የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ምክረ-ሃሳብ
~ ተቋሙ በታዋቂ ሰዎች የፍርድ ሂደት ዘገባ ሁሉንም መገናኛ ብዙሀን እንዲሳተፉ ሀሳብ አቀረበ፣
ለኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ጠቅላይ ፍርድ ቤት
አዲስ አበባ
ግልጽ የመንግሥት አሠራርና ተጠያቂነት የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መገለጫ ነው፡፡ ግልጽ የሥልጣን ክፍፍል ባላቸው ዲሞክራሲያዊ ሃገሮች ደግሞ ነጻነቱ የተጠበቀ፣ የግልጽነትና የተጠያቂነት አሠራር የተላበሰ የዳኝነት አካል (ፍርድ ቤት) መኖር የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት እንደ ቁልፍ መሣሪያ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ የፍርድ ቤቶች የግልጽነትና የተጠያቂነት መገለጫ ተደርገው ከሚወሰዱበት መካከል በግልጽ ችሎት ማስቻልና በምክንያት የተደገፈ ውሳኔዎችን ለህዝብ ተደራሽ ማድረግ ይገኝበታል፡፡ ከመዝገብ መክፈት እስከ ፍርድ አፈጻጸም ያለው የፍርድ ቤቶች የዳኝነት አሰጣጥ አሠራር በአደባባይና በግልጽ ችሎት የሚከናወን በመሆኑ ከማንም ተቋም በላይ በባህሪው ለግልጽነትና ተጠያቂነት የተጋለጠ ተቋም ያደርገዋል፡፡
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግሥት በግልጽ እንደተመለከተው ፍርድ ቤቶች ከሶስቱ የመንግሥት አካላት መካከል አንዱ ናቸው፡፡ በዚህም የዜጎች በፍርድ ሊወሰን የሚገባን ጉዳይ ለነጻና ገለልተኛና ፍርድ ቤት የማቅረብና ውሳኔ/ፍርድ የማግኘት መብት እና የፍርድ ቤቶችን የፍርድ ሂደት እና ውሳኔ አስመልክቶ መረጃ የመጠየቅ፣ የማግኘትና የማሰራጨት ነጻነት በህገ-መንግስቱ እውቅና ተሰጥቶታል፡፡እንዲሁም ፍርድ ቤቶች ህግ የመተርጎም ሃላፊነታቸውን (የዳኝነት ሥራ) ከማንኛውም የመንግስት አካል ከማንኛውም ባለስልጣን ይሁን ከማንኛውም ወገን ጫናና ተጽዕኖ ነጻ ሆነው በተከራካሪ ወገኖች የሚነሱ የህግና የፍሬ ነገር ክርክሮችን ህግንና ህግን ብቻ መሠረት አድርገው ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት ለሆነው ህዝብ ግልጽ በሆነ መንገድና በተጠያቂነት መንፈስ የማከናወን ተቋማዊና የሙያ ሃላፊነት አለባቸው፡፡
ከግልጽ የመንግሥት አሠራር እና ተጠያቂነት አንጻርም የፍርድ ቤቶች የፍርድ ሂደት እንዴትና በምን አግባብ ለህዝብ ግልጽ በሆነ መልኩ መከናውን እንዳለበት በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅና በመረጃ ነጻነት አዋጅ እንዲሁም በኢፌዲሪ ወንጀል ህግ ድንጋጌዎች ተመልክቷል፡፡ የተጠርጣሪን የወንጀል ክስና የፍርድ ሂደት አስመልክቶ መረጃ ለህዝብ ይፋ ማድረግ/መግለጽ የወንጀል ክሱን የሚያሰናክል፣ ፍትሕን የሚያጨናግፍ ወይም የፍርድ ሂደቱን ሚዛናዊነት ወይም ገለልተኝነት የሚያዛባ ካልሆነ በስተቀር የወንጀል ክስንና የፍርድ ሂደትን የተመለከተ ማንኛውም መረጃ ለህዝብ ሊቀርብ እንደሚገባ፤ እንዲሁም ለህዝብና ለመንግሥት ሠላምና ጸጥታ አስጊ ወይም ለህዝብ መልካም ጠባይ ወይም ግብረገብነት አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ማንኛውም የፍርድ ሂደትና የህግና የፍሬ ነገር ክርክር ለማንኛውም ሰው ግልጽ በሆነ ችሎት መታየት እንዳለበት ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ. አዋጅ ቁጥር 590/2000 አንቀጽ 21 እና ከፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 26 ድንጋጌዎች መረዳት ይቻላል፡፡
በፍርድ ቤት ሊወሰን የሚገባን የህግና የፍሬ ነገር ክርክርና የፍርድ ሂደትን ለህዝብ ግልጽ በሆነ ችሎት የማስቻል መሠረታዊ ዓላማ በውስን ክልከላ እና በሰፊ ግልጸኝነት መርህ የፍርድ ቤቶችን (የችሎቶችን) የፍርድ ሂደት እና ውሳኔ ወይም የእለት ተዕለት ዉሎ አስመልክቶ ሉዓላዊ የሥልጣን ምንጭ የሆነው ህዝብ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ የማግኘትና የማሰራጨት መብትን ተግባራዊ ማድረግ ሲሆን፤ በዚህም በችሎቱ ነጻ፣ ገለልተኛና ፍትሐዊ የፍርድ ሂደት ላይ የህዝብን የመወሰን አቅም ማጎልበት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የወንጀል ጉዳይን የፍርድ ሂደት በግልጽ ችሎት ማስቻል ወንጀል ያልፈጸሙ ሌሎች ዜጎች ከመሰል የወንጀል ድርጊት እንዲቆጠቡ በማስተማር ረገድ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን በእርግጥም ከማናችንም በላይ የተከበረው ፍ/ቤት ይገነዘበዋል፡፡
የዜጎች ህገ-መንግሥታዊ መብቶችና ጥቅሞች መከበራቸውንና ፍትሐዊ ዳኝነት የማግኘት መብትን ለማረጋገጥ በአጠቃላይ የፍርድ ሂደቱ በግልጽነትና ተጠያቂነት በተሞላበት ሁኔታ ስለመከናወኑ ለህዝብ መረጃ በማቅረብ ረገድ ነጻና ገለልተኛ የመገናኛ ብዙሃን የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ ይሁን እንጂ በግልጽ የፍርድ ቤቶች አሠራር እና ተጠያቂነት ወይም በመረጃ ማግኘትና ማሰራጨት መብት ሽፋን የችሎትን ነጻ፣ ገለልተኛ እና ፍትሐዊ የፍርድ ሂደት ህጋዊ ባልሆነ መንገድ አደጋ ላይ መጣል የተከለከለ ነው፡፡ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የወንጀል ህግ ከአንቀጽ 449 እስከ 451 በግልጽ እንደተመለከተው በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በንግግር፣ በህትመት ወይም በሌላ አድራጎቶች የፍርድ ቤቶችን ወይም የችሎትን የፍርድ ሂደት ማወክ/ማደናቀፍ፣ ነጻነትና ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ማድረግ እና በቀጠሮ ወይም በመሰማት ላይ ባሉ ወይም ውሳኔ ባላገኙ የዳኝነት ጉዳዮች ትክክለኛ ያልሆነ/የተዛባ መረጃን፣ ማስታወሻን፣ ፍሬ ሐሳብን ወይም የተከለከለ ዘገባን ማሰራጨት/መግለጽ የወንጀል ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል ሁሉም የመገናኛ ብዙሃን ይረዱታል፡፡
የአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳን ህልፈት ተከትሎ በደረሰው የህይወትና ንብረት ውድመት ተጠርጥረው ታዋቂ ግለሰቦችንና የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችንና አባላትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች በህግ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውና ጉዳያቸውም በግልጽ የፍርድ ችሎት እየታየ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ ተጠርጣሪዎች የችሎቱን የፍርድ ሂደት (ውሎ) ለመዘገብ ወደ ችሎት አደራሽ እየገቡ ያሉት የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን (ሚዲያዎች) ብቻ ናቸው፡፡ እነሱም በዘገባቸው ለህዝብ ይፋ የሚያደርጉት የፖሊስን የምርመራ ውጤት እና የችሎቱን ትዕዛዝ ብቻ ነው የሚያቀርቡት ሚዛናዊ አይደለም፡፡ በመሆኑም የተወሰኑ ተጠርጣሪዎች የችሎቱን ውሎ እኛ የምንፈልገው ሚዲያ እንዲዘግብ ይደረግልን ሲሉ፤ የተቀሩት ደግሞ የችሎቱን ውሎ ሁሉም ሚዲያ እንዲዘግብ ይፈቀድ አልያም ሁሉም ሚዲያ ይከልከል በማለት ቅሬታቸውን ለችሎቱ ማቅረባቸውን ተገንዝበናል፡፡
የታዋቂውን አርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ ህልፈት ተከትሎ በአንዳንድ ከተሞች ከተደረሰው ጥፋት ጋር በተያያዘ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችና አባላት እንዲሁም በርካታ የመንግስት ሥራ ሃላፊዎች መታሰራቸው ግልጽ ነው፡፡ ድርጊቱም ተራ ወንጀል ሣይሆን በተቀነባበረ መንገድ የሃገርን አንድነትና የህዝቦችን አብሮነት አደጋ ላይ ለመጣል የተፈጸመ ከባድ ወንጀልና ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት መሆኑ በሁሉም የሚዲያ አካላት ማለት ይቻላል በስፋት ወደ ህዝብ ጆሮ እንዲደርስ ተዘግቧል፡፡ እንዲህ ባለ ጊዜ ከፖሊስ የምርመራ ውጤት ጀምሮ ያለውን የፍርድ ሂደት እና የመጨረሻ ውሳኔ በአካል በችሎት ተገኝቶ መከታተል፣ መዘገብ ወይም ሚዛናዊ መረጃ እንዲቀርብለት የሚፈልግ ዜጋ ቁጥር እጅግ በጣም ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡ የተከበረው ፍርድ ቤትም የችሎቱን የፍርድ ሂደት መከታተልና መዘገብ የሚፈልግ ሰው ሁሉ ችሎቱን እንዲታደም ቁርጠኛ ፍላጎት እንዳለው ብንገነዘብም የችሎቱን የፍርድ ሂደት ለመከታተል የሚመጣን ሰው በሙሉ ሊሸከም የሚችል ማስቻያ አዳራሽ አለመኖሩን እንረዳለን፡፡
የችሎት የፍርድ ሂደት (ውሎ) ከሳሽና ተከሳሽ ለችሎት የሚያቀርቡትን በማስረጃ የተደገፈ ክርክር እንዲሁም ዳኞች በችሎት የሚሰጡትን ትዕዛዝ/ውሳኔ ያካትታል፡፡ ሚዛናዊ መረጃ የማግኘትና የማሰራጨት ነጻነት በዘር፣ በቋንቋ፣ በቀለም፣ በዜግነት… ወዘተ ልዩነት ሣይደረግ ለማንኛውም የተፈጥሮና የህግ ሰው የተሰጠ ህገ-መንግሥታዊ መብት በመሆኑ በማስቻያ ቦታ (በችሎት አደራሽ) ጥበት የተነሣ የችሎቱን የፍርድ ሂደት (ውሎ) ለመከታተልና ለመዘገብ ከመጡት ሰዎች መካከል የተወሰኑት እንዲከታተሉ ወይም እንዲዘግቡ ፈቅዶ ሌሎቹን መከልከል በአንድ በኩል በሰዎች መካከል ህጋዊ ያልሆነ ልዩነት እንዲፈጠር ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጥር በሌላ በኩል የችሎቱን የአሠራር ነጻነትና ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ እንዳያስገባ በትኩረት ሊጤን ይገባል፡፡ አቅም በፈቀደ መጠን ሌሎች አማራጭ ዘዴዎችን ሥራ ላይ በማዋል የሰዎችን ሚዛናዊ መረጃ የማግኘትና የማሰራጨት መብትን ተግባራዊ ማድረግ ተገቢ ነው ፡፡
በዚህም ለተከበረው ፍርድ ቤት የሚከተሉትን አማራጭ ምክረ ሐሳቦች እናቀርባለን፡፡
ለለዳኞችና አቃቤ ህጎች እንዲሁም ለተጠርጣሪዎችና ለችሎት ታዳሚዎች ደህንነትና ጥበቃ አመቺ በሆነ ስፍራ ሰፊ አደራሽ የሚገኝ ከሆነ ችሎቱን የፍርድ ሂደት በሰፊ አደራሽ ማስቻል፡፡
የችሎቱን የፍርድ ሂደት ሁሉም የመንግስትና የግል የህትመትና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ አካላት ብቻ እንዲዘግቡት ማድረግና በዘገባዎቻቸው የችሎቱን የምርመራ ሥራ በሚያዉኩ/በሚያደናቅፉ፣ የችሉቱን ነጻነትና ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ በሚያደርጉና ትክክለኛ ያልሆነ/የተዛባ መረጃን ወይም የተከለከለ ዘገባን በሚያሰራጩ የሚዲያ አከላት ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ሚዛናዊ መረጃ ለህዝብ ከማቅረብ አንጻር የተሻለ አማራጭ ይሆናል፡፡
ይህ የማይቻል ከሆነም ደግሞ በአንድ ወገን በመንግስትና በግል የኤሌክተሮኒክስ ሚዲያ አካላት በሌላ ወገን በመንግስትና በግል የህትመት ሚዲያ አካላት መካከል በሚደረግ የጨረታ ውድድር የችሎቱ የፍርድ ሂደት በአሸናፊው የሚዲያ አካል አማካይነት በቀጥታ ስርጭት ለህዝብ እንዲደርስ ማድረግ ሶስተኛ አማራጭ ተደርጎ ቢወሰድ፡፡ በመጨረሻም የችሎቱን የፍርድ ሂደት መከታተል ለሚፈልጉ አካላት በፕላዝማ ቴሌቪዥን ተደራሽ ማድረግ የሚቻልበትን አማራጭ ማየት ቢቻል የሚል ምክረ ሀሳብ አቅርቧል።