ገዳን መማር ያስፈራው፤ ከገዳ ያልተማሩ ጥቂት አረመኔዎች ተግባር ነው፡፡ ገዳ ንድፈ ሀሳቡ ብቻ ሳይሆን ተግባሩም በኦሮሚያ በደንብ ሊሰጥ ይገባል፡፡
(ከስናፍቅሽ አዲስ)
—
አዲስ አበባ ውስጥ ገዳ በሥርዓተ ትምህርት ተካቶ ሊቀርብ ነው የሚለው ዜና መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ እርግጥ ገዳ ሀገረሰባዊ አንዱ የኢትዮጵያ እውቀት ነው ይሁን እንጂ በቅጡ አናውቀውም፡፡ ገዳን መማሩ ከዚህ አንጻር ችግር ላይሆን ይችላል፡፡ ገዳን ትማራለህ ተባልኩ ብሎ የደነገጠው እና እዚህ መንደር ሲንጫጫ የከረመው ግን ምክንያቱ ከገዳ ያልተማሩ ጥቂት አረመኔዎች ተግባር ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ቢያንስ አስር ሚሊዮን የሚሆን የኦሮሞ ወጣት አለ፡፡ ከዚህ አስር ሚሊዮን ቄሮ ውስጥ በተለያያ ቦታ ሊያውም ተደጋጋሚ ችግር በሚከሰትበት ውስን አካባቢ ሰው መግደልን፣ ቤት ማንደድንና ሀገር ማፍረስን ዓላማው ያደረገው ቁጥር ተደምሮ ሃምሳ ሺህ አይደርስም፤ ግን ተጽእኖው አይሏል፡፡
ምክንያቱ ደግሞ ጨዋው አደብ አላስዛውም፤ ህግና ስርዓት ዋጋውን አልሰጠውም፡፡ በዚህ አይነት ወጣት እይታ ገዳን የማያውቅ ገዳ የዚህ ወጣት ተግባር ይመስለዋል፡፡
እርግጥ ነው ገዳ ከሰለጠነውና ብዝሃነት ከገራው የአዲስ አበባ ተማሪ ይልቅ እንደ ምዕራብ አርሲ እና ባሌ ባሉ አካባቢዎች ትምህርቱ በአግባቡ ቢሰጥ ውጤት ያመጣል፡፡
ገዳ አቃፊ ቢሆንም ዛሬም በእነዚህ አካባቢ ከሚስት እቅፍ ባል ነጥቆ የሚያርድ ገዳን ያልተረዳ ገዳዳ አለና፤ የገዳ ሥርዓት በአያሌ አፍሪቃው መልካም እውቀቶችና ጥበቦች የተሞላ ነው ብናውቀው ብቻ ሳይሆን ብንተገብረው ገዳ ብዙ ይጠቅመናል፡፡
ገዳ ሌብነትን ይጠየፋል፤ ዛሬ በፖለቲካ ባኮረፈ ቁጥር የወገኑን ሱቅ የሚዘርፈው ወንበዴን ገዳ ቢማር ጥቅሙ ለሀገር ነው፡፡
የገዳ ሥርዓትን በትምህርት አካቶ ማስተማሩ በተለይም ኦሮሚያ ክልል በደንብ ቢተገበር ለውጥ ይመጣል፡፡
ለምሳሌ የጋሞ ወጣቶች ቅጠል ይዞ ሽማግሌ እግራቸውን ሰብሮ ከጥፋት ያስቀራቸዋል፤ በኦሮሚያስ የገዳ አባቶች ተቀባይነት ምን ድረስ ነው? አንድ አባ ገዳ ጥፋት ሊያስቆም ቢሞክር ይጠፋል ወይስ የሰበከው ሰላም ይሰማል?
የክልሉ መንግስት የኦሮሞ የባህል መሪዎችን ማገዝ አለበት፡፡ የገዳ ሥርዓት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በተግባር ሁሉ ታግዞ ሊማሩትና ሊያስፋፉት የሚገባው አንዱ ስፍራ ኦሮሚያ ነው፡፡
እንስሳ መግደልን የሚጠየፈው ገዳ ሰው መግደል ምን እንደሆነ ትርጉሙ ጥቂት ጽንፈኞችን ሊያስተምር ያስፈልጋል፡፡ ተምሮ የተለወጠ እና ሰላም የሚያጣጥም ወጣት ምን ተምሮ ነው በሚል ሌላውን ያስቀናል፤ ሌላው ከቀና ይማራል፡፡
እናም መጀመሪያ የገዳ ልጆች ገዳ ተምረው ገዳ የሚያስቀና ሰብዕና ሲያላብሳቸው ማሳየቱ ተጽእኖ ይበልጣል፡፡ እንዲያ ከሆነ ሁላችንም የገዳ ልጆች እንሆናለን፡፡