Connect with us

የነጃዋር መሐመድ እና የቤተሰቦቻቸው የባንክ አካውንት መታገዱ ተሰማ

ጃዋር መሐመድ እና በቀለ ገርባ፡ የታሳሪዎችና የቤተሰቦቻቸው የባንክ አካውንት መታገዱ ተሰማ
Photo: Social Media

ህግና ስርዓት

የነጃዋር መሐመድ እና የቤተሰቦቻቸው የባንክ አካውንት መታገዱ ተሰማ

የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች እና የቤተሰብ አባላት የባንክ አካውንት እንዲታገድ በመደረጉ የቤተሰብ አባሎቻቸው ገንዘብ ማንቀሳቀስ ባለመቻላቸው ለችግር መጋለጣቸውን ለቢቢሲ ተናገሩ።

የተጠርጣሪዎች ጠበቃ በበኩላቸው የባንክ አካውንቶቹ እንዳይንቀሳቀሱ የተደረገው ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ነው በሚል ቅሬታ አሰምተዋል።

የባንክ አካውንታቸው እንዳይንቀሳቀስ ከተደረገባቸው ሰዎች መካከል የአቶ ጃዋር መሐመድና ቤተሰባቸው፣ የአቶ በቀለ ገርባ እና የቤተሰባቸው እንዲሁም የጋዜጠኛ መለሰ ዲሪብሳ እና ባለቤቱ እንደሚገኙበት ተገልጿል።

የአቶ ጃዋር መሐመድ እህት የሆነችው ራዲያ ሲራጅ፤ የእሷን ጨምሮ የአምስተ ወንድሞቿ የባንክ አካውንቶች እንዳይንቀሳቀስ መደረጉን ለቢቢሲ ተናግራለች።

“አጠቃላይ የስድስት ሰዎች አካውንትን ነው የተዘጋው። የእኔንም አካውንት ዘግቷል። የአዋሽ እና የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ አካውንቶች ናቸው የተዘጉት። ለምን እንደተዘጋ ስንጠይቃቸው እኛ የምናውቀው ነገር የለም፤ ስልክ ተደውሎ ነው ዝጉ የተባልነው አሉን። የሚያደርጉትን ያድርጉት ብለን ትተነዋል” ብላለች።

በተመሳሳይ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋዜጠኛ መለሰ ዲሪብሳ ባለቤት የሆነችው ታደለች መርጋ፤ የእርሷ እና የባለቤቷ የቁጠባ ሂሳብ እንዳይንቀሳቀስ መደረጉን ለቢቢሲ ተናግራለች።

ታደለች በትናንትናው እለት የቤት ኪራይ ለመክፈል በማሰብ ገንዘብ ለማውጣት ወደ ባንክ መሄዷን ጠቅሳ ማውጣት እንደማትችል ከባንኩ ሠራተኞች ሲነገራት ለምን እንደሆነ መጠየቋን ገልጻለች።

“የባንክ ቤቱ ሠራተኞች አካውንቱ ታግዷል የሚል መልስ ሰጥተውኛል” የምትለው ታደለች “ምንም ማድረግ ስለማልችል ወደ ቤቴ ባዶ እጄን ተመለስኩ” በማለት ለቢቢሲ ተናግራለች።

ታደለች የባለቤቷን የቁጠባ ሂሳብንም ስትጠይቅ መታገዱን እንደተናገራት ጨምራ አስረድታለች።

በአካውንቱ ውስጥ ያለው ጥቂት ገንዘብ ነው የምትለው ታደለች “ሰርቼ ያመጣሁት ደሞዜ እንጂ ከየት እናመጣለን?” ስትል ትጠይቃለች።

ስለጉዳዩ ለጠበቃው መንገሯን በመግለጽ በዚህ የተነሳ የቤት ኪራይ ለመክፈል እንዳልቻለች ሁለት ልጆቿም ሆኑ እርሷ ችግር ውስጥ መሆናቸውን ትናገራለች።

ከዚህ በተጨማሪ የአቶ በቀለ ገርባ፣ የአቶ በቀለ ገርባ ባለቤት እና የልጃቸው አካውንት እንዲዘጋ መደረጉን የአቶ በቀለ ባለቤት ወ/ሮ ሃና ረገሳ ባለፈው ሰኞ ተናግረዋል። አካውንቶቹም እስካሁን ዝግ ሆነው እንደሚገኙም ጨምረው አረጋግጠዋል።

የእነ አቶ ጃዋር እና አብረዋቸው የታስሩ ሰዎች ጠበቃ የሆኑት አቶ ቱሊ ባይሳ የደንበኞቻቸው እና የቤተሰብ አባላቶች የባንክ አካውንቶችን ፍርድ ቤት እንዳላገዳቸው ይናገራሉ።

ጠበቃው አክለውም የኦኤምኤን ጋዜጠኞችና ሠራተኞች፣ የአቶ ጃዋር መሐመድና የቤተሰባቸው እንዲሁም የአቶ በቀለና የቤተሰባቸው የቁጠባ ሂሳቦች በሙሉ መታገዳቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ስለ ጉዳዩ የሰሙት በቅርብመሆኑን የገለፁት አቶ ቱሊ፤ አገደ የተባለውን አካል አጣርተን ቅሬታ ለማቅረብ እየተዘጋጀን ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“በፊት ቢሆን በጸረ ሙስና ሕጉ መሰረት አቃቤ ሕግም ማገድ ይቻል ነበር። አሁን ግን የአንድን ሰው አካውንት ማገድ ያለበት እኔ እስከማቀው ድረስ ፍርድ ቤት ነው” በማለት በፍርድ ቤት ታግዶ ቢሆን ይሰሙ እንደነበር ይናገራሉ።

በዚህ ፋይል ላይ ምንም የተነገረን ነገር የለም። በተለይ የአቶ በቀለ ገርባን ጠይቀው ፍርድ ቤቱ እንደማያውቅ እንደነገራቸው ገልጸዋል።

በጉዳዩ ላይ የመርማሪ ፖሊስን እና የጠቅላይ አቃቤ ሕግን ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

የፌደራል ፖሊስ ቃል አቀባይ ጄይላን አብዲ፤ በጉዳዩ ላይ አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ ጠቅሰው የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቃል አቀባይን እንድንጠይቅ ነግረውናል።

የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቃል አባይ ኮማንደር ናደው በበኩላቸው የሥራ እረፍት ላይ መሆናቸውን በመጥቀስ ማብራሪያ መስጠት እንደማይችሉ ገልጸዋል።

የሚመለከታቸው የጠቅላይ አቃቤ ሕግ ባልደረቦች የእጅ ስልካቸው መነሳት ባለመቻሉ አስተያታቸውን ማግኘት አልቻልንም።

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top