Connect with us

ምስራቅ ኢትዮጵያን ከቅኝ ገዢ ምኞት ያመከኑት ጀግናው ልዑል ራስ መኮንን ማን ናቸው?

ምስራቅ ኢትዮጵያን ከቅኝ ገዢ ምኞት ያመከኑት ጀግናው ልዑል ራስ መኮንን ማን ናቸው?
Photo: Facebook

ባህልና ታሪክ

ምስራቅ ኢትዮጵያን ከቅኝ ገዢ ምኞት ያመከኑት ጀግናው ልዑል ራስ መኮንን ማን ናቸው?

በኢትዮጵያ ታሪክ ብቻ አይደለም ሰውዬው ከአድዋ አብሮ የሚነሳ ታሪክ ስላላቸው በጥቁር ልጆች የክብር መዝገብ የነጻነት ጀብደኛ በመሆን ስማቸውን በወርቅ አጽፈው አልፈዋል፡፡ የማይፈረስ ታሪክ ብል የማይበላው ስም የማይበሰብስ ክብር ባለቤትም ናቸው፡፡

ቻርለስ ማይክልኮት “በጊዜያቸው ይኖሩ ከነበሩ ታላላቅ ሰዎች ጎላ ብለው የሚታዮት በትክክል ማናቸውንም ጉዳይ ያለአንዳች ስህተት በመፈጸማቸው ነው፡፡” ይላቸዋል፡፡

አባታቸው ደጃዝማች ወልደ ሚካኤል ጉዲሳ ይባላሉ፡፡ በእናታቸው ደግሞ የሳህለ ሥላሴ ወገን ናቸው፡፡ የወይዘሮ ተናኘ ወርቅ ሳህለ ሥላሴ ልጅ፡፡ የተወለዱት በወርሃ ግንቦት አስራ ሦስተኛው ቀን በ1849 ዓ.ም. ሲሆን የትውልድ ስፍራቸውም ደረፎ ማርያም ይባላል፡፡

አባታቸው በልጅነታቸው ነበር ለንጉሥ ምኒልክ በአደራ የሰጧቸው፡፡ ወጣቱ መኮንን ሁሉን የተካኑ ስለነበሩ የንጉሥ ምኒልክን ቀልብ ሳቡ፡፡ በአጭር ጊዜም ባላምባራስነት ማዕረግ አገኙ፡፡ በሃያ አራት አመታቸው ባላምባራሱ ወጣት የወይዘሮ የሺእመቤት ባለቤት ሆኑ፡፡

የራስነት ማዕረጋቸውን ያገኙት ቦሩ ሜዳ ነው፡፡ አድዋ ላይ የነ ራስ ሚካኤልና የነራስ ወሌን ጦር በበላይነት ያዘመቱ የጥቁር ድሉ ኮኮብ ናቸው፡፡

በታዋጊነታቸው ስማቸው ከፍ ብሎ ይነሳል፡፡ በጦር ሜዳ ጀብድ ብቻ ሳይሆን በስልጣኔ ጥማትም ሀገር መስራት የሚመኙ ነበሩ፡፡ በቱርክ ሞግዚትነት የአባይን ማህጸን በእጇ ማስገባት ያሰበችው ግብጽ በምጽዋ በኩል ብቅ ስትል የዮሐንስ አራተኛን ክንድ ቀመሰች፡፡ ዙሪያ ተጠምዛ በታጁራ ዳግም እድሏን ስትሞክርም የአውሳው ሱልጣኔት ክንዱን አቅምሶ ወደ መጣችበት መለሳት፡፡ ራኡፍ ፓሻ የሚመራው ጦር ግን በጂልዲሳ በኩል እየገፋ መጥቶ ተሳካለትና ሐረርን በቁጥጥር ስር ያዘ፡፡ አስር ዓመታትን በሐረር የቆየችው ግብጽ ከዚያ በኋላ ሐረር ምኞቷ ሆና ቀረች፡፡

ሐረር በዐፄ ምኒልክ ሠራዊት ቁጥጥር ስር ስትውል ምሥራቃዊ ቀጠናው ይመሩ ዘንድ በወቅቱ የ35 ዓመት ጎልማሳ የነበሩት ተሾሙበት፡፡ ከዚያ በኋላ ምስራቁ ቀጠና ቀዥ ለሚገዛው ወራሪ ምኞት ብቻ ሆኖ ቀረ፡፡ የሀገር አንዱ ክፍል በታላቁ የጦር መሪ ታፈረ፡፡

