የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ የስራ አስፈጻሚ አባላት በባቱ እና አዳሚ ቱሉ ከተሞች ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች አጽናኑ
***
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በኦሮሚያ ክልል ባሳለፍነው ወር በተከሰተው ሁከትና ግርግር ሳቢያ የቤተሰብ ሕይወት ያለፈባቸውንና የንብረት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች አጽናንተዋል።
በዚሁ ወቅት ክቡሩ የሰውን ልጅ መግደልና ጥሮ ግሮ ያፈራውን ሀብት ማውደም በማንኛውም እምነት ተቀባይነት የሌለው ተግባር መሆኑንም ጠቅሰዋል።
”ኢትዮጵያውያን ተዋደንና ተከባብረን ለረጅም ዓመታት እንደኖርን ሁሉ ለወደፊትም ያለ እምነትና ብሔር ልዩነት አብረን ልንኖር ይገባል” ሲሉም መክረዋል።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ የሃይማኖት አባቶች ጉዞ ዋና ዓላማ ተጎጂዎችን መጎብኘትና ካሉበት ስሜት እንዲወጡ ለማጽናናት መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ከጉብኝቱ በኋላ ሕዝቡን በማስተባበር የበኩሉን ድጋፍ ለማድረግ መሆኑን ጠቁመዋል።
የተፈጸመው ድርጊት በሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ዘንድ ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም ተናግረዋል።
በርካታ ሰዎች አማኝ በሆኑባት አገር እንደዚህ አይነት እኩይ ተግባር መፈጸሙ የሃይማኖት ተቋማት ትውልድን በሥነ ምግባር የማነጽ ሥራቸውን በአግባቡ እንዳልተወጡ እንደሚያሳይ ገልጸው፤ተቋማቱ ትውልዱን በሥነ ምግባር ቀርጸው ሊያሳድጉ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ድርጊቱ ዳግም እንዳይፈጸም የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ሕዝቡን የማወያየትና የማግባባት ሥራ እንደሚሰራ ተናግረው፤ ለተጎጂዎች መንግሥትና ኅብረተሰቡ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የተወከሉት ንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃ እንዳሉት፤ የተፈጸመው ድርጊት በአማኞች ዘንድ የተወገዘ ነው።
ተጎጂዎቹ ትናንት በብሩህ አዕምሮ ሰርተው ሀብት እንዳፈሩት ሁሉ ዛሬም በዚህ እኩይ ተግባር ሳይደናገጡ ተግተው መሥራት እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
ከኢትዮጵያ እስልምና ምክር ቤት የተወከሉት ሼህ መሀመድ ሲራጅ ”ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ ልንደጋገፍ ይገባል እንጂ መጠፋፋቱ የማይበጅ ነው” ብለዋል።
ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የተወከሉት አባ ገብርኤል ወልደሃና በበኩላቸው ”እንደዚህ ዓይነት ተግባር የፈጸሙ ሰዎች ከሰው ብቻ ሳይሆን ከፈጣሪያቸውም የተጣሉ ናቸው” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከተጎጂዎች ጎን ሆኖ አለኝታነቱን ሊገልጽላቸው እንደሚገባም ገልጸዋል።
“የሰው ልጅ በራሱ ላይ እንዲደረግ የማይፈልገውን ተግባር በሌሎች ላይ መፈጸም አይገባውም” ያሉት ደግሞ ከኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ የተወከሉት ቄስ ዶክተር ዋቅሹም ሥዩም ናቸው።
በባቱ ከተማ ባሳለፍነው ወር በተከሰተው ሁከትና ግርግር ሳቢያ የአንድ ሰው ሕይወት ሲያልፍ በርካታ ንብረቶች ላይ ጉዳት ደርሷል።
በተያያዘም በአዳሚ ቱሉ ከተማ በአንድ ቤት ውስጥ የአምስት ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል።
የሃይማኖት አባቶቹ ጉብኝት ዛሬም የሚቀጥል ሲሆን በሻሸመኔና በአርሲ ነገሌ ከተሞች ተጎጂዎችን የሚያጽናኑ ይሆናል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።