Connect with us

የሳተላይት ምስሎች የህዳሴ ግድብ የውሃ መጠን መጨመሩን አመለከቱ

የሳተላይት ምስሎች የህዳሴ ግድብ የውሃ መጠን መጨመሩን አመለከቱ
(Maxar Technologies via AP)

ዜና

የሳተላይት ምስሎች የህዳሴ ግድብ የውሃ መጠን መጨመሩን አመለከቱ

በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴው ግድብ አካባቢ የተገኙ የሳተላይት ምስሎች በግድቡ ውስጥ ያለው የውሃ መጠን እየጨመረ መሆኑን አመለከቱ።

ይህ 5 ቢሊየን ዶላር ወጪ የሚደረግበት የኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ በኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን መካከል ድርድር እየተደረገበት ነበር።

አዲሱ የሳተላይት ምስል የተወሰደው ሰኔ 20/2012 እና ሐምሌ 5/2012 ሲሆን ግድቡ የሚይዘው የውሃ መጠን በተከታታይ እየጨመረ መምጣቱን ያሳያል።

ቢቢሲ በአካባቢው ካሉ የግብርና ባለሙያዎች በማጣራት እንደተረዳው ግድቡ በሚገኝበት በምዕራብ ኢትዮጵያ ጉባ አካባቢ ከፍተኛ የሆነ የክረምት ዝናብ በመጣል ላይ ነው።

ጋዜጠኛ ቤንጃሚን ስትሪክ የሳተላይት ምስሎቹን በመከታተል እንደገለፀው ምናልባት ግድቡ ከፍተኛ ውሃ መያዝ የጀመረው በአካባቢው በሚጥለው ዝናብ ምከንያት ይሆናል።

የግብጹ አል አህራም ጋዜጣም በአውሮፓ ስፔስ ኤጀንሲ የተነሱ ሳተላይት ምስሎችን መሰረት አድርጎ ግድቡ ውሃ መያዝ የጀመረ መሆኑን አመልክቶ፤ ይህ ግን በአካባቢው በሚጥለው ከባድ ዝናድ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል የክራይስስ ግሩብ ተንታኝ ዊሊያም ዳቪሰንን ጠቅሶ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በሐምሌ ወር ግድቡን በውሃ መሙላት እንደሚጀምር በተደጋጋሚ የገለፀ ሲሆን ግብጽ በበኩሏ ድርድሩ ሳይጠናቀቅ ሙሌቱ እንዳይካሄድ ፍላጎት አላት።

በአፍሪካ ሕብረት አሸማጋይነት ሲካሄድ የነበረው የሦስትዮሽ ድርድር ያለስምምነት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) በትዊተር ገፃቸው የያሰፈሩት ዛሬ ማለዳ ነበር።

እስካሁን በተካሄደው ድርድር መሻሻሎች ቢኖሩም በአጠቃላይ ስምምነት ላይ መድረስ እንዳልተቻለ የገለፁት ሚኒስትሩ፣ በዛሬው ዕለትም አገራቱ የደረሱባቸውን ጉዳዮች ለመሪዎቹ እንዲሁም ሲያሸማግል ለነበረው አፍሪካ ሕብረትም በሪፖርት መልክ ያቀርባሉ ብለዋል።

የሦስቱ አገራት ድርድር
ሦስቱ አገራት ሲያደርጉት የነበረው ለዓመታት የዘለቀው ድርድር ያለምንም ውጤት ሲንከባለል መጥቶ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ሙሌትን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እጀምራለሁ ማለቷን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገባ ግብጽ መጠየቋ የሚታወስ ነው።

ድርድሩ በአፍሪካ ሕብረት ሸምጋይነት ለኢትዮጵያ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት የተባለ ሲሆን፤ የግድቡ ውሃ አሞላልና አለቃቅ፣ የድርቅ የውሃ ስሌት፣ የግድቡ አስተዳደርና ቁጥጥር፣ የግድቡ ደኅንነት ጉዳዮችን በተመለከተም የአገራቱ ቴክኒክና ሕግ ባለሙያዎች እየተወያዩ ነበር ተብሏል።

በአስረኛው ቀንም የሦስቱ አገራት የውሃና መስኖ ሚኒስትር የቴክኒካልና ህጋዊ ኮሚቴ ውይይቶችን መገምገማቸውንም የግብጽ የውሃና መስኖ ሚኒስቴርን ጠቅሶ ‘ኢጅፕት ቱደይ’ ዘግቧል።

በተለይም በባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ ስምምነት ያልተደረሳባቸው ጉዳዮች ለሌላ ጊዜ ይተላለፉ ማለታቸው ከግብጽ በኩል ተቀባይነት አለማግኘቱንም ዘገባው አስነብቧል።

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ከሰሞኑ ለአገሪቱ ሚዲያዎች በሰጠው መግለጫ ድርድሩ ፍሬ አልባ እንደነበር ገልጿል።

አረብ ኒውስ በበኩሉ ኢትዮጵያ ለአወዛጋቢዎቹ የሕግ እና ቴክኒካዊ ጉዳዮች አማራጭ ሃሳቦችን ብታቀርብም በግብጽ ዘንድ ተቀባይነት እንዳላገኘ ዘግቧል።

ኢትዮጵያ የአማራጭ ሃሳቧን በስምንተኛው የድርድር ቀን ማቅረቧን የገለፀው ዘገባው ስምምነት ያልተደረሰባቸውን ጉዳዮችንና ስምምነቶቹ ተግባራዊ መሆናቸውንም ለማየት አንድ የቴክኒክ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደዚያ እንዲያመራ ማሰቧን ዘግቧል።

ግብጽ በበኩሏ ድርቅና የድርቅ ውሃ ስሌትን በተመለከተ አማራጭ ሃሳብ ማቅረቧን የውሃና መስኖ ሚኒስትሩን ጠቅሶ ዘግቧል። ቴክኒካል ጉዳዮችንም በተመለከተ አንዳንድ መሻሻሎች መኖራቸውንም የሱዳን የውሃና መስኖ ሚኒስቴርን ዋቢ በማድረግ ዘገባው አስነብቧል።

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top