Connect with us

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ጋር የሚጣሉ ይደቃሉ

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ጋር የሚጣሉ ይደቃሉ
Photo: Social Media

ህግና ስርዓት

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ጋር የሚጣሉ ይደቃሉ

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ጋር የሚጣሉ ይደቃሉ:- የፋሽስቱ ሞሶሎኒን የመከነ አጀንዳ ለማስፈፀም የሚኳትኑ የዘመናችን ቡክኖች

በዲ/ን ተረፈ ወርቁ

‘‘ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ይደቅቃሉ፤’’ (፪፤፲)
ፋሽስቱ፣ የኢጣሊያ መሪ ሞሶሎኒ ከዐርባ ዓመት በኋላ የዐድዋውን አሳፋሪ ሽንፈትና ውርደት ለመበቀል ‘‘ክተት ሰራዊት ምታ ነጋሪት’’ ብሎ ኢትዮጵያ ሀገራችንን ሲወር አስቀድሞ በሚሲዮናዊነት (በወንጌል ስብከት ስም) እና በጥናትና ምርምር ሰበብ ለስለላ ባሰማራቸው ሰዎቹ/ሰላዮቹ በሰበሰበውና ባሰባሰበው መረጃ መሠረት በሕዝባችን ላይ ለማየትም ሆነ ለመስማት የሚዘገንኑ በርካታ አሰቃቂ የጭካኔ ድርጊቶችን ፈጽሟል፡፡

ፋሽስቱ ሞሶሎኒ ኢትዮጵያን በቅኝ ለመግዛት ያለመበትን ጦርነት በድል በመወጣት፣ የዐድዋውን ሽንፈት በመበቀል ‘‘የታላቂቱ’’ ሮማን ክብር ለመመለስና፣ ሀገሩን ከተከናነበችው የታሪክ ቅሌቷና ስብራቷ ለመታደግ፤ ለነጻነቱ ቀናዒ በሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ሁለት ዐበይት ርምጃዎችን ወስዷል፡፡

የመጀመሪያው ሕዝቡን በብሔር/በጎሳ ለመከፋፈል ያደረገው ሙከራ ሲሆን ሌላኛው የጭካኔ ርምጃው ደግሞ ለኢትዮጵያ አንድነትና ነጻነት መምህር፣ ጠበቃ የሆነችውን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያንን ማዳከም፣ ቢቻልም ማጥፋትን ዋናና ተቀዳሚ ሥራው/አጀንዳው አድርጎት ነበር፡፡

ወራሪው የፋሽስት ኢጣሊያ መንግሥት በዚህ እኩይ ድርጊቱ ለኢትዮጵያ ነጻነትና አንድነት መምህርና ጠበቃ በሆነችው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ላይ ፈርጣማ ክንዱን አሳርፎባት ነበር፡፡ በዚህም እኩይ ድርጊቱ ከታላቁ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ጀምሮ ባሕር ማዶ ተሻግሮ በኢየሩሳሌም በሚገኘው ዴር ሱልጣን ገዳማችን ድረስ በዘለቀ የጥቃት ሠንሠለት የቤተክርስትያኒቱን ታላላቅ አባቶቻችንና ሊቃውንትን በፋሽስታዊ ጭካኔ እንዲወገዱ፣ እንዲረሸኑ አድርጓል፡፡

በቤተክርስትያኒቱ ዘንድ እንደ አዕማድ መስለው የሚታዩትን እንደ ሰማዕታቱ አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካኤል የመሳሰሉ ብፁዓን አባቶችንም በአደባባይ ሕዝብ ሰብስቦ በጥይት እንዲበደቡ በማድረግ ሕዝቡን በማሸማቀቅ፣ ክቡር የነጻነት መንፈሱን በማዳከም የኢትዮጵያ ቤተክርስትያንን በፋሽስት መዳፍ ሥር እንድትወድቅ የቻለውን ሁሉ ሞክሯል፡፡

