድምቀት ለማዘጋጀት የተሳተፉ አካላትን አመስግነው ወደፊትም በትብብር እና በድምቀት ውድድሩ እንደሚካሄድ ቃል ገብተዋል።
አትሌት አበበ በቂላ በሮምና በቶኪዮ ኦሊምፒክ ካስመዘገባቸው የማራቶን ድሎች ውጪ በ1960 ዓ.ም በሜክሲኮ በተካሄደው 19ኛው የኦሊምፒክ ውድድር በማራቶን ተሳትፎ 17 ኪሎ ሜትር ከሮጠ በኋላ እግሩ ላይ በነበረበት ሕመም ምክንያት ውድድሩን ማቋረጡ አይዘነጋም። ውድድሩን ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ማሞ ወልዴ ማሸነፉም እንዲሁ።
በ1961 ዓ.ም አትሌት አበበ ከቶኪዮ ኦሊምፒክ መልስ ከአጼ ኃይለስላሴ በሽልማት ያገኘውን የቮልስ ዋገን መኪና አዲስ አበባ ውስጥ ሲያሽከረክር በደረሰበት አደጋ ከወገቡ በታች መንቀሳቀስ እንዳይችል አድርጎታል።
አትሌት አበበ በቂላ በ1961 ዓ.ም በ41 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
አትሌት አበበ ከወይዘሮ የውብዳር ወልደጊዮርጊስ ጋር በትዳር አራት ልጆችን አፍርቷል። #ኤዜአ