Connect with us

“የኮምሽኑ ሪፖርት ሚዛናዊ አይደለም” የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት

"የኮምሽኑ ሪፖርት ሚዛናዊ አይደለም" የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት
Photo: Social Media

ፓለቲካ

“የኮምሽኑ ሪፖርት ሚዛናዊ አይደለም” የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት

“የኮምሽኑ ሪፖርት ሚዛናዊ አይደለም” የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ነሐሴ 14 ቀን 2012 ዓ.ም የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሰሞናዊ ሁኔታን በተመለከተ መግለጫ መዉጣቱ ይታወቃል፡ መግለጫዉ በኦሮሚያ ክልል “የጸጥታ አካላት ተመጣጣኝ ያልሆነ የሀይል እርምጃ ወስደዋል፡፡ ሰላማዊ ሠልፍ የወጡ ዜጎች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት ደርሷል” በሚል ያወጣዉ ሪፖርተ ከእዉነት የራቀ እና ነባራዊ ሁኔታን ያላገናዘበ መሆኑን እንገልፃለን ፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በህግ የበላይነት በማስከበር የዜጎች ነፃነት፤ እኩልነትና አብሮነት እንዲገነባ ግዴታዉን ለመወጣት በከፍተኛ ቁርጠኝነት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ ስለሆነም አንድም ዜጋ ያለአግባብ እንዲጎዳና ሰብአዊ መብቱ እንዲጣስ ፈጽሞ አይፈቅድም፡፡

የክልሉ መንግሥት የዜጎች ሰብአዊ መብት ተከብሮ በሀገር ግንባታ ሂደት ዉስጥ በነፃነት እንዲሳተፉና የበኩላቸዉን ድርሻ እንዲያበረክቱ ከህግ ማዕቀፍ ዝርጋታ እስከ ተቋማት ግንባታ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የዴሞክራሲ ምዕዳሩ ሰፍቶ ሁሉም የፖለቲካ ተዋናዮች በሠላምና በነፃነት ህግን አክብረዉ እንዲንቀሳቀሱና በያዙት ሃሳብ በሰላማዊ መንገድ እንደዲወዳደሩ ምቹ ምህዳር ለማመቻቸት በቁርጠኝነት በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ይሁን እንጂ ከዚህ በተቃራኒ የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደቱንና የዜጎችን በነፃነት የመወሰን መብት በማጨናገፍ ሀገሪቷን በሴራ ፖለቲካ በማተራመስ በአቋራጭ የመንግስትን ስልጣን ለመቆናጠጥ የተሰማሩት እንደ ወያኔ እና ኦነግ ሸኔ፤ኦሮሚያን የትርምስ ማዕከል ለማድረግ በገጠርና በከተማ ወንጀለኛ ቡድኖችን መልምለዉ አሰልጥነዉ እና አስታጥቀዉ በማሰማራት የመንግሥት አመራሮች፤ ታዋቂ ሰዎችንና የፀጥታ አካላትን እንዲሁም ሰላማዊ ሰዎችን በመግደል እና አካላዊ ጉዳት እንዲደርስ ተቀናጅተዉ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኙ ሀገር ያወቀዉ ጸሃይ የሞቀዉ እዉነታ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

እነዚህ ሀይሎች በተካኑት የተንኮል እና የሴራ ፖለቲካ ተቀናጅተዉ በመንቀሳቀስ ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት፣ በየደረጃዉ ያለዉን የመንግሥት መዋቅር በማፍረስ፤ የመንግሥትና የፋይናንስ ተቋማትን በማዉደም፤ የግለሰቦችን ሃብትና ንብረት በማዉደም፣ የአገልግሎት ተቋማትን በማጋየትና ንብረትን በመዝረፍ ተግባር ላይ አትኩረዉ እየተንቀሳቀሱ መሆኑ በተጨባጭ ተረጋግጧል፡፡

በእስካሁን ሂደት መንግሥት የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ያሳየዉን ሆደ-ሰፊነትና ትዕግስት እንደ እድል ተጠቅመዉ በሃሳብ ልዕልና አምነዉ ከመወዳደር ይልቅ ለሽብር ተግባራት አሰልጥነዉ ካሰማሩአቸዉ ቡድኖች በተጨማሪ፣ ሀላፊነት በጎደለዉ መልኩ በዉጭ ሃገር እና በሀገር ዉስጥ ሚዲያዎች የመንግሥትና የግል ተቋማት እንዲወድሙ፤ መንገዶች እንዲዘጉ፤ የንግድና ማናቸዉም እንቅስቃሴዎች እንዲገደቡ፣ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ በግልጽ ቅስቀሳ እያደረጉ እንደሆነ መላዉ ህዝባችን የሚያዉቀዉ ጉዳይ ነዉ፡፡

ሠሞኑን “12/12/12” ብለዉ የጠሩት የጥፋት ድግስም ሰላማዊ ሰልፍ ሳይሆን የሁከትና የብጥብጥ ሰልፍ ነበር፡፡ ይህ የብጥብጥና የሁከት ጥሪ ጠሪ ባለቤት የሌለዉ፣ ሀገራችን የኮቪድ 19 ወረረርሽን ለመቆጣጠር ያወጀችንዉን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚቃረን፣ በጦር መሳሪያ የታገዘ እና በወያኔ ሚዲያዎች ዉጭ ሀገር ባሚገኙ ጽንፈኛ ሚዲያዎች ሰፊ የጥፋት ቅስቀሳዎች የተደረገበት ነዉ፡፡ ዓላማዉም ሁከት እና ብጥጠብጥ በመፍጠር መንግስት ላይ ጫና በማሳደር በወንጀልተጠርጥረዉ የህግ ቁጥጥር ስር ያሉ ግለሰቦችን በማስፈታት የመንግስትን ህግን የማስከበር ሂደት ማደናቀፍ ነዉ፡፡

በተለይም በኦሮሚያ ክልል ብሄር ተኮር እና ሃይማኖታዊ ግጭቶችን ለመቀስቀስ፣ መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ማድረስ፣ መንገድ በመዝጋት የዜጎችን በነጻነት የመንቃሰቀስ መብት በመገደብ እና መንግስታዊ ተቋማትን በማዉደም መንግስትን በዓመጽ ለመጣል ያለመ ነበር፡፡ በዚህም ሂደት ወያኔ እና ኦነግ ሸኔ አሰልጥነዉ በየቦታዉ ያሠማሩዋቸዉ ቅጥረኞች የብሄር እና የሀይማኖት ግጭቶች ለመቀስቀስ፣ የፖለቲካ የአመራሮች ላይ ጥቃት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ፣ የጸጥታ አካላት ካምፖችን በሃይል ለመዉረር ሲሞከሩ እና የጸጥታ አካላት ላይ ቦምብ በመወርወር፣ ተኩስ በመክፈት ጥቃት ለፈመጸም ሞክረዋል፡፡ በዚህ ሂደትም የመንግስት የጸጥታ አካላት እና ፖለቲካ አመራሩ ላይ የህይወት እና የአካል ጉዳት ደርሷል፡፡ እነዚህ የሴራ ፖለቲከኞች ያሰማሩአቸዉ ቡድኖች ሰላማዊ ግለሰቦች ላይ ጥቃት በመፈጸም በአርቲስት ሀጫሉ ግድያ ማግስት የተፈጠረዉን ጉዳት ለመድገም በተጨባጭ ሲንቀሳቀሱ በመታየታቸዉ የጥፋት ተልእኮአቸዉን የሰላማዊ ዜጎችን ህይወት ለማዳን፣ የመንግስት እና የግል ተቋማትን ለመታደግ በማሰብ የጸጥታ ሀይሉ ህግን የማስከበር ተመጣጣኝ እርምጃ ወስዷል፡፡ የጸጥታ አካላት ህግን የማስከበር እርምጃ ባይወሰዱ ኖሮ የከፋ ጉዳትና ቀዉስ ሊከተል እንደሚችል ምንም አያጠራጥርም፡፡

ስለሆነም ሰሞኑን በተደረጉት አደገኛ የወንጀል ሙከራዎች በጸጥታ አካላት የተወሰዱት ህዝቡን የማዳን፣ ህገመንግስቱን የመከላከል፣ የህግ የበላይነት የማስከበር ኃላፊነትን ከተጠያቂነት ማዕቀፍ ጋር በማገናዘብ የተሰወዱ መሆኑን ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡

ህዝባችም በሰላም ወጥቶ የመግባት፣ ሰርቶ መኖር መብቱ እንዲከበርለት የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ በተደጋጋሚ መንግስትን በመጠየቅ ላይ ይገኛል፡፡ መንግስትም የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት የሚደረገዉ ሁሉ አቀፍ ጥረት እንደደተጠበቀ ሆኖ፤ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ፤ የሀገር ግንባታ ህደቱን የማሳለጥና የህዝቦች ነፃነትና እኩልነት የማረጋገጥ ሚናዉን የመወጣት ሙሉ ኃላፊነትና ግዴታ እንዳለበት ሊታወቅ ይገባል፡፡ ወደፊትም መንግስት የሰላማዊ ዜጎቸን ደህንነት የመጠበቅ እና የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራዉን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

እዉነታዉ ይህ ሆኖ ሳለ የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን የጸጥታ አስከባሪ አካላት የህግ የበላይነትን የማስከበር እርምጃ የሚኮንን፣ ሚዛናዊ ያልሆነ እና ከእዉነታ የራቀ በወቀሳ የተሞላ መግለጫ ማዉጣቱ ተገቢነት ሌለዉና ካንድ ኃላፊነት ከሚሰማዉ ተቋም የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ኮሚሽኑ ያወጣዉ መግለጫ የጸጥታ ችግር ተከስቶባቸዉ የነበሩ አካባቢዎቸን እዉነታ ያላገነዘበ፣ ችግር ተከስቶባቸዉ የነበሩ አካባቢዎች በአካል ተገኝቶ ተጨባጭ መረጃዎቸን በማሰባሰብ፣ በየደረጃዉ ያለዉን የመንግስት አመራር በመጠየቅ ሚዛናዊነቱን የጠበቀ መረጃ ማቅረብ ይገባዉ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ትልቅ ሀገራዊ ተቋም እንደመሆኑ እዉነተኛ እና የተጣራ መረጃ ማቅረብ ሲገባዉ በማህበራዊ ሚዲያ የሚነዙ የፕሮፓጋንዳ መልእክቶቸን እንደ መረጃ ምንጭ መጠቀሙ የተሳሳተና መታረም ያለበት ጉዳይ እንደሆነ የክልሉ መንግስት ያምናል፡፡

በዚህ አጋጣሚ ማንኛዉም ኃላፊነት የሚሰማዉ አካል በገለልተኝነት ለማጣራትና የደረሰዉን ጉዳት መነሻና መድረሻ ለማረጋገጥ ከፈለገ መንግስት የተሟላ መረጃ ለመስጠትና የማጣራት ሂደቱን ለመደገፍ፣ የተፈጠሩ ስህተቶች ካሉም ለማረም ዝግጁ መሆኑን ይገልፃል፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
ነሐሴ 2012
ፊንፊኔ

Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top