የምሥራቅ አፍሪቃ ኢጣሊያ ቅኝ ሀገራት ገዥ የነበረው ግራዚያኒ ለአለቃው ለሞሶሎኒ የላከው ምሥጢራዊ የቴሌግራም- የፋሽስት መንግሥት በኢትዮጵያ ቤ/ክ ላይ ያራምድ የነበረውን እኩይ፣ መሰሪ አቋሙንና ድብቅ አጀንዳውን ያጋለጠ ነበር፡፡ ለአብነት ያህልም የፋሽስት መንግሥት በወቅቱ ያደረጓቸውን የቴሌግራም መልእክት ልውውጦችን እንመልከት፡፡

ኢጣሊያ ምሥራቅ አፍሪካ ጠቅላይ ግዛት
የፕሮቶኮል መዝገብ ቁጥር 9325
አዲስ አበባ ግንቦት 24/1937 ዓ.ም.
ጥብቅ ምሥጢር፡- ለጄኔራል ማሌቲ- ደብረ ብርሃን፣
ለካራቢኜራዎች ዋና አዛዥ- አዲስ አበባ፤
ቁጥር 26609- የደብረ ሊባኖስ ጉዳይ ሙሉ ሓላፊነቱ የእርስዎ እንደሆነ አረጋግጬያለሁ፡፡ የደብረ ሊባኖስ ገዳም መነኮሳትና ዲያቆናት ሁሉም አንድ ሣይቀር በጥይት እንድትፈጇቸው አዝዣለሁ፡፡ ትእዛዝህን በአስቸኳይ አስፈፅሜያለሁ በሚል ቃል እንድታረጋግጥልኝ ይሁን!
(ማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኒ)

የኢትዮጵያ ታላቅ ባለውለታ የነበሩትና የኢጣሊያን ፋሽስት ጭካኔና ግፍ ለዓለም ሁሉ በማጋለጥ ከኢትዮጵያውያን ጎን የቆሙት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ የነበሩት ሲሊቪያ ፓንክረስት፤ የፋሽስቱ መሪ ቤኒቶ ሞሶሊኒ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ አባቶችና ሊቃውንት ላይ እየተወሰደ ያለው ርምጃ ሌሎች ኢትዮጵያውያንን ሊያሸማቅቅ እንደሚችልና ጭፍጨፋውም ውጤታማ እንደሆነ በወቅቱ ለምሥራቅ አፍሪካ ለቅኝ ግዛት ሚ/ሩ ለግራዚያኒ ያስተላለፈውን ምስጢራዊ የቴሌግራም መልእክት Ethiopia and Eritrea በሚለው መጽሐፋቸው እንዲህ ጠቅሰውታል፤

… the execution of Abune Petros, one of the four Ethiopian bishops, has terrified the leaders and the public. The work of repression against armed groups dispersed in the forest continues. All prisoners have been shot. Inexorable reprisals have been effected against the populations guilty, if not complicity, at least of lack of favourable attitude. (A telegram of March 1, 1937)

ይሁን እንጂ ፋሽስቱ ሞሶሎኒ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን መንፈሳዊ አባቶችና ሊቃውንት በመግደል እንዲሁም በርካታ አብያተ ክርስትያናትንና ገዳማትን በማቃጠልና በመዝረፍ ቤተክርስትያኒቱንም ሆነ ኢትዮጵያን በመዳፉ ሥር ለማድረግ ያደረገው ሙከራ ሊሳካለት አልቻለም፡፡ እንደውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ጫፍ- እምቢ ለሃይማኖቴ፣ እምቢ ለነጻነቴ፣ እምቢኝ ለሀገሬ ኢትዮጵያ! በሚል ቀፎው እንደተነካ ንብ በአንድነት ሆ! ብሎ ተነሣ፡፡

ዐርበኞችን ለሀገር መሞት፤ ማን አስተማራቸው፣
ጴጥሮስ አይደለም ወይ ባርኮ የሰጣቸው፡፡

በሚል ቅኔ በተቀኘላቸው በሰማዕቱ የአቡነ ጴጥሮስ ጀግንነት፣ የሀገር ፍቅርና የነጻነት ክቡር መንፈስ እልፍ ኢትዮጵያውያን አባትና እናት አርበኞች ፋሽስት ሠራዊትን በጀግንነት በመፋለም መቆሚያ መቀመጫ ነሱት፡፡ የሰማዕታቱ የአቡነ ጴጥሮስ፣ የአቡነ ሚካኤል የነጻነት ክቡር መንፈስ በኢትዮጵያ ተራሮች፣ ዱርና ሸንተረሮች በስፋት ናኘ፡፡ የሰማዕታቱ፣ የአባቶቻችን ደም እልፍ ጀግኖችን አብቅሎ የፋሽስት ጦርን እረፍት ነሳው፡፡ በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ በየአድባራቱና በየገዳማቱ ያሉ አባቶች፣ መነኮሳትና መናንያንም መንፈሳዊ ሰይፋቸው፣ ሥውር ሰራዊታቸው በሆነው ምሕላቸው እና ጸሎታቸው፤

