Connect with us

ፍ/ቤቱ የታችኛውን ፍ/ቤት ውሳኔ በማፅናት የኢዜማ አባሏን ዋስትና ፈቀደ

ፍ/ቤቱ የታችኛውን ፍ/ቤት ውሳኔ በማፅናት የኢዜማ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባሏን ዋስትና ፈቀደ
Photo: Facebook

ዜና

ፍ/ቤቱ የታችኛውን ፍ/ቤት ውሳኔ በማፅናት የኢዜማ አባሏን ዋስትና ፈቀደ

ከድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ አምስት ኪሎ አካባቢ ከ70 እስከ 100 የሚደርሱ ወጣቶችን በማደራጀት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ በማድረግ ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ የነበሩት የኢዜማ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሒሩት ክፍሌ፣ በስድስት ሺሕ ብር ዋስ እንዲለቀቁ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ማክሰኞ ሐምሌ 28 ቀን 2012 ዓ.ም. ባስቻለው ችሎት፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ አባል በተሰጠው ስምንት የምርመራ ቀናት የሠራውን ገልጿል፡፡ በዚህም የምስክሮችን ቃል መቀበሉን፣ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች የምርመራ ውጤት የሰነድ ማስረጃ መቀበሉን፣ ጉዳት ለደረሰባቸው ድርጅቶች ደብዳቤ መጻፉን፣ ተጨማሪ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ እየሠራ መሆኑን አስረድቷል፡፡

ቀሪ ምስክሮችን መስማት፣ የደረሰውን ጉዳት እንዲገልጹለት ደብዳቤ የጻፈውን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ክፍላተ ከተሞች ምላሽ መሰብሰብ፣ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ምስክርነት ቃል መቀበል እንደሚቀረው በማስረዳት ተጨማሪ 14 የምርመራ ቀናት እንዲፈቀዱለት ጠይቋል፡፡

የሒሩት ጠበቆች የመርማሪ ፖሊሱን ሪፖርት በመቃወም ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ መርማሪው ቀደም ብሎ በነበረው የጊዜ ቀጠሮ በተሰጠው ትዕዛዝ ምርመራውን አጠናቆ እንዲቀርብ የመጨረሻ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል፡፡ ምርመራው አንድ ወር እንዳለፈው፣ ደንበኛቸው ሳይታሰሩ 14 ቀናት ምርመራ ማድረጉንና ለሦስት ተከታታይ ቀጠሮ ተጨማሪ ጊዜ እንደተሰጠው በማስታወስ፣ ይህ የተጠርጣሪዋን ሰብዓዊ መብት የሚነካ፣ ከጤናቸውና ኮሮና እያሳደረው ካለው ተፅዕኖ አንፃር ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡ ደብዳቤ ለመቀበል የደንበኛቸው መታሰር የሚፈይደው ነገር እንደሌለ ጠቁመው፣ ፍርድ ቤቱ መዝገቡን ዓይቶና መርምሮ በመዝጋት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን በማክበር እንዲዘጋላቸው ጠይቀዋል፡፡

ፖሊስ በሰጠው ምላሽ ሒሩት የተጠረጠሩበት ወንጀል የሰው ሕይወት የጠፋበት፣ በርካታ ንብረት የወደመበትና ሰፊ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑን አስረድቶ፣ ዋስትናው ውድቅ ተደርጎ የጠየቀው ጊዜ እንዲፈቀድለት አመልክቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከመረመረ በኋላ በሰጠው ትዕዛዝ ተጠርጣሪዋ አድርሰውታል ከተባለው ጉዳት አንፃር የሰውም ሆነ የሰነድ በርካታ ማስረጃ ማሰባሰብ መቻሉን፣ የምርመራ መዝገቡ እንደሚያሳይ ገልጿል፡፡ ነገር ግን ተጠርጣሪዋ በዋስ ቢወጡ ምስክሮችን ሊያባብሉና ማስረጃ ሊያሸሹ ይችላሉ የሚለው አሳማኝ አለመሆኑን ጠቁሞ፣ የተሰጠው ጊዜ በቂ በመሆኑ ተጠርጣሪዋ የስድስት ሺሕ ብር ዋስ አስይዘው ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ በመስጠት መዝገቡን ዘግቷል፡፡

ሆኖም ፖሊስ ይግባኝ እጠይቃለሁ በሚል ወ/ሮ ሒሩትን አስሮ በማቆየት በዛሬው እለት ፍ/ቤት አቅርቧቸዋል።

የፖሊስን የይግባኝ አቤቱታ የሰማው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት ትላንት የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ በማፅናት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የሙያ ማኅበራት ተጠሪ ሂሩት ክፍሌ የዋስትና መብታቸው ተከብሮ ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ ፖሊስ የስር ፍርድ ቤት ትዕዛዝን ሳይፈጸም ተጠርጣሪዎችን በእስር አቆይቶ ይግባኝ መጠየቁ ወንጀል ነው ሲል ለፖሊስ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። (ምንጭ ሪፖርተር፣ ኢዜማ)

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top