ራስ መኮንን ሐረርን ይወዱት ነበር፡፡ እንደ ብዙ ሹማምንት መናገሻ ከተማው ተቀምጠው በርቀት የመሩት ሳይሆን ህዝቡን አብሮ በመሆን ተወደው የመሩ ሰው ናቸው፡፡ ስልጣኔ አብልጦ ያጓጓቸዋል፡፡ ምክንያቱም ልዑሉ የዳግማዊ ምኒልክ መልዕክተኛ ሆነው ወደ አውሮጳ ሁለት ጊዜ ሄደዋል፡፡ የንጉሥ ኤድዋርድ ሰባተኛን የንግስ በዓል ለማክበር ንጉሠ ነገሥቱን ወክለው ወደ ኤሮጳ ሲጓዙ የሲውዘርላንድም የሎንዶንንም ውበትና ስልጣኔ አይተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በተለይም በጦር መሳሪያ ኢንዱስትሪ ራሷን የቻለች ሀገር ካልሆነች የወራሪን አደብ ማስገዛቱ ከባድ እንደሚሆን ቀድመው የተረዱም ሰው ናቸው፡፡ በአውሮጳ ጉብኝታቸው ነጻነትና ብልጽግና ትርጉሙ ምን እንደሆነ ዘልቆ ገብቷቸዋል፡፡

ዘውዴ ረታ ተፈሪ መኮንን ረዥሙ የስልጣን ጉዞ በሚል በጻፉት መጽሐፍ ራስ መኮንን ለመጨረሻ ጊዜ ሀረርጌን ሲሰናበቱ እንዲህ ብለው ነበር ለባለሟሎቻቸው አደራ ያሉት “ከዚህ ቀደም የነገርኳችሁን ልብ በሉ፡፡ መቼውንም ቢሆን እኔ አብሬያችሁ ብኖርም ባልኖርም በሀገራችን ጉዳይ ይህ ጎደለ ይህ ቀረ የሚባል ነገር መኖር የለበትም፡፡ ሁላችሁም በመሃላ በተቀባላችሁት አደራ የአገራችን ዳር ድንበሯ እንዳይደፈር፣ የንጉሠ ነገሥታችን ክብር እንዳይነካ፣ በህዝባቸው ላይ በደል እንዳይደርስ፣ ፍርድ እንዳይጓደል፣ የየድርሻችሁን ሃላፊነት መፈጸም ግዴታችሁ ነው፡፡”

ታላቁ ልዑል ጀግናው ራስ መኮንን በንጉሠ ነገሥቱ ተጠርተው ከሐረር ወደ ሸዋ ሲመጡ በመንገድ ላይ በገጠማቸው ህመም ሳቢያ መጋቢት 12 ቀን 1898 ዓ.ም. ይህቺን ዓለም ተሰናበቱ፡፡ ለምስራቁ የኢትዮጵያ ምድር የነጻነት ምልክት ሆነው የቀኝ ገዢዎችን ቅዠት ያከሸፉት ጀግና ይታሰቡበት ዘንድ በሀረር ከተማ በአባ ቃኘው ላይ ቁጭ ብለው የሚያሳይ የመታሰቢያ ሐውልት ቆመላቸው፡፡ ይኼ ሐውልት ነው በሰሞኑ ግብጽ መራሽ አጀንዳ በጥቂት መንጋዎች እንዲፈርስ የተደረገው፡፡ ራስ መኮንን በኖሩበት ዘመን የማይፈረስ ስምና ታሪክ አኑረዋል፡፡ የማይፈርስ ስምና ታሪክ እያኖረ ሀገር መስራት የቀጣዩ ትውልድ ድርሻ ነው፡፡ ሀገርን ለማፍረስ የሚቃዥ እጁን ወደ ጀግናው ሐውልት ቢሰነዝርም ማስታወስ የሚገባው ከባርነት ያወጡትን ጀግና ውለታ እንዴት እየመለሰ እንደሆነ ነው፡፡

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top