Connect with us

ይደርሰኛል ብሎ ከመጠበቅ እርም አውጥቶ መኖርም እድል ነው

ይደርሰኛል ብሎ ከመጠበቅ እርም አውጥቶ መኖርም እድል ነው
Photo: Social media

ማህበራዊ

ይደርሰኛል ብሎ ከመጠበቅ እርም አውጥቶ መኖርም እድል ነው

ይደርሰኛል ብሎ ከመጠበቅ እርም አውጥቶ መኖርም እድል ነው፡፡
ለመሆኑ በራሳችን የሰራነው ቤት ለራሳችን ለመሆኑ ዋስትና አለን?
****
ከስናፍቅሽ አዲስ
ሀገሩ መርዶ ሰምቶ ተቆራምቷል፤ ለኮንዶሚኒየም ተመዝጋቢ እርሙን እየበላ ከሚኖር እንዲህ ቁርጡን ማወቅ እድል ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ከንቲባዋ አዳነች አበቤ ካቢኔያቸውን ሰብስበው ጉዳዮን ሲያጠኑ ተመዝጋቢው የቤት ባለቤት የመሆን እድሉ በሰማይ ላም አለኝ ስለሆነባቸው እውነቱን ተናግረዋል፡፡

እውነቱን እንቀበል፤ የማይሰራ ቤት ይሰራል እያሉ ከዛሬ ነገ በጉጉት መሞት ለማንም አይጠቅምም፤ እውነቱን ከንቲባዋ እንዳሉት ለተመዘገበውና ለቆጠበው ቤት ሰርቶ ማስረከብ በቅርብ የማይቻል የሩቅ ስራ ከሆነ ጠብቁ ብሎ ማባበሉ ከመጠበቅ ያለፈ የቤት ባለቤት አያደርግም፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ሁለት ምርጫ ሰጥቷል፤ ብር ያለው ቤት ወስዶ ይገንባ ብር የሌለው ምርጫ ስለሌለው የሰራን ቀን እጣውን ጠብቆ ይግባ፡፡ ይህ እውነት ነው፡፡ ይልቁንስ ስላልተሰራው ከመነጋገር ስለተሰራው ቤት እጣ ፈንታ ብንመካከር ደግ ነው፡፡

አንዳንዶች ጥያቄያቸው ተደራጅተን የቤት ማህበር ስንመሰርት መሬት እንደሚሰጥ ቢነገርንም ቤት ሰርተን ቤቱ የኛ ነው ላለመባላችን ምን ዋስትና አለን? ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ይሄ ቀልድ መሬት ያለው መራር እውነት ማሳያ ነው፡፡ ዜጎች ቆጥበው በሰሩት ቤት እጣ ወጥቶላቸው የቤታቸው ባለቤት አልሆኑም፡፡ በአዲስ አበባ ነዋሪ ብር የተገነባ ቤት አንዴ ለተፈናቀለ፤ ሌላ ግዜ ለሹመኛ ደግሞ እንደ እዝን እንጀራ ለከንቲባ ለቅሶ መድረሻ ሆኖ ሲታደል አይተናል፡፡

ወያኔ ቤት ሰርታ ዘግና ትወስዳለች እንጂ በሙሉ አታፍሰውም፡፡ የሃያ ሰባት አመቱን ልማት በቤት ልማት ስንገመግመው ከአሁኑ ብቻ ሳይሆን ከሚመጣውም የሚሻል ነው ብለን ለመፈረጅ እንገደዳለን፤ ምክንያታችን ደግሞ የተሰራ ቤት እጣ ለማስረከብ ሁለት አመት ከአነሰ ቤት ለመስራት ሃምሳ አመት እንደማይበቃ መረዳት ይቻላል፡፡ በዚህ ስሌት የአዲስ አበባ ካቢኔ የወሰነው ውሳኔ ልክ ይመስለኛል፡፡

አሁንም ግን በገዛ ሀቃችን የምንገነባው ቤት ሲያልቅ የእኛ ለመሆኑ ምን ዋስትና አለው የሚለው ስላቅ ብዙ ጠቋሚ ምልክት ነውና ከስላቁ ጀርባ ያለውን መመልከት ለመንግስት ይጠቅመዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ መልካም ዘመን ለቤት ገንቢ ኮንትራክተሮች ብያለሁ፡፡

Click to comment

More in ማህበራዊ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top