Connect with us

የትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔ በመጭው ትውልድ ላይ የተሰነዘረ የንህዝላሎች

"የትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔ በመጭው ትውልድ ላይ የተሰነዘረ የንህዝላሎች ቅጣት ነው"
Photo: Social Media

ትንታኔ

የትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔ በመጭው ትውልድ ላይ የተሰነዘረ የንህዝላሎች

“የትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔ በመጭው ትውልድ ላይ የተሰነዘረ የንህዝላሎች ቅጣት ነው”
(ሙሼ ሰሙ)

ትምህርት ሚኒስቴር መግለጫ ከሰጠ ቀን ጀምሮ ወላጆች የማመዛዘኛ ጊዜ እንኳን ሳናገኝ በት/ ቤቶች የስልክ መልዕክት እየተጨናነቅን ነው፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር እድሉን ነፍጎናል፣ መ/ቤቱ በጉዳዩ ላይ “ቢወያይም” ውሳኔው ላይ እንዴት እንደ ደረሰ አልገለጸልንም፡፡ የውይይት ሰነዱ ላይ ባለሙያ አስተያየት እንዲሰጥበት ይፋ አልተደረገም። ከውይይቱ በፊት ግብዓት የሚሆኑ ሙያዊ ጥናቶች መኖራቸው አይታወቅም፡፡ ውይይቱ ወላጆችን ጨምሮ የትኞቹን ባለድርሻ አካላት እንዳሳተፈ አይታወቀም፡፡

በርካታ መላ ምቶች ቢኖሩም ትምህርት ቤት መክፈት ዓለምን እያወዛገበ ያለ ጉዳይ ነው። ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት በቂ ዝግጅት ቢኖርም እንኳን የቫይረሱን ስርጭት ከ5 % በታች ካልወረደ ትምህርት ቤት መክፍትን አይመክርም፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ የቫይረስ ስርጫቷ ከ5 % በላይ ነው ፡፡

በየትምህርት ቤቶቻችን በአንድ ክፍል ውስጥ ከ30 እስከ ሰማኒያ ተማሪዎች ተፋፍገው ይማራሉ፡፡ በመመገቢያ ሰዓት እንደ ሰርዲን ታጭቀው ይተራመሱበታል። በእረፍት ስዓት አናት በአናት ይረባረቡበታል። ወላጆች በየቀኑ ሳኒታይዘርና የአፍ መሸፈኛ ለማቅረብ ይቅርና ልጆቻቸውን ምግብ አስይዘው ት/ቤት መላክ ዳገት የሆነባት ሃገር ነች፡፡ አብዛኛው የሀገራችን ት/ቤቶች ውሃ ለማቅረብ እንኳን መሰረተ ልማቱ የላቸውም፡፡ ቧንቧ ቢኖር እንኳን ውሃ በየቀኑ ይቅርና በየሳምንት ማግኝታቸው ለተዓምር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከምግብ እጥረት የተነሳ በቀላሉ ለበሽታ የሚጋለጡና ለጤና እክሎች የተዳረጉ ሕፃናት በስፋት የሚኖሩባት ሀገር ነች፡፡ ረጅም መንገድ በትራንስፖርት ተጉዞ ትምህርት ቤት መሄድ፣ ዛሬም ያልተፈታ ችግር ነው፡፡

ይህ ሁሉ ውስብስብ ችግር ባለበት ሁኔታ ልጆቻችንን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ አንድ ሚኒስቴር መስርያ ቤት የሚገኙ የጤናና የኮቪድ ሙያዊ እውቀት የሌላቸው ግለሰቦች ጉዳይ ብቻ ተደርጎ መወሰዱ ከቸልተኝነቱም በላይ በትውልዱ ሕይወት ላይ የመቀለድ ያህል ነው፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ትምህርት ቤት ልከፍት ነውና “እንደ ፍጥርጥራችሁ” ጥንቃቄ አድርጉ በማለት፣ ያለ በቂ ዝግጅትና ምክክር አደጋውን ከነውጤቱ ወላጆች ላይ ወርውሮ ከደሙ ንጹህ ነኝ እያለ እንደሆነ ከመግለጫው ይዘት መረዳት ይቻላል፡፡

ማንም እርግጠኛ ባልሆነበት በተለይ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የበሽታውን ስርጭት አስመልክቶ ያለኝ መረጃ አስተማማኝ አይደለም በሚልበት፣ ዓለም በሚወዛገብበት ጊዜው፣ በሙያዊ ጥናት ሳይታገዙ፣ በውይይት ላይ ብቻ ተመስርቶ ልጆቻችሁንና እራሳችሁን ለኮቪድ አጋልጡ የሚል ውሳኔ ላይ ለመድረስ ማንኛውም ምድራዊ ሃይል ስልጣን የለውም። ሌላው ቢቀር ልጆቻችንን ጨምሮ ለበሽታው ልንጋለጥ የምንችለው ወላጆች፣ አመዛዝነን መወሰን እንድንችል በቅድሚያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይቶች በመገናኛ ብዙሃን መካሄድ ነበረባቸው።

በዚህ ሁሉ ውጥንቅ ውስጥ ተመዝገቡ ማለት ትምህርት ቤቶች የገጠማቸውን የገንዘብ እጥረት በልጆቻችሁ ሕይወት እናካክስ ከማለት ውጭ ትርጉም አይሰጥም፡፡ ዛሬ መግለጫ ሰጥቶት፣ ነገ ተመዝገቡ ማለትስ ወላጅን አስጨንቆ ክፍያ እንዲፈጽም ከማድረግ ውጭ ምን ትርጉም ይሰጠዋል።

አሁንም የተመዝገቡ ጥሪው ቆሞ ጉዳዩ እንደገና በሁሉም ባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎና በሙያተኞች ጥናት ላይ ተመስርቶ በጋራ መተማመን ላይ ተደርሶበት ልንወስን ይገባል፡፡ ልጆች ተጋላጭነታቸው ዝቅተኛ ነው ቢባልም በልጁ ሕልውና ላይ መወስን የሚችለው ወላጅ ብቻ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ በጥቅሉ፣ ይህ ውሳኔ በመጭው ትውልድ ላይ የተሰነዘረ የንህዝላሎች ቅጣት ነው።

Click to comment

More in ትንታኔ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top