‘እግዝትነ ማርያም ስሚዓ ኀዘና ወብካያ ለሀገሪትነ ኢትዮጵያ’ በሚል ጠዋትና ማታ በእንባ በኢትዮጵያ አምላክ ዘንድ እንደ ራሄል ወደ ሰማይ፣ ወደ አርያም የረጩት እንባቸው፣ በጨካኞቹ የፋሽስት እጅ በግፍ የፈሰሰ የሰማዕታቱ ደም ሀገራችን ኢትዮጵያን ከጨካኙ የፋሽስት ቅኝ ገዥ ኃይል ጽኑ አገዛዝ እንድትላቀቅ አደረጋት፡፡

ፋሽስቱ ሞሶሎኒ በሮም አደባባይ ለሕዝቡ ባደረገው ንግግሩ፤ ‘‘ኢትዮጵያን አምላኬ የምትለው እግዚአብሔር ከኃያሉ ክንዴ የሚታደጋት፣ የሚያድናት ከሆነ የእኔንም እግዚአብሔር፤ የእኔንም አምላክ ልጨምርላት እችላለኹ፡፡’’ የሚለው በእብሪትና በትእቢት የተሞላው ንግግሩ ከንቱ ሆኖ ቀረ፡፡ እናም ፋሽስቱ ቢኒቶ ሞሶሎኒ የውርደት ሽንፈቱን ተከናንቦ በገዛ ሀገሩና ሕዝቡ ፊት በስቅላት፣ የውርደት ሞት ፍርዱን እንዲቀበል ተደረገ፡፡

‘‘ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች’’ የሚለው ትንቢታዊ ቃል ፍጻሜውን አግኝቶ- የእግዚአብሔር ኃይልና ክንድ- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያንን፣ የሀገራችንን የኢትዮጵያ ጠላቶችን እንዲደቁ፣ እንደ ጭስ በነው እንደ ጉም ተነው እንዲጠፉ አደረጋቸው፡፡ ዛሬም ድረስ ስም አጠራራቸው የከፋ እንዲሆንም ሆነ፡፡

ግራዚያኒም ለአለቃው ለፋሽስቱ ሞሶሎኒ፤ ‘‘የኢትዮጵያን ከሕዝቧ ጋር ካልሆነም ኢትዮጵያን ብቻዋን አስረክብኻለኹ፤’’ በማለት የገባው ቃል እንደ ግንቦት ደመና ተበትኖ ቀረ፡፡ የፋሽስቱ ኢጣሊያ ሽንፈቱንና ውርደቱን ተከናንቦ ወደመጣበት ሀገሩ አንገቱን አቀርቅሮ ተመለሰ፡፡ መላው ዓለም ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ተጋድሎ ነጻነቷና ሉዓላዊነት የተከበረ ታላቅ ሀገር መሆኗን ዳግመኛ አረጋገጠ፡፡ የኢትዮጵያ ጠላቶችም አፈሩ፣ የሃፍረት ማቅን ለበሱ፡፡

ይህን የታሪክ ሐቅ የማያውቁ አሊያም ለማወቅ የማይሹ የታሪክ ጠበኞች- የፋሽስቱ ሞሶሎኒንን የመከነ የጥፋት አጀንዳ፤ በሀገራችን ኢትዮጵያ እና በኦርቶዶክሳዊት በቤተክርስትያናችን ላይ ለማስፈፀም የሚኳትኑ የዘመናችን ቡክኖችን በተመለከተ፣ በቀጣይ የመጨረሻ ክፍል ጽሑፌ እንደምመለስበት ቃል በመግባት ልሰናበት፡፡
አምላከ ሰማዕታት አፅራረ ቤተክርስትያንን ያስታግስልን!!
ሰላም!!

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top