Connect with us

ዛሬ የዓለም ሬንጀር ቀን ነው

ዛሬ የዓለም ሬንጀር ቀን ነው፡፡ እናንተ የዱር ሕይወት ጀግኖች ከጎናችሁ ነን፡፡

ህግና ስርዓት

ዛሬ የዓለም ሬንጀር ቀን ነው

ዛሬ የዓለም ሬንጀር ቀን ነው፡፡ እናንተ የዱር ሕይወት ጀግኖች ከጎናችሁ ነን፡፡
በዓሉን በዱር ለምታሳልፉ ሬንጀር ሙስሊሞች እንኳን አደረሳችሁ፡፡
****
(ከሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ)
የዓለም ሬንጀር ቀን ነው፡፡ እነኚህ ቡራቡሬ ለባሾች ሰው ለማጥቃት ሳይሆን ሰው ለማዳን የታጠቁ ናቸው፡፡ እነኚህ የዱር ህይወት ጀግኖች የትግል ምክንያታቸው አንዱን ሀገር ወርሮ ለሌላው ለማስገበር ሳይሆን ምድር ከነ ክብሯ ትኖር ዘንድ ስለ ፍጥረት ግድ ብሏቸው ነው፡፡

ዛሬ አረፋ ነው፡፡ ብዙ የማውቃቸው ሙስሊም ሬንጀሮች እንዲህ ባለው የክት በዓል እንኳን ከዱሩ አይርቁም፡፡ ስለ ተፈጥሮ ፍቅር የከተማው ጩኽት ሳያጓጓቸው በስፍራቸው ናቸው፡፡ ከገራሌ እስከ ሀላይደጌ አሰቦት፣ ከአዋሽ እስከ ባቢሌ በሁሉም አቅጣጫ ያላችሁ እንኳን አደረሳችሁ፡፡

ዓለም ዛሬ ከዱር ህይወት ጠባቂዎቹ ሬንጀሮች ጎን እቆማለሁ ብሎ ቃል የሚገባበት ቀን ነው፡፡ የዓለም ሬንጀሮች እንደ ሀገራቸው ስልጣኔ ደረጃና እንደ ህዝባቸው እውቀት መጠን በዓሉ በተለያየ መልኩ ያከብሩታል፡፡ የኔ ሀገር ሬንጀር እንደሚጠብቀው ዱር እንስሳ ራሱም እየታደነ ይገደላል፡፡ በእሱ ሞት ሚስት ልጆች ታቅፋ ሜዳ ትወድቃለች፡፡ ቢገድልም ቢሞትም መከራው ያው ነው፡፡ ያም ሆኖ “እኔ ሬንጀር ነኝ” በሚል የክብር ቃል ስሙን ጠርቶ ከሚከበረው የዓለም ሬንጀር ቀን ጋር ቀናቸውን ያከብራሉ፡፡ አንድ ቀን ኢትዮጵያውያን በሙሉ “እኛም ሬንጀር ነን” የሚሉበት ቀን ሩቅ አይሆንም፡፡

ሀገሩ በራስ ወዳድነት በሰከረበት በዚህ ጨለማ ዘመን ሰው በወንድሙ ላይ እጁን በሚያነሳበት በዚህ አስፈሪ ጊዜ ስለተፈጥሮ ኖሮ ስለተፈጥሮ መሞት ጸጋ ብቻ ሳይሆን ጽድቅም ነው፡፡ ይህ ቀን የሬንጀር ቀን እንበለው እንጂ የጽድቅም ቀን ነው፡፡ የጻድቃንም፤

በኢትዮጵያ ሰማይ የእናንተ ጸሐይ እንድትወጣ እመኛለሁ፡፡ ድካማችሁ ፍሬ የሚያፈራበት፤ ሞታችሁ ሰው የሚያኖርበት ውለታችሁ ለልጅ ልጆቻችሁ የሚመለስበት ቀን እንዲመጣ እመኛለሁ፡፡ እስከዛው ስቆቃችሁን እጋራለሁ፡፡ በየቀኑ ከተፈጥሮ ሀብት ውድመት ጋር አብሮ ስለሚወድመው ስሜታችሁ፤ አብሮ ስለሚጨፈጨፈው ቀልባችሁ አብሮ ስለሚሞተው ህይወታችሁ አዝናለሁ፡፡ እናንተ ቀናችሁ ዛሬ ብቻ አይደለም፡፡ አመቱን ሙሉም አይደለም፡፡ ይህቺ ምድር እስካለች ድረስ መስዕዋትነታችሁ ያበጀው ቀን ዘለዓለማዊ ነው፡፡ እንኳን አደረሳችሁ፡፡

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top