Connect with us

የመልስ መልስ ~ ይድረስ ለታከለ ኡማ!!

የመልስ መልስ ~ ይድረስ ለታከለ ኡማ!!
Photo: Social media

ትንታኔ

የመልስ መልስ ~ ይድረስ ለታከለ ኡማ!!

የመልስ መልስ ~ ይድረስ ለታከለ ኡማ!!
(እሱባለው ካሳ)

የቀድሞ የአዲስአበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ታከለ ኡማ ተናዷል። ኢዜማ የተባለውና በገዥው ፓርቲ ደጋፊነቱ ስሙ ተደጋግሞ የሚነሳው ፓርቲ በአዲስአበባ ከመሬት ወረራ እና ከህገወጥ የጋራ መኖርያ ቤቶች እደላ ጋር በተያያዘ የከተማውን አስተዳደር መተቸቱ ነው የንዴቱ መነሻ። እናም ትላንት በማህበራዊ ድረገፃች በለቀቀውና መልስ በሚመስል ሐተታ እንዲህ አለ።”…ለ20ሺህ አርሶአደሮች የተሰጡ የኮንዶሚኒየም ቤቶች በተመለከተም ከአንድ አመት ተኩል በፊት በካቢኔ የተወሰነና የተተገበረ ነው። በድብቅ የተተገበረም ሳይሆን በመንግስት ሚዲያም በይፋ የተገለፀ ነበር።

ከመሬታቸው ተፈናቅለው ሜዳ ላይ ከወደቁ በራሳቸው መሬት ላይ በተሰራ ህንጻ ዘበኛ እና ተሸካሚ ሆነው ከቀሩ 67 ሺህ አባወራዎች መሃል የከፋ ችግር ላይ ለወደቁት 20 ሺህ ኮንዶሚንየም ቢያንስ እንጂ የሚበዛ አይደለም።ከዚህ ውጭ በህገወጥ መንገድ የተሰጠ ምንም አይነት ቤት የለም።

ይህ ሥራችን በተደጋጋሚ በይፋ ስንናገር እንደነበረው የምናፍርበት ሳይሆን የምንኮራበት ነው። በግፍ የተገፋን፣ በግፍ ከመሬቱ የተፈናቀለን አርሶ አደር መካስ ያኮራናል…”

በእርግጥ ባለፉት ዓመታት የህወሓት/ኢህአዴግ የአገዛዝ ዘመን የኦሮሞ አርሶአደሮች በገፍ መፈናቀላቸው እውነት ነው። በወቅቱ የኦሮሞ ብቻ ሳይሆን የአማራ፣ የጋምቤላ፣ የአፋር…አርሶአደሮችም እጣቸው ተመሳሳይ ነበረ።

ከማንም በላይ ባለፉት ዓመታት የአዲስአበባ ህዝብ ሆን ተብሎ ታቅዶ በተተገበረ ስልት ተፈናቅሏል፣ ደኸይቷል። እትብቱ ከተቀበረበትና ኑሮውን ከመሰረተበት መሀል ከተማ በማፈናቀል ሕይወቱ ምስቅልቅሉ እንዲወጣና ማህበራዊ መሰረቱ እንዲንኮታኮት ተደርጓል።

ለአብነት ያህል አራት ኪሎን እንውሰድ።በአሁን ሰዓት የባሻወልዴ ችሎት ኮንደምኒየም የተሰራበት ቦታ ላይ በርካታ የጉስቁልና ህይወት የሚመሩ ሰዎች ነበሩ። ጠላና አረቄ ጭምር ቸርችረው የእለት ጉርሳቸውን የሚሸፍኑ ነበሩ። በግፍ ተነስተው ወደጀሞ አካባቢ ሲጣሉ የብዙዎች የዕለት ከእጅ ወደአፍ ገቢ ቀጥ አለ። በዚህ ምክንያት ቤታቸውን በርካሽ ሸጠው ለጎዳና ህይወትና ልመና የተዳረጉ፣ በብስጭት የአእምሮ ህመም የገጠማቸው፣ የሞቱ፣ የተጎዱ፣ የተሰደዱ ወገኖች ቤት ይቁጠራቸው። የብዙዎች አዲስአቤ እጣ ፈንታ እንዲሁ ተመሳሳይ ነበር። እናም “የቁስል ትንሽና ትልቅ አለው፣ የጉዳትም ብሄር አለው” ካልተባለ በስተቀር እነታከለ ኡማ የእነዚህም ወገኖች ጉዳት ሊሰማቸው ይገባ ነበር።

ከምንም በላይ አገር እንዲያስተዳድር ስልጣን የተረከበ አካል ታች ወርዶ “ብሄሬ፣ ጎሳዬ ተጎድቶ ነበር…ጅኒ ቁልቋል” እያለ የራሱን ብሄር ብቻ እየለየ በህዝብ ገንዘብ የተሰራ ቤትን ማደል ለህዝብ ማሰብን፣ መቆርቆርን ያሳያልን? የከንቲባነት ማእረግ ይዘው የነበሩት አቶ ታከለ ኡማ ሳይተርፈው ከ15 አመታት በላይ በየወሩ እየቆጠበ በተስፋ የሚኖረው ህዝብ ተስፋውን በመንጠቅ እንዴት በዚህ ደረጃ ሊጨክኑበት ቻሉ? ያሳዝናል!!

የሆነስ ሆነና ነገ ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ባለፉት ዓመታት “እኛም ተጎድተናል፣ ካሳ ይገባናል” በሚል ተመሳሳይ ጥያቄ ቢያቀርቡ የእነታከለ ብልፅግና ፓርቲ መልሱ ምን ሊሆን ነው?

እኔ እንደገባኝ ብዙዎቹ አክራሪ ብሄርተኞች ትልቁ ችግራቸው ከራሳቸው ብሄር ውጪ አሻግረው ማየት አለመቻላቸው ነው። ታከለ ኡማ የአዲስአበባ ከተማ ምክትል ከንቲባነቱ ወቅት ሁሉንም ወገን እኩል ከማገልገል ይልቅ “የእኔ ብሄር” ላለው ብቻ ታማኝነቱን ለማሳየት ብዙ ርቀት መሄዱ እንደእሱ አገላለፅ የሚያኮራ ሳይሆን የሚያሳፍር ነው።

”የእኔ ብሄር ተለይቶ ተጎዳ” አጀንዳ በሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ዘንድ ብቻ ሳይሆን አክራሪነትን አጥብቆ በሚጠየፈው የኦሮሞ ህዝብ ፊት ሲቀመጥ አንገት የሚያስደፋ እንጂ የሚያኮራ ሊሆን አይችልም።
አበቃሁ።

Click to comment

More in ትንታኔ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top