ህግና ስርዓት
በኦሮሚያ የደረሰውን ቀውስ አስመልክቶ ከህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የተሰጠ መግለጫ
በኦሮሚያ በአንዳንድ ከተሞች የደረሰውን ቀውስ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የተሰጠ መግለጫ
—
~ ተቋሙ በመግለጫው ያለፈ ትርክት እና ዘረኝነት የፖለቲካ የቅስቀሳ አጀንዳ እንዳይሆን በህግ እንዲታገድ ጠይቋል፣
የኢትዮጵያ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ በተሻሻለው የተቋሙ መቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1142/2011 እና በመገናኛ ብዙሀንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 በተሰጠው ስልጣን መሠረት በህግ የተደነገጉ የዜጎች መብቶች እና ጥቅሞች በአስፈፃሚው አካላት መከበራቸውን እንዲሁም የተሻለ የመንግስት አስተዳደርን ለማስገኘት ነባር ህጎች ወይም አሠራሮች ወይም መመሪያዎች እንዲወጡ ወይም ፖሊሲዎች እንዲቀየሱ የማሳሰብ ስልጣንና ኃላፊነት ተሰጥቶታል።
በዚህ መሠረት በ 2012 የበጀት አመት የመንግስት አስፈፃሚ አካላትን በቁጥጥር በራስ ተነሳሽነት ምርመራ እና በስልታዊ የምርመራ ዘዴ በአመቱ በርካታ ተግባራት አከናውኗል ከመደበኛው ስራ በተጨማሪም ሀገራዊ እና ወቅታዊ ጉዳዮች በሚከሰቱበት ወቅትም የቁጥጥር እና የምርመራ ስራዎች በማካሔድ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ለሚመለከተው የመንግስት አስፈሚ አካላት የተገኙ ግኝቶች ምክረ ሃሳብ ሲሰጥ ቆይቷል።
ለአብነት በአማራ በኦሮሚያ በደቡብ በቤንሻንጉልና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የህዝብ መፈናቀልን አስመልክቶ በቡራዩ በለገጣፎ በወላይታና በአዲስ አበባ በህገ ወጥ ቤቶች ስም የዜጎች መጠለያ ቤቶች ማፍረስ ኢ-ህገመንግስታዊ መሆኑን እንዲሁም የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የወጣውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም በተመለከተ የተደረገውን ቁጥጥር ለአብነት ማንሳት ይቻላል።
በተመሳሳይ የአርቲስት ሀጫሉ ግድያን ተከትሎ በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች በዜጎች ላይ የደረሰውን አሰቃቂ ግድያ እና የንብረት ውድመት አስመልክቶ በኦሮሚያ በተለይ በምእራብ አርሲ ገጠር ወረዳዎች በዝዋይ በአርሲ ነገሌና በሻሸመኔ ከኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ከዋናው መ/ቤትና ከኦሮሚያ ቅርንጫፍ የተውጣጡ የቁጥጥር ቡድን ስምሪት የሰጠ ሲሆን የቁጥጥር አላማውም፤
1. በዜጎች ላይ የደረሰውን አሰቃቂ ግድያ እና የንብረት ውድመት የፀጥታ መዋቅሩ በተለይ የፖሊስ ሀይል ለምን መከላከል አልቻለም ?
2. በደረሰው የዜጎች ህይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት በኋላ የሚመለከታቸው የመንግስት አስፈፃሚ አካላት የህግ የበላይነትን ለማስከበር እየወሰዱ ስላለው እርምጃ
3. ቤተሰባቸው የሞተባቸው ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸውን በመንግስት በኩል እየተደረገላቸው ባለው ጊዚያዊ እርዳታና ድጋፍ እንዲሁም በዘላቂነት ለማቋቋም እየተሰራ ያለው ስራ ከተጎጂ ቤተሰቦች ከመንግስት እና ከጸጥታ መዋቅሩ መረጃ በማሰባሰብ ሪፖርት እንዲያቀርብ በተሰጠው ተልእኮ እና ግኝት መሰረት ተቋሙ በየደረጃው ያለ የመንግስት አስፈጻሚ አካል በቀጣይ ችግሩን በዘላቂነት እና በጊዚያዊነት መፍታት ባለባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ላይ መግለጫ (ወይም press Helease) ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል።
በመሆኑም በምርመራ ከተገኙት ግኝቶች ውስጥ
♦ ከላይ በተጠቀሱት ከተሞች ማለትም በምእራብ አርሲ ገጠር ወረዳዎች በዝዋይ (ባቱ) በአርሲ ነገሌ እና በሻሸመኔ ከተሞች በዜጎች ላይ የደረሰው ግድያ እጅግ አሰቃቂ እና ከአንድ ሰብአዊ ፍጡር ይደረጋል ተብሎ የማይታመን ወንጀል የተፈጸመ መሆኑን መገንዘብ ችለናል
♦ የተገደሉት እና ንብረታቸው የወደማበቸው ዜጎች በአንዳንድ አካባቢዎች የብሄር በአንዳንድ አካባቢዎች ሀይማኖት ተኮር እንዲሁም በትላልቅ ከተሞች የመንግስት ደጋፊዎች ናቸው ተብለው የተለዩ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ መሆኑን
♦ የአካባቢው የጸጥታ ሀይሎችም ይሁኑ የመንግሰትና የፖለቲካ አመራሩ የከፋ ጥፋትና ጉዳት ሳይደረስ መከላከል የሚችልበት ሁኔታ መኖሩን ግን ደግሞ የጸጥታ ሀይሉን በመምራት የአካባቢውን ህብረተሰብ በማስተባበር ለመከላከል ሲደረግ የነበረው ጥረት ደካማ መሆኑን እንዲሁም አንዳድ የፖለቲካ አመራሮችና የጸጥታ አካላት ተባባሪ መሆናቸውን ድርጊቱ በሚፈጸምበት ወቅት ፊት ለፊት ሰው እየሞተና ንብረት እየወደመ በነበረበት ሁኔታ ከፖሊስና ከመከላከያ በኩል ትዕዛዝ ከበላይ የመጠበቅ ሁኔታ እንደነበረ ለመገንዘብ ተችሏል፣
♦ በግድያ እና ንብረት ማውደም ላይ የተሳተፉ ግለሰቦችን የፌደራል እና የክልሉ የፍትህ አካላትና የጸጥታ መዋቅሮች በቅንጅት ወንጀለኞችን ለህግ የማቅረብ ስራ በተጠናከረ መልኩ እየተሰራ መሆኑን ማረጋገጥ ችለናል በቀጣይም መንግስት የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራውን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ስለዚህ የዚህ አይነት ወንጀል ዳግም እንዳይከሰት መንግስት ከአሰቃቂው ከሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ እና ተከትሎ ስለወሰዱት ህጋዊ ፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃዎች ብዙ ሊማሩ እንደሚገባቸው እንጠቁማለን፡፤
♦ በሻሸመኔ ድጋፍና እርዳታን በተመለከተ የአካባቢው አስተዳደር እና ህብረተሰብ አቅሙ በፈቀደ መጠን ድጋፍ የኮቪድ-19 መከላከያ ጨምሮ ሕዝቡን፣ የመንግስት ሠራተኛውን እና ነጋዴውን ባሳተፈ መንገድ ከዞን እስከ ወረዳ ወደ 4,067,780 ብር እንዲሁም ከተቋራጭ በአይነት በማሰባሰብ በድጋፍ አካውንት ተከፍቶ የቤት ግንባታ ስራ መጀመሩን ሆኖም ግን በአርሲ ነገሌ እና ባቱ ከተማ የሚደረገው ድጋፍ በህብረተሰቡ ብቻ መሆኑንና እንዲሁም ከክልልና ከፌደራል መንግስቱ ግን እስካሁን የቀረበ ድጋፍ አለመኖሩን መመልከት ችለናል።
በቀጣይ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት እና በመንግስት አስፈጻሚ አካላት ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባቸው የመፍትሄ ወይም ምከረ ሃሳብ
አንደኛ– መንግስት የህግ የበላይነትን አጠናክሮ እንዲቀጥልና ትላልቅ የአገልግሎትና የማምረቻ እንዱስትሪዎች ጥበቃ እንዲደረግላቸው
በኢፌዲሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 14 ማንኛውም ሰው ሰብኣዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በህይወት የመኖር የአካል ደህንነትና የነጻነት መብት እንዳለው ይደነግጋል ከዚህ በተጨማሪም በህገመንግስቱ አንቀጽ 32 (1) ማናኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በህጋዊ መንገድ ሀገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጪ ዜጋ በመረጠው የሀገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት እንዲሁም በአንቀጽ 40 (1) ማናኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የግል ንብረት ባለቤት መሆኑ ይከበርለታል በአንጻሩ እነዚህን ህገ መንግስታዊ መብቶች የማስከበርና የማክበር የመንግስት ተቀዳሚ ተግባሩ ነው
በህገ መንግስቱ አንቀጽ 77/9 የሚንስትሮች ም/ቤት ህግና ስርአት መከበሩን የማረጋገጥ የክልል መንግስታትም በህገ መንግስቱ 52/ሲ መሰረት የክልላቸውን የፖሊስ ሀይል ያደራጃሉ ይመራሉ ሰላምና ጸጥታ ያስጠብቃሉ በዚህ ረገድ ከአርቲስት ሀጫሉ ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ የተከሰተውን የዜጎችን ህይወት እንዲሁም ሀብትና ንብረት በመከላከልም ይሁን በመጠበቅ ረገድ መንግስትና የጸጥታ መዋቅሩ ይደርስ የነበረውን ከዚህ የከፋ ችግር በመንግስትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ ለማክሸፍ ጥረቱ የሚደነቅ ቢሆንም ተግባርና ሃላፊነቱን አልተወጣም
ስለዚህ በየደረጃው ያለ የመንግስት መዋቅር ሃላፊነታቸውን ባልተወጡ የጸጥታ እንዲሁም የመንግስት አመራሮች ላይ የጀመረውን የተጠያቂነት እና የህግ የበላይነት የማስከበር ሃላፊነቱን አጠናቅሮ እንዲቀጥልበት ስለዚህ በየደረጃው ያለ የመንግስት መዋቅር የህግ የበላይነትን በማስከበር የሀገራችንን ሰላምና ደህንነት የዜጎችን በህይወት የመኖር ሀብት ንብረት አፍርተው የመኖር ህገ መንግስታዊ መብታቸው አስተማማኝ ዋስትና ሊሰጣቸው ይገባል ከዚህ በተጨማሪም የአንድ ሀገር የኢኮኖሚ መሰረት የሚገነባው በሀገር ውስጥ እና ከውጪ በሚመጡ የግል ባለሀብቶች ነው (Private Sector) ለአንድ የግል ባለሀብት ገንዘቡን ኢንቨስት ለማድረግ ሲፈልግ የመጀመሪያው ጥያቄው ሰላምና ጸጥታ ነው ስለዚህ በከፍተኛ ወጪ በርካታ የስራ እድል ያሉ የአገልግሎትና የማምረቻ እንዱስትሪዎች በልዩ እየፈጠሩ ሁኔታ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል፤
ሁለተኛ-የጸጥታና የፖሊስ ተቋማትን ሪፎርም ማድረግ የአለም አቀፍ ተሞክሮዎችም ይሁኑ የተለያዩ ንድፈ ሃሳቦች እንደሚያሳዩን የፖሊስ አደረጃጀት የግድ የመንግስት መዋቅሩን ፌደራላዊ ወይም አሃዳዊ (Unitary) አደረጃጀትን መከተል ግድ አይልም ስለዚህ የጸጥታ መዋቅሩ በተለይ የፖሊስ አሁን ያለውን ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ለውጥ ተከትሎ የዜጎችን ሰላም እና ደህንነት ማስጠበቅ በሚያስችለው ቁመና እና አመለካከት እንደገና የማደራጀት ወይም የሪፎርም ስራ ሊሰራ ይገባል ይህ ሲባል ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ ዴሞክራሲያዊ ስርአት እስከምትሸጋገር ድረስ የፖሊስ አደረጃጀት በየደረጃው ባሉ ሲቪል የመንግስት መዋቅር የሚመሩ ሆነው የዜጎችን ሰላም እና ደህንነት ለማስጠበቅ ስምሪትና ፖሊሲያዊ (Operational) ተልእኮው በተማከለ አደረጃጀት (Centralized) ለፌደራል ፖሊስ ቀጥታ ተጠሪ ሆነው የሚመሩበት ሁኔታ ቢፈጠር ምክረ ሃሳብ እናቀርባለን፤
ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የክልል መንግስታት የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ የራሳቸውን ፖሊስ እንደሚያደራጁ ያስቀምጣል ሆኖም ግን ምን አይነት ፖሊስ ማደራጀት እንዳለባቸው በግልጽ የተቀመጠ ነገር የለም ስለዚህ ክልሎች ሊኖራቸው ስለሚገባ የፖሊስ ሀይል አደረጃጀት የህግ አውጪው የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በህግ ወሰን እንዲያበጅለት እየመከርን አሁን በክልሎች ያለውን የልዩ ሀይል የፌደራል ፖሊስ አካል ሊሆን በሚችልበት ጉዳይ መንግስት ምክክር ቢያደርግበት ምክንያቱም ይህን ሀይል ዴሞክራት አመራሮች ሲኖሩ የክልላቸውን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ሲጠቀሙበት በአንጻሩ አምባገነን የክልል መሪዎችና አመራሮች የዜጎችን የሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት ሲደፈጥጡና ሲጨፈልቁበት ይስተዋላል ይህም ብቻ ሳይሆን በአንዳንድ ክልሎች የግለሰብ በሚመስሉ መልኩ የተከፋፈሉበትን ሁኔታ መታዘብ ይቻላል ለምሳሌ በሶማሌ ክልል የአብዲ ኢሌ እና የሙስጠፌ በኦሮሚያ ክልል አዲሱና ነባር በአማራ ክልል የጄነራል አሳምነው ጦር እየተባለ ባለ ክፍፍል ለህዝብ የወገነ የፖሊስ ሰራዊት መገንባት ስለማይቻል አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጠው መንግስትን እንመክራለን
በአጠቃላይ የፖሊስ ሀይላችን ህግንና ስርአትን የሚያከብር የሚያስከብር የሚጠብቅ ወንጀልን የሚከላከል ወንጀል ተፈጽሞ ሲገኝም እርምጃ የሚወስድ ለዜጎች የመልካም አስተዳደር እና ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ የሚታገል ለህግና ለህገ መንግስቱ ብቻ ተገዢ የሆነ በግልጸኝነት በተጠያቂነት እና በቅንነት ሊሰራ የሚችል እና በቂ ፖሊሳዊ ትጥቅና ቁሳቁስ የተሟላለት ስለሚበላውና ስለሚኖርበት መኖሪያ የማይጨነቅ በሁለንተናዊ መስኩ ብቁ የፖሊስ ሰራዊትና የፖሊስ ተቋም መፍጠር የሚያስችል የሪፎርም ስራ ያስፈልገዋል ይህን ተቋም መልሶ ለማደራጀትና ለማብቃት በሰአታት እድሜ የሚወድመውን ሀብትና ንብረት የሚጠፋውን የሰው ህይወት እና በሙስና የሚባክነውን ሩብ ሀብት ያህል እንኳን የመንግስትን ካዝና አይጎዳም፤
ሶስተኛ– ያለፈ ትርክት እና ዘረኝነት የፖለቲካ የቅስቀሳ አጀንዳ እንዳይሆን በህግ እንዲታገዱ በተመለከተ
የባለፉትን 29 አመታት ዘር እና ሀይማኖት ተኮር የሆኑ ግጭቶች ስንመለከት አንዱም ግጭት የአካባቢውን ህዝብ የወከለ ግጭት አይደለም። ይልቁን ጥቂት ተምረናል ወይም ፖለቲከኛ ነን የሚሉ የህዝቡ አብሮ እና ተጋምዶ የመኖር እሴቱን ያልተረዱ አንዱን ብሄር ጠላት ሌላውን ብሄር ወዳጅ አንዱን መልአክ አንደኛውን ሰይጣን አንዱን ጨቋኝ ሌላውን ተጨቋኝ በማድረግ እና በመከፋፈል በአጭር ጊዜ በአነስተኛ ወጪ የፖለቲካ ተከታዮችን ለማሰባሰብ እንዲሁም ሴረኛ ፖለቲከኞች ከፋፍሎ ለመግዛት እንዲያመቻቸው የሚቀይሱት ስትራቴጂ ሲሆን ተከታይን በአስተሳሰብ ወይም በርእዮተ አለም ማሰባሰብ የሚጠይቀው ወጪ ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ ገዢ ሃሳብ በማመንጨት በርካታ ተከታይ ለማፍራት አቅምና ብቃት የሚጠይቅ በመሆኑ ያለፉ ትርክቶች ተከታይ የማፍራት የፖለቲካችን ባህሪ ከሆነ ውሎ ያደረ ጉዳይ ነው።
ስለዚህ ያለፈ ታሪክ ከበጎው ትምህርት ልንወስድ ከስህተታችን መማር እንድንችል ካልሆነ ዛሬ ላይ ለመገዳደል ምክንያት ሊሆን አይገባም ከአንድ ሰብአዊ ፍጥረት የሚጠበቅ ጉዳይም ስለዚህ አርቲስት ሀጫሉ እንደተናገረው ዘርንና ዘረኝነትን የሚለይ የፖለቲካ ባህል ልንገነባ ይገባናል።
በዚህ ረገድ አብዛኛውን የአማራ እና የኦሮሞን ህዝቦች ለማጋጨት እንዲሁም አማራውን ከሌሎች ብሄሮች ጋር ለማጋጨት በመሳሪያነት ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው ከአጼ ሚኒልክ ጋር ተያይዘው የሚነሱት ትርክቶች ናቸው ከሀጫሉ ግድያ በኋላም አንዳንድ የኢትዮጵያን መበተን የሚመኙ ሚዲያዎች በከፍተኛ ሁኔታ የፕሮፖጋንዳ ማእከላቸው በማድረግ ምንም የማያውቀውን ዜጋ የጥቃት ሰለባ አድርጓል ባለፉት ስርአታትም ይሁን ወደፊት መሪዎች ጥፋት ሊያጠፉ ይችላሉ ስለዚህ ሊጠየቁ የሚገባቸው ራሳቸው መሪዎቹ እንጂ የወጡበት ብሄር ወይም ማህበረሰብ ሊጠየቅ አይገባም ስለዚህ ከሩዋንዳ የዘር ፍጅት ትምህርት ወስደን በቀጣይ የሚደረጉ የፖለቲካ ክርክሮችም ይሁን ውይይቶች ያለፈ ትርክትን እና ዘርን መሠረት ማድረግ የሚከለክል ህግ የህግ አውጪው ወይም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህግ እንዲያወጣ ምክረሃሳብ እናቀርባለን።
አራተኛ– የመረጃ ነጻነትና ሚዲያዎችን በተመለከተ
በሃገራችን በኢፌዲሪ ህገ-መንግሥት የተረጋገጡትን የህዝብ ተሣትፎና የሥልጣን ባለቤትነት እንዲሁም ግልጸኝነት፣ ተጠያቂነትና ውጤታማ የመንግሥት አሠራርና የመልካም አስተዳደር እሴቶችን ለማዳበርና ይበልጥ ለማጠናከር በተለይም የህዝብን ጥቅም የሚመለከቱ መረጃ፣ ሐሳብና አመለካከት ይፋ ወጥተው ዜጎች እንዲወያዩባቸውና የዜጎችን በመረጃ ላይ ተመስርቶ የመወሰን አቅምና ባህል ለማዳበር/ለማጎልበት የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነጻነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 መታወጁ ለማንም ግልጽ ነው። በዚህም የሃገርና የህዝብን ጥቅምና መብት ለመጠበቅ ሲባል እንዳይገለጹ ከተከለከሉት መረጃዎች በስተቀር መንግሥት የተለያየ ዘዴን በመጠቀም ማንኛውንም መረጃ ለህዝብ የማቅረብ/ የመስጠት ግዴታ አለበት።
ከዚህ አንጻር መንግሥት የተፈጥሮ ወይም ሰው ሰራሽ አደጋ/ክስተት ሲያጋጥምና በዚህም የተነሣ በህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ሊደርስ የሚችል መሆኑን በተገነዘበ ጊዜ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመከላከል/ለመቆጣጠር ወይም የጉዳቱን መጠን ለመቀነስ ይረዳ ዘንድ ስለአደጋው/ክስተቱ እና አደጋውን ተከትሎ ሊወሰድ ስለሚገባው ጥንቃቄ አስመልክቶ መረጃ አስቀድሞ ለህዝብ የመስጠት ሃላፊነት አለበት። ይሁን እንጂ የታዋቂውን አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሣን አሰቃቂ ግድያ ተከትሎ በአንዳንድ የሃገራችን ከተሞች የአደባባይ ላይ የተቃውሞ ሰልፍ መኖሩን ሣያውቁ ዜጎች አገር ሠላም ነው ብለው እንደ ወትሮው ሁሉ የእለት ተዕለት ተግባራቸውን ለማከናወን በወጡበት በድንገት የደረሰ ጉዳት መሆኑን ስንመለከት በእርግጥም ዜጎችን ድርስ ከሆነ አደጋ ለመከላከል መንግስት ለዜጎቹ መረጃ የመስጠት ሃላፊነቱን ተወጥቷል ወይ የሚለው መሠረታዊ ጉዳይ ጥያቄ የሚያስነሣ ጉዳይ ነው።
ስለዚህ የሚመለከተው የመንግስት አስፈጻሚ አካል ከሁኔታዎች ጋር የተናበበ እና ተተንባይ (Predicatable) የሆነ የጸጥታ ወይም የሰላም ችግር ሊያጋጥም እንደሚችል ሲገምት አስቀድሞ ዜጎች እንዲጠነቀቁ መረጃ ሊሰጥ ይገባል ፤ በሃሳብ ነጻነት ዜጎች መረጃ በማግኘት እና የዜጎችን ሰላም እና ደህንነት ስጋት ላይ የጣሉና በሚጥሉ የሚዲያ ተቋማትን በተመለከተ ዜጎች የሃሳብ ነጻነትን በህገ መንግስቱ አንቀጽ 29/2 ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እንዳለው ይደነግጋል የዚህ ድንጋጌ መሰረታዊ መርህ በአንድ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ህዝቡ የፖለቲካ ሉኣላዊ የስልጣን ባለቤት ነው ተብሎ ስለሚታመንና መንግስትም የህዝብን ፍላጎት መሰረት አድርጎ እንዲሰራና መንግስትም በሰራው ልክ ዜጎች መጠየቅ እንዲችሉ ታሳቢ ያደረገ የዜጎች መብት ነው።
በዚህ ረገድ በመንግስት በኩል የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ዜጎችም ሃሳባቸውን በነጻነት እንዲለማመዱ መደረጉ እስከውስንነቱ መንግስት ሊበረታታ ይገባዋል፤
የዜጎች መረጃ የማግኘት መብትን በተመለከተ ከማንኛውም መንግስታዊ አካል ዜጎች መረጃን የመጠየቅ የማግኘት እና የማስተላለፍ መብት እንዳላቸው ህገ መንግስቱና የመገናኛ ብዙሀንና የመረጃ ነጻነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 ያዛል።
ሆኖም ግን ዜጎች በተለይ የመገናኛ ብዙሀንና ጋዜጠኞች አሁንም መረጃ ለማግኘት ያለው ሳንካ ከፍተኛ ነው። ከዚህም አለፍ ሲል በጸጥታ አካሉ ጋዜጠኛን ለተወሰነ ደቂቃ የማሰርና ካሜራ ቀምቶ መረጃ እንዲጠፋ የማድረግ ዝንባሌ ኢ-ህገመንግስታዊ ነው ብሎ ተቋማችን ያምናል ስለዚህ አንዳንድ የመንግስት አስፈጻሚ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እናሳስባለን።
በመጨረሻም የሃሳብ ነጻነት እና መረጃ የማግኘት የመጠየቅ እና የማስተላለፍ መብት እንዳለን ሁሉ በህገ መንግስቱ 24/1 ማንኛውም ሰው ሰብኣዊ ክብሩና መልካም ስሙ የመከበር መብት አለው (Honor and Dignity) በተጨማሪም በመገናኛ ብዙሀንና የመረጃ ነጻነት አዋጅ 590/2000 የሀገር ወይም የብሄራዊ ደህንነትን የሚጎዳ የህዝብን ሰላምና ደህንነት ስጋት የሚጥል የህዝብ ጤና እና ሞራል የሚጎዱ መረጃዎችን ማስተላለፍ እንደማይቻል ተደንግጓል።በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ይህን ህግ ተላልፈው በተገኙ የሚዲያ ተቋማት ላይ የወሰደው እርምጃ ተገቢ ነው ብለን እናምናለን።