ጥቂት ነጥቦች ስለአይ ኪው
(ታምራት ኪዳነማርያም)
ስለ አይ ኪው ወይም ትምህርት የመረዳትና ማመዛዘን ችሎታ መመዘኛ ውጤታችን ብዙ እየተባለ ነው። እርግጥ የትምህርት ሥርዓታችን በርካታ ችግሮች እና ድክመቱ እንደተጠበቀ ሆኖ መለኪያው ግን መሠረታዊ ችግር አለበት። ሲጀመር መለኪያ ጥያቄው የሚዘጋጀው በእንግሊዝኛ ነው። ጥሩ የእንግሊዝኛ ዕውቀት ያለውና የሌለው ሰው ተፈትኖ እኩል አያመጣም።
ሁለተኛ የአውሮፖውያንን ባህልና አኗኗር የሚያውቅና የማያውቅ ሰው ተፈትኖ ዕኩል አያመጣም። ኮሪያንና ሆንግኮንግን የመሳሰሉ የነሱ ኮሎኒዎችን እና ሸቀጥ ማራገፊያዎች አንደኛ ወጡ ይሉሀል።
ይሄ የጥቁር አፍሪካውን ሞራል መንኪያ ዘዴ ነው። ኮሪያ ሁለተኛ ወጣች አሉ እንጂ በኢኮኖሚ ዕድገት ግን ጆሮዋ ቢቆረጥ እንግሊዝኛ የማትሰማው ቻይና ሁለተኛ መሆኗን ልባቸው ያውቀዋል። ኧረ በቅርቡ አንደኝነቱን እንዳትረከብ ያሰጋታል። በአጠቃላይ ልጆቻችን እና ወጣቱ ዕኩል አይደለሁም እንዲል እና የአዕምሮ የበታችነት እንዲሰማው ማድረጊያ ነው።
ምዕራባዊነትን ማስፋፊያ ነው። ልጆችህን የራስህን ቋንቋ እና ባህል እርግፍ አድርገህ ትተህ ሙሉ ለሙሉ በእነሱ ቋንቋ እንድታስተምር እና ባህላቸውን እንድትወርስ መገፋፊያ ነው። በሰው ቋንቋ ተምሮ የበለፀገ አንድም ሀገር የለም። ስለዚህ ወደ እድገት መምጪያው አንዱ መንገድ በራስ ቋንቋ መማር፣ መመራመር፣ መጻፍና ማሰብ በመሆኑ እንዳንደርስባቸው የሚጠቀሙበት የረቀቀ ዘዴ ነው።
በቅጡ ማሰብ እንዳንጀምር የሚደረግብን ክልከላ ነው። ኢትዮጵያውያን ዘመናዊ/አውሮፓዊ ትምህርት ቤቶችን ካቋቋምን አንስቶ በቅጡ እያሰብን ነው ወይ ብለን እራሳችንን መጠየቅ አለብን። አፍሪካ ፈረንጆችን ከመከተል ውጪ በራሷ እንድታስብ እና በራሷ አስተሳሰብ እንድትመራ አይፈለግም። እንደ ሩቅ ምሥራቆች የራሷን አስተሳሰቦች እና ዕውቀቶች አበልፅጋ ዕለት ተለት ኑሮዋን በምትመራበት ቋንቋ ተምራና ተመራምራ ተፎካካሪ እንድትሆን አይፈለግም።
በፈረንጅ እንጂ በራሷ አዕምሮ ማሰብ አትችልም። ተማሪዎቻችን የሚማሩት በባዕድ እና ቢያንስ ዕለት ተዕለት ኑሯቸውን መምራት በማይችሉበት ቋንቋ በመሆኑ የተማሩት ትንሽ እንኳን የሚገባቸው ለፈተና ከሸመደዱ በኋላ ነው። እየገባቸው አይማሩም። ለማሰብና አስተማሪውን በጥያቄ ለማፋጠጥ ፋታ የላቸውም። የሚነገራቸውን ሳይገባቸው ከመቀበልና ከመሸምደድ ውጪ ምንም ማድረግ አይችሉም። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ዕውቀቱን ሊሸመድዱት እንጂ ሊይዙትና ሊዋሀዳቸው አይችሉም። ሊመራመሩበትና ሊመረምሩት አይችሉም ወይም ይከብዳቸዋል።
የጃፓን ልጅ ፊዚክስ በጃፓንኛ ሲማር ወዲያው ይገባዋል። ፊዚክስ ሲማርና ሲያጠና ጊዜውን ሙሉ ለሙሉ የሚያጠፋው በፊዚክሱ ብቻ ነው። የኛ ልጆች ግን ፊዚክስ ሲማሩ አብዛኛው ጊዜያቸው የሚባክነው ከቋንቋው ጋር በመታገል ነው። አንዳንዴ ጥያቄ ሲሰሩ የሚሳሳቱት ቋንቋው ስለሚሸውዳቸው ነው። ዕውቀቱ ከውስጣቸው ጋር አይዋሀድም። ኑሮ ውስጥ አይጠቀሙበትም። መማሪያ መጻሕፍቱም ከኢትዮጵያ ጋር ያልተገናዘቡ የውጪ መጽሀፎች በመሆናቸው በቀላሉ አይዋሀዱንም።
የሶሻል ሳይንስ ተማሪዎቻችንም መጀመሪያ በውጪ ቋንቋ የተቀመጠውን የውጪ ዕውቀት በድንግዝግዝ እንኳን ለመረዳት ጊዜ ያጠፋሉ። ከዛ በድንግዝግዝ የተረዱትን ዕውቀት መልሰው በእንግሊዝኛ አሳክተው ለመጻፍ ጊዜ ይወስድባቸዋል። በ1ወር ማለቅ የሚችል ሪሠርች ዓመት ይወስድባቸዋል። በዚያ ላይ በምርምር ጽሁፋቸው ችግር ፈቺ ሀሳብ ለማቅረብ ፋታ የላቸውም። አዲስ ዓይነት ሀሳብ ይዞ ብቅ ማለትማ ጨርሶ የሚታሰብ አይደለም። ያነበቧቸው መጻህፍቶችን አደናንቀው ያንኑ ሀሳብ ከመድገም ውጪ ሌላ ነገርና የራሳቸው መፍትሄ ለማመንጨት ይቸገራሉ። ያገኙትን ዕውቀት ትክክለኛነቱን መልሰው ለመገምገምና ለማብጠልጠል የሚታሰብ አይደለም። ያገኙትን ዕውቀት ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር እያስተያዩ ለመገምገም ፋታ የላቸውም። የራሳቸውን አገራዊ ዕውቀት አይማሩም።
ባህላዊ ዕውቀቶቻችንን ዞር ብሎ ለማየት ጊዜ የላቸውም። ዲሲፕሊኑም ያን ያህል አይፈቅድላቸውም። አገራዊውን ዕውቀት ማበልጸግ አይችሉም። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ፈረንጅን ሁሌ መከተል እንጂ መቅደም ወይም በራስ መንገድ መሄድ አይቻልም። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ የራሳችንን ስልጣኔ ይዘን ብቅ ለማለትና ለዓለም አዲስ ነገር ለማበርከት አስቸጋሪ ነው።
አይኪው መለኪያ ተብዬውም በዚሁ በውጪ ቋንቋ የመማር የስህተት ጎዳናችን አጠንክረን እንድንቀጥልና የበታችነታችንን እንድንቀበል ማድረጊያ ዘዴ ነው። ወጣቱ በዚህ ቁጭት ሊይዘውና ማሰብ ሊጀምር እንጂ ማሰብ ሊያቆም አይገባም። በፈረንጅ አዕምሮ ማሰብ ትቶ በራሱ አዕምሮ ማሰብ መጀመር አለበት። ምሁሩ ችግር ፈቺ ጥናቶችን እና ምርምሮችን ማድረግ አለበት። ከውጪ ሀገር የሚገቡትን ምርቶች በሙሉ እራሳችን ለማምረትና ኮፒ ለማድረግ መጣጣር አለብን።
በመቀጠል ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እነሱን ወደ ማሻሻልና አዳዲስ ምርቶችንና ዘዴዎችን ወደ መፈልሰፍ እንደርሳለን። መንግሥት በሳይንስ ሚኒስቴር ስር ይህንን የሚሠራና የሚያስተባብር አንድ ግዙፍ ተቋም ቢያቋቁም ጥሩ ነው። የራሳችንን ባህላዊ ምርቶችንም መጠቀም፣ ማሳደግና ማዘመን ይኖርብናል። የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤቶችም በእንግሊዝኛ መንደፋደፉን ትተው ዋና ዋና ዕውቀቱን ለተማሪው በራሳችን ቋንቋ/ዎች ማስጨበጥ አለባቸው። የሚያስቡ ቴክኒሻኖችና ኢንጂኒየሮች ማፍራት ያስፈልጋል።
እንግሊዝኛውን እንደ አንድ የውጪ ቋንቋ መጻፍና ማንበብ ብቻ ሳይሆን መናገርና ማዳመጥ ላይ ያተኮረ ትምህርት ማስተማር ይቻላል። ወጣቱ የሚያነበውን ነገር በሙሉ እየገመገመ እና እየተቸ ማንበብ እንጂ ትክክል አድርጎ መቁጠር ማቆም አለበት። የሚሰማውንም እንዳለ መቀበሉን መተው አለበት። ከውጪ የሚገቡ ሀሳቦችና ዕውቀቶች በሙሉ መገምገም አለባቸው እንጂ እንደትክክለኛ ተደርገው ሊወሰዱ አይገባም።
ለኛ የሚሠሩ እና የማይሠሩ መሆናቸው መፈተሽ አለባቸው። የራሳችንን አገር በቀላዊ ዕውቀቶች መመርመርና መመራመር መጀመር አለብን። የራሳችንን ዕውቀቶች የትምህርታችን እና የምርምሮቻችን መሠረት ማድረግና ማበልፀግ ይገባናል። የአይኪው መለኪያ ውጤት የተባለው እውነት ከሆነ ትክክለኛውን ጎዳና ለመፈለግ የሚያነሳሳን ሊሆን ይገባል እንጂ የትውልዱን ሞራል የሚሠብርና ወደ ስህተት የሚመራው መሆን የለበትም።