Connect with us

ከአንተና ከእኔ የሚጠበቀው

ከአንተና ከእኔ የሚጠበቀው
Hachalu Hundessa dressed in traditional costume in Addis Ababa, Ethiopia, in 2019.Credit...Tiksa Negeri/Reuters

ህግና ስርዓት

ከአንተና ከእኔ የሚጠበቀው

ከአንተና ከእኔ የሚጠበቀው
(ጫሊ በላይነህ በድሬቲዩብ )

ጤናይስጥልኝ፤ እንኳን በሠላም ለመገናኘት በቃን። ኢንተርኔት መዘጋቱ ምንም እንኳን ጉዳቱ ከፍተኛ ቢሆንም ከሀገር ደህንነት አንፃር ተገቢ ነበር። እንዲህ በሠላም ተገናኝቶ “እንደምን ከረምክ/ከረምሽ” ለመባባልም በቅድሚያ የእኛ የምንላት ሀገር ሊኖረን ያስፈልጋል።

ከሳምንታት በፊት የፓለቲካ ሹኩቻችንን መስመር መሳት ትልቅ ማሳያ የሆነው የወንድማችን አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ሞት ብዙ ነገር አሳይቶናል። የኢትዮጵያ ጠላቶች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ባፈሩዋቸው ባንዳ ተላላኪዎቻቸው በኩል ሊያጠፉን ክብሪቱን ለኩሰው አይተናል። የአርቲስቱን ሞት ተከትሎ በሰአታት ጊዜ ልዩነት ውስጥ የተቀነባበረና ተመሳሳይ ጥቃት ውስጥ የተገባው እንዲሁ በተራ ገጠመኝ አልነበረም። ጠላቶቻችን አስቀድሞም እንደተዘጋጁበት ክስተቶቹ በቂ ምስክር ነበሩ።

በአሁን ሰአት ለደህንነት ሲባል ተዘግቶ የከረመው የማህበራዊ ሚድያ ተከፍቷል። ለሀገር ጥፋት የደገሱ ሀይሎች ሌላ ዙር “የተነስ ታጠቅ” ቅሰቀሳ መጠቀሚያ አድርገውት መከራችንን እንዳያረዝሙት መከላከል የእኔ እና የአንተን ብርቱ ጥረትን ይጠይቃል። በተለይም የፌስቡክ መከፈት ተከትሎ አንዳንድ ለኦሮሞ ህዝብ ራሳቸውን ተቆርቋሪ አድርገው የሾሙ ግለሰቦች እና ዘራፊው የህወሓት ቡድን ያሰማራቸው ተከፋይ ብሎገር ተብዬዎች ያልተቀደሰ ጋብቻ መስርተው አሁንም መርዝ መትፋታቸውን መቀጠላቸው የማይቀር ነው። ብዙዎቹ በአሜሪካ እና በአውሮፓ ተቀምጠው ሠላማዊ ኑሮአቸውን እያጣጣሙ የኦሮሞን ወጣት በእሳት ሊማግዱ የአዞ እምባቸውን እንደሚረጩ የሚጠበቅ ነው።

ይኸን የጥፋተኞች መንገድ በአስተማማኝ መልኩ መግታት የእኛ የኢትዮጵያውያን ሀላፊነት ነው። የተረጋጋችና ሠላሟ የተጠበቀ ሀገር እንድትኖረን የምንሻ ኢትዮጵያውያን በዚህ ረገድ ልንተባበርና በአንድ ልንቆም ይገባል።
እናም እኔና አንተ ምን ልናደርግ እንችላለን?ተከተለኝ?!…

በአሜሪካ እና በአውሮፓ ያላችሁ ወገኖቼ፤ በቅድሚያ ትብራችሁን አጠናክሩ። እንዲህ አይነቱን ተነሳሽነት ሌሎች ሰዎች እስኪያደርጉት አትጠብቁ። የጥንካሬያችሁ ምንጭ ትብብር እና በአንድ መቆም ብቻ መሆኑን ለአፍታም አትዘንጉ። በፍጥነት ተገናኙና ተነጋገሩ። አንተም፣ አንቺም ዛሬውኑ ልትጀምሩት ትችላላችሁ። ስትገናኙ የጋራ ዓላማ እና ግብ ቅረፁ። ለሚያስፈልጋችሁ አስተዳደራዊ ወጪዎችም የወገናችሁን ድጋፍ እየጠየቃችሁ ሥራችሁን ግን ቀጥሉ። በተራጀና በሰለጠነ መንገድ የጥፋት መንገድ የተከተሉ የፌስቡክ አርበኞችን መለየት የመጀመሪያ ሥራችሁ ይሁን። እነዚህ የጥፋት ሀይሎች ለማስታገስ ሥራዎችን ተከፋፈሉ።

አንድ ቡድን የግለሰቦቹን ፅንፍ የወጣ ጦረኛ ቅስቀሳ ለፌስቡክ ኩባንያ በተደጋጋሚ ሪፖርት በማድረግ ገፃቸው እንዲዘጋ ተከታታይ ሥራዎችን ይስራ። ሌላኛው ቡድን ግለሰቦቹን በአካል በማግኘት ከጥፋታቸው እንዲቆጠቡ ይምከር፣ ያስመስክር። ሌላኛው ቡድን እነዚህ የጥፋት ቡድኖች በህግ ለመጠየቅ የሚያስችል በቂ ዝግጅት ያድርግ። አደገኛ የሆኑትን በመለየትም በፍርድ ቤት ክስ ያቅርብ።

በሀገር ውስጥ ያላችሁም ወገኖች ብትሆኑ በተለይም በብዕር ስም እና በውሸት ፎቶዎችን በመለጠፍ የግጭት ቅስቀሳዎች የሚያደርጉ ግለሰቦች ተከታተሉ። እያንዳንዱን ፖስታቸውን ስክሪን ሹት በማድረግ እርኩስ ተግባራቸውን በማጋለጥ ወጣቱ እንዲወያይበት እድል ፍጠሩ። በተጨማሪም በእያንዳንዱ ፖስታቸው ስርም የድርጊታቸውን ህገወጥነት ከመንገር ጎን ለጎን ማንነታቸውን ለማወቅ የተቻላችሁን አድርጉ። ስለሰዎቹ ማንነት ፍንጭ ስታገኙ ለፖሊስ መረጃ በመስጠት የዜግነት ግዴታችሁን ልትወጡ ትችላላችሁ።

ወገኖቼ፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሀገሩን ደህንነትና ሠላም ለመጠበቅ የአቅሙን ማበርከት ያለበት ጊዜ ቢኖር አሁን ነው። ፀረ ኢትዮጵያ ሀይሎች እንደፈለጉ ሊቦርቁ፣ ህዝብንም እርስ በርስ በማጋጨት ንግዳቸውን ሊያጧጡፉ እንደማይችሉ በግልፅ መንገር፣ ማስጠንቀቅ፣መታገል ከእኛ ከኢትዮጵያውያን ይጠበቃል። መንግስታችንም በዚህ ረገድ ይበልጥ እንዲሰራ ማገዝ የምንችለው እኛም የድርሻችንን ስንወጣ ብቻ ነው።

ወገኖቼ በሉ ወደሥራ?!

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top