የኮሮና ቫይረስ በሽታ (ኮቪድ-19) በአለማችን ከተከስተ ዕለት አንስቶ እስካሁኑ ደቂቃ ድረስ በሚሊዩን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለህመም አጋልጧል፣ የበርካታ ሰዎችን ህይወት ነጥቋል፣ ማህበራዊ ስነ- ልቦናዊ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አስከትሏል፡፡
በሃገራችንም በመጋቢት ወር አንድ ታማሚ ከተመዘገበበት ዕለት ጀምሮ 48ሺ 140 በቫይረሱ የተያዙ፣357 ፅኑ ህሙማን እና 17 ሺ 415 ያገገሙ ሰዎች ደርሷል፡፡
የኮሮና ቫይረስ አዲስ ወረርሽኝ እንደመሆኑ በሰዎች ላይ የሚያስከትላቸውን የጎንዮሽ ችግሮች፣ የበሽታውን ሂደት፣ለመከላከል የሚያስችሉ ክትባቶች ብዙ ጥናቶች እና መላምቶች በመተንበይ ላይ ናቸው፡፡
አንድ ሰው ከኮሮና ቫይረስ ካገገመ በኃላ ምን አይነት የረጅም ጊዜ የጤና እክል ይኖረዋል ለሚለው ጥያቄ በተደረጉ ጥናቶች እንደ ሳንባ ቁስለት፣ የኩላሊት፣ የልብ እና የጭንቅላት የጤና እክል እንደሚያስከትል የወጡ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡
ከኮቪድ-19 ባገገሙ ሰዎች ላይ የሚታየው የሳንባ ቁስለት፣ በሽታው በታመሙበት ጊዜ በአይን የማይታዩ ለኦክስጅን ዝውውር የሚረዱ የሳንባ ክፍሎች ላይ በሚፈጥረው ችግር ምክንያት ይከሰታል፡፡ ከኮቪድ-19 በኋላ የሳንባ ቁስለት ያለባቸው ሰዎች በተከታታይ እንደትንፋሽ ማጠር፣ ደረቅ ሳል የመተንፈስ ችግር ያሳያሉ፡፡
ምንም እንኳን በእድሜያቸው ትንሽ የሆኑ ወጣት እና ጎልማሳዎች ከበሽታው ሊያገግሙ ቢችሉም በቻይና፣ ቪየና እንዲሁም በቅርብ በ20 ዓመት የቺካጎ ነዋሪ ላይ የተደረገው የሳንባ ንቅለ ተከላ በሽታው የሚያመጣው የሳንባ ቁስለት የጎላ ተጵፅኖ እንዳለው አሳይተዋል፡፡
ሌላው በረጅም የጤና እክል የሚጎዳው አካላችን የአንጎል እና የነርቭ ስርአት ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ካገገሙ በኃላ እንደራስ ምታት፣ መፍዘዝ፣ ነገሮችን በትኩረት አለማሰብ ወይም የማስታወስ ችግር እንደሚያጋጥማቸው ተናግረዋል፡፡ ተመራማሪዎቸ ይህ የጤና ችግር ሊከሰት የሚችለው በበሽታው ምክንያት አንጎል ላይ በኦክስጅን እጥረት በሚመጣው ጉዳት እንደሆነ አሳውቀዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ቫይረሱ በልብ ጡንቻ ላይ ከሚኖረው ተጽእኖ ጋር ተያይዞ የልብ ህመም እና ድካም በብዙዎቹ ታማሚዎች ላይ እንደሚያደርስ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡
እነዚህ የልብ፣ የሳንባ እና የደም ቧንቧ ችግሮች በኮሮና ቫይረስ ቤተሰብ በሆነው በሳርስ ታማሚዎች ላይ በተደረገ ጥናት 44 በመቶው የሚሆኑት ላይ ቫይረሱ ከተያዙ ከ12 አመት በኃላ ቢከሰትም በኮቪድ-19 ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ መከሰቱ በሽታው ምን ያክል አስጊ እንደሆነ ያመለክታል::
ምንም እንኳ እነዚህ ችግሮች ከፅኑ ህመም ባገገሙ ታማሚዎች ላይ ጎልቶ ሊታይ እንደሚችል ጥናቶች ቢያሳዩም፤ ምን ያህሉ እንዲሁም የትኞቹ የማህበረሰብ ክፍሎች እነኚህን የረጅም ጊዜ የጤና እክሎች እንደሚያጋጠሟቸው ለማወቅ ተጨማሪ ጥናቶች ያስፈልጋሉ፡፡
ስለሆነም ማኅበረሰቡ ማገገም ማለት ወደ ሙሉ ጤነኝነት መመለስ ላይሆን እንደሚችል በመረዳት ቫይረሱን ለመከላከል አካላዊ ርቀትን እና የእጅ ንፅህናን በመጠበቅ እንዲሁም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ በትክክል በመጠቀም ራስን እና ቤተሰብን ከኮሮና ቫይረስ እንዲጠብቅ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሳስቧል፡፡
ምንጭ:- የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት