Connect with us

«ሰማይ ቢቀደድ ሽማግሌ ይሰፋዋል»

«ሰማይ ቢቀደድ ሽማግሌ ይሰፋዋል»
Photo: Social Media

ባህልና ታሪክ

«ሰማይ ቢቀደድ ሽማግሌ ይሰፋዋል»

ኢትዮጵያውያን ለሽምግልና ትልቅ ክብር ይሰጣሉ። በሽምግልና ያምናሉ፤ ችግሮቻቸውን በሽምግልና ይፈታሉ። ቂምና ቁርሾ ሁሉ የሚሽረው በሽምግልና በሚካሄድ እርቅ ነው። ሽምግልና ካለው ክብርና ተቀባይነት አንጻር ‹‹ ሰማይ ተቀደደ ቢሉ ሽማግሌ ይሰፋዋል›› እስከማለት ይደርሳሉ። በኢትዮጵያዊ ባህል ከሽምግልና የሚያመልጥ ነገር እንደሌለ ይታመናል።እንደውም ሽምግልና አመጣጡ ከሰው ልጅ አብሮነት ጋር እንደሆነም ይገለጻል። ሰው ከሰው ጋር አብሮ ሲኖር ግጭት ይፈጠራል።እናም ያ ግጭት ከሮ አደጋ እንዳያስከትልና ቂምና ቁርሾ እንዳይያዝበት ሽምግልና ደም በማድረቅ ወሳኝ ሚናውን ይጫወታል።

ሽምግልና እንደየአካባቢው ባህልና አኗኗር ይለያያል።ነገር ግን በሁሉም ደረጃ ሰላም መፍጠር ነው ዋነኛ መሰረቱ ።ታዲያ ይህ ስርዓት አገር አቀፋዊ ብቻ ነው ወይስ ዓለም አቀፋዊ ፤ ፋይዳውስ የሚሉና መሰል ሀሳቦችን በማንሳት ከተለያዩ ባለሙያዎች ጋር ቆይታ አድርገናል።

በጉዳዩ ላይ መጀመሪያ ማብራሪያ የሰጡን የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ናቸው። እሳቸው እንዳሉት፤ ሽምግልና ከእድሜ ትልቅነት ጋር የተያያዘ ብቻ አይደለም።በግጭት ምክንያት የተጣላን ሁሉ የማስማማት ጉዳይ ነው።በእውቀት መብሰልንም መሰረት ያደርጋል።በመሆኑም በአገር ደረጃ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ክዋኔ ነው ይላሉ።

ሽምግልና የሰው ህይወት እንዳይጠፋ፣ አገር በኢኮኖሚውም ሆነ በፖለቲካው ችግር ውስጥ እንዳትገባ አለኝታ የሚሆን ስርዓት ነው። ይህ የሽምግልና ዋጋ በተለይም በኢትዮጵያውያን ዘንድ ለየት ያለ ግምት የሚሰጠው እንደሆነ ይገልጻሉ።ሌሎች ዓለማት የሁሉም ሀሳብ እንዲደመጥበት ለማድረግ የጸጥታው ምክር ቤትንና የመሳሰሉትን በማቋቋም ችግሮችን ይፈታሉ።እንደ ኢትዮጵያውያን ግን በዚህ መልኩ ሳይሆን ህብረተሰቡ ውስጥ አብሮ በመኖር ህይወቱ ሆኖ ችግር የሚፈታበት የሽምግልና ስርዓት መሆኑን ያነሳሉ።

ሽምግልና ማለት ‹‹ሸምጋዩ›› በራሱ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ ከፈጣሪ ዘንድ በረከት ለማግኘት የሚከወንበት የእምነት ስርዓት ነው።በመጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ የሚያስታርቁ ብጹአን ናቸው፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ በረከትን ያገኛሉና›› እንደሚባለው ሸምጋዮች ይህንን ለማግኘት የሚሞክሩበት ነው።ብዙ ማህበረሰብ በሽማግሌዎች ላይ ተስፋ የሚጥለው ከአምላክ የተቀቡና ፤ ለእኛ በረከትን የሚያሰጡ ናቸው ብሎ ስለሚያምንባቸውም ነው።ጉልበት ያለው አቅሙ የደከመን እንዳይበድለው ለማድረግም የሚውል ዘዴ ነው ሽምግልና።ይሁንና የፈጠርነው ትውልድ የሚያዳምጥ ባለመሆኑ የተነሳ ብዙ ነገሮች በውጤት እየተደገፉ አልሄዱም።የሽምግልና ታሪክን አዛብተን ተርከንለት የተሻለ እሳቤ እንዳይኖረው ሆኗል።በተለይ እናትና አባትን ከማክበር ጀምሮ ባለመሰራቱ ለሽማግሌዎች የሚሰጠው ዋጋ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መጥፋቱን ያነሳሉ።

የሽምግልና ስርዓታችን ቀደም ሲል ወደነበረበት ክብር ለመመለስ መጀመሪያ ቤተሰብ ልጁ ላይ ይስራ፤ በስነምግባር እያነጸ ያሳድግ፣ የአገርን ዋጋ ይንገረው።ከዚያ ደግሞ የእምነት ተቋማት ስለሚረከቡት ቀሪውን ዕድሜ ደግሞ እነርሱ ሊያንጹና ኮትኩተው ሊያሳድጉ ይገባል።ይሄ ውጤታማ የሚሆነው ወላጆች፣ የሃይማኖት ፣ መምህራን… ራሳቸው አርአያ መሆን ሲችሉ ነው።

ሌላው ያነሱት ደግሞ የመንግሥትን ኃላፊነት ነው። መንግሥትን ከሥርዓተ ትምህርቱ ጀምሮ ትውልድ ቀረጻ ላይ እንዲሰራ ማድረግ አለበት።ዛሬ የተበላሸውን ትውልድ አሁን መመለስ ባይቻል እንኳ ነገ ሌላ ትውልድ ፣ አገር ወዳድና ለሽማግሌዎች የሚታዘዝ ይፈጠራልና ሁሉም ኃላፊነታቸውን ይወጡ ሲሉ ያሳስባሉ።

ሌላው ሀሳባቸውን ያካፈሉን ደግሞ የህክምና፣ የስነልቦና እና የሥነ-መለኮት ባለሙያው ዶክተር ወዳጄነህ ማህረነ ናቸው።ሽምግልና በመኖር ውስጥ ላሉ ግጭቶች ሰላም መፍጠሪያ ስርዓት ነው።በየእለት ከዕለት ኑሯችን ብዙ ግጭቶች ከሰዎች ጋር ልንፈጥር እንችላለን።በዚህም

ሽማግሌ ሦስተኛ አካል በመሆን መፍትሄ ሊሰጠን ይመጣል።ግጭቱ ግለሰብ ከግለሰብ፤ ከአለቃ ፣ ሹፌር ከተሳፋሪ ፣ መንግሥት ከመንግሥት ፣ ጎሳ ከጎሳ ጋር ወዘተ ሊሆን ይችላል።እናም ሸምጋዮችም በዚያው ልክ እንደ ጉዳዩ ክብደት ጓደኛ፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች ፣ የመንግሥት ባለስልጣናትና ሙያተኞች እንደየሁኔታው ጉዳዩን አጥንተውና መፍትሄ ሰጥተው ስምምነት ላይ ያደርሳሉ።

‹‹ሽምግልና እንደየ አይነቱና ቦታው ይለያያል›› የሚሉት ዶክተር ወዳጄነህ፤ ሦስት አይነት አካሂዶች በዋናነት ጥቅም ላይ እንደሚውል ይናገራሉ ።ይኸውም የመጀመሪያው ተሸማጋዮቹ በነፃነት ሃሳባቸውን እንዲሰነዝሩ በማድረግና በራሳቸው ጊዜ እርቅ እንዲያወርዱ የሚደረግበት ነው።በዚህ ላይ ሽማግሌዎቹ የመነጋገሪያ መድረክ በመፍጠርና ሃሳባቸውን ይበልጥ እንዲያወጡ ያደርጋል እንጂ ውሳኔ አያሳልፉም።

ሁለተኛው ደግሞ ተሸማጋዮቹ የሚግባቡበትን መንገድ በመፍጠር፣ ማስረጃዎችን በማሰባሰብ እና በዚያ ላይ ተመርኩዞ ውሳኔ የሚያሳልፉበት ነው።በዚህ ላይ መንፈሳዊ እምነትም ሊታከልበት ይችላል።

ሌላው ሦስተኛውና የመጨረሻው በህግ የሚከወነው ሲሆን፤ ይህንን በአብዛኛው በመንግሥት የሚደረግ ነው።ይሁንና የአገር ሽማግሌም ችግሩን የሚፈታበት አጋጣሚ እንዳለም ይናገራሉ።

ወደ አገራችን ስንመጣ ደግሞ ሽምግልና የተለየ ትርጉም እንደሚሰጠውና ከጊዜ ወደ ጊዜ ልዩነት እያሳየ እንደመጣ ይታያል።በባህላችን ዘንድ ሽምግልና ትልቅ ዋጋ የሚሰጠውና በህዝብ መካከል ማህበራዊ ትስስርን የምንፈጥርበት ነው።የሚመረጡ ሽማግሌዎች በማህበረሰቡ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው፣ የሚፈሩ፣ የሚደመጡና የሚታፈሩ በመሆናቸው ከእነርሱ ማንም ሊወጣ የማይቻልበት ነው።እነሱ ባቀረቡት ሀሳብ ላይ በመነጋገር እና በመተማመን ስምምነት ላይ የሚደረስበት መሆኑን ይናገራሉ።

በመንግሥት በኩል የተፈጠሩ ችግሮች ግን ‹‹አንተም ተው አንተም ተው›› በሚል የሚታለፍ እንዳልሆነ የሚያነሱት ዶክተር ወዳጄነህ፤ ይህ ሁኔታ ሽማግሌዎች እንዲፈረጁና የአንድ አካል ