በመጪው ረቡዕ ጳጉሜ 4/2012 ዓ.ም ይካሄዳል የተባለውን የትግራይ ክልል ምርጫን ለመዘገብ ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ ዛሬ ረፋድ በመጓዝ ላይ የነበሩ የአገር ውስጥና የውጪ ጋዜጠኞች ከቦሌ የአውሮፕላን ማረፊያ እንዳይሄዱ መከልከላቸውን ለቢቢሲ ገለጹ።
በፌደራል መንግሥቱና በትግራይ ክልል መካከል ለወራት የውዝግብ ምንጭ ሆኖ የቆየው ክልላዊ የተናጠል ምርጫን በተመለከተ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባለፈው ቅዳሜ በካሄደው አስቸኳይ ስብሰባው ምርጫው ከአገሪቱ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን በመሆኑ ሕገ ወጥ ነው ብሎታል።
ምክር ቤቱ ከነገ ወዲያ የሚካሄደው የትግራይ ክልላዊ ምርጫ “እንዳልተደረገ የሚቆጠር፣ የማይጸናና ተፈጻሚነት የሌለው ነው” ሲል ነበር ተቀባይነት እንደማይኖረው ያሳወቀው።
ከምርጫው ጋር ለተያያዘ ሥራ በአውሮፕላን ሊጓዙ የነበሩት ጋዜጠኞች ቁጥራቸው ከ10 በላይ እንደሆነም የተነገረ ሲሆን፤ በበረራ መርሃ ግብራቸው መሰረት ወደ አውሮፕላን ከገቡ በኋላ ከአውሮፕላኑ እንዲወርዱ መደረጉ ተገልጿል።
ከጋዜጠኞቹ መካከል አንዱ የሆነው ለብሉምበርግና ለአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ የሚሰራው ሳይመን ማርክስ “የተወሰንን ሰዎችን መታወቂያ ካርድ ከተመለከቱ በኋላ ተሳፍረንበት ከነበረው አውሮፕላን ተገደን እንድንወርድ ተደርገናል” በማለት ለቢቢሲ ተናግሯል።
ዛሬ ረፋድ ላይ ወደ መቀለ ሊጓዝ በነበረው አውሮፕላን ውስጥ ሰላሳ የሚደርሱ መንገደኞች የነበሩ ሲሆን የአውሮፕላን ማረፊያው የደኅንነት ሠራተኞች የተሳፋሪዎቹን መታወቂያ ከተመለከቱ በኋላ ተጓዦቹ እንዲወርዱ ማደረጋቸውን አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ተሳፋሪ ገልጸዋል።
ቢቢሲ ያናገራቸው አንድ ተጓዥ እንዳሉት ደግሞ የጸጥታ ሠራተኞቹ የመንገደኞቹ ሞባይል እና ላፕቶፕ ሲቀበሉ መመልከታቸውን ተናግረው በረራውም ሳይሰረዝ እንዳልቀረ ገልጸዋል።
ወደ መቀለ እንዳይጓዙ ከተደረጉ ተሳፋሪዎች መካከል የዓለም አቀፉ የቀውስ ጉዳዮች አጥኚ ተቋም የኢትዮጵያ ተመራማሪ የሆነው ዊሊያም ዳቪሰንም እንዳለበት ቢቢሲ አረጋግጧል።
ሮይተርስ ወደ መቀሌ ለማምራት በዝግጅት ላይ የነበረው አውሮፕላን ውስጥ የነበሩ መንገደኞች ነገሩኝ ብሎ እንደዘገበው ከሆነ አረራት ጋዜጠኞችን ጨምሮ 12 የሚሆኑ ሰዎእ ወደ መቀሌ በረራ ለማድረግ ከተዘጋጀው አውሮፕላን ውስጥ እንዲወርዱ ተደርገዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔን ተከትሎ አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃንና ጋዜጠኞች በትግራይ የሚካሄደውን ምርጫ እንዳንዘግብ ጫና እየደረሰብን ነው ያሉ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዳይሬክተር ጌታቸው ደንቁ (ዶ/ር) ለድምጸ ወያኔ እንዲህ አይነት ነገር እንደሌለ ባለፈው ቅዳሜ ተናግረው ነበር። (BBC)