Connect with us

26 የዎላይታ ዞን ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች ታሰሩ

26 የዎላይታ ዞን ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች ታሰሩ
Photo: Social Media

ህግና ስርዓት

26 የዎላይታ ዞን ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች ታሰሩ

የደቡብ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ << አገርን ለማፍረስ እየሰሩ ከሚገኙ ሀይሎች ጋር አብረዋል >> ያላቸውን 26 የዎላይታ ዞን ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎችን አሰረ።

አመራሮቹና ባለሙያዎቹ ትናንት ከሰዓት በኋላ 10 ሰዓት አካባቢ የተያዙት በዞኑ ሁከት ለመቀስቀስ በዝግጅት ላይ ስለመሆናቸው መረጃ በመገኘቱ ነው ተብሏል።

የደቡብ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አለማየሁና ባውዲ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ነብዩ ኢሳያስ አመራሮቹና ባለሙያዎቹ ኢመደበኛና ህገ ወጥ ቡድኖችን በማደራጀት የጥፋት ተግባር ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ ነበር ሲሉ ትናንት ምሽት የክልሉ መንግስት ንብረት ለሆነው የደቡብ ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

ባለስልጣናቱ አያይዘውም << አመራሮቹና ባለሙያዎቹ የአገሪቱን ህልውና አደጋ ውስጥ ለመክተት እየሰሩ ከሚገኙት ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት ) እና ኦነግ ሸኔ ከተባሉ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው በመረጃ አረጋግጠናል። አመራሮቹ ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታረሙ በተደጋጋሚ ቢነገራቸውም ሊመለሱ ባለመቻላቸው በህግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል። በቁጥጥር ስር የማዋሉ ስራ የተከናወነው ከብሄራዊ የመረጃ ድህንነትና ከአገር መከላከያ ሰራዊት የኮማንድ ፖስት ጋር በመቀናጀት ነው።

ሂደቱ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ነው የተከናወነው። እስከአሁንም በአካባቢው የተፈጠረ ምንም ነገር የለም >> ብለዋል።
የክልሉ የጸጥታ ባለስልጣናት በዚሁ መግለጫቸው በቀጥጥር ስር አውለናል ያሏቸውን ተጠርጣሪዎች << የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች >> ከማለት በስተቀር በስም አልጠቀሱም። ዶቼ ቨለ ( DW ) ከታማኝ ምንጮች እንዳረጋገጠው ታስረዋል ከተባሉት አመራሮች መካከል የዎላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳጋቶ ኪምቤ እና የበታች ሹማምንቶቻቸው ይገኙበታል።

ዶቼ ቨለ ( DW ) በስልክ ያነጋገራቸውና ስሜ ይቅር ያሉ አንድ የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪ ትናንት በከተማው ጉተራ ተብሎ በሚጠራው አዳራሽ ተሰብስበው የነበሩ የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች በጸጥታ አባላት ተይዘዋል የሚል ወሬ መሰራጨቱን ተከተሎ ምሽቱን በሁኔታው የተቆጡ ወጣቶች ጎዳናዎች ላይ ተሰብስበው መመልከታቸውን ተናግረዋል። ከቀኑ 11 ሰዓት እስከ ምሽቱ ሶስት ሰዓት በከተማው የተለያዩ አካባቢዎች የተኩስ ድምፅ ሲሰማ እንደነበር የገለጹት የአይን አማኙየተኩስ ድምፅ ዛሬ ከጠዋት ጀምሮ አልፎ አልፎ እየተሰማ ይገኛል ብለዋል።

በደቡብ ክልል በክልል መዋቅር ለመደራጀት ጥያቄ ካቀረቡት በርካታ የዞን መስተዳድሮች መካከል አንዱ የሆነው የዎላይታ ዞን ምክር ቤት ጥያቄዬ በክልል ደረጃ ሊታይልኝ አልቻለም በሚል ጉዳዩን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በይግባኝ በማቅረብ መላሽ እየጠበቀ ይገኛል።

የወላይታ ዞንን በመወከል በደቡብ ክልል ምክር ቤት መቀመጫ ያላቸው 38 የብሄሩ አባላት ምክር ቤቱ ለጥያቄያችን ተገቢውን ምላሽ አልሰጠም በሚል በቅርቡ ራሳቸውን ከአባልነት ማግለላቸው ይታወቃል ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የደቡብ ክልል የዞንና የወረዳ አመራሮች በአክቲቪስቶች ተጠልፈዋል ይገኛሉ በማለት አመራሮቹ ህዝብን ሊያጋጩ ከሚችሉ አንቅስቃሴዎች እንዲታቀቡ ሲሉ በቅርቡ አሳስበው እንደነበር ይታወሳል።
#DW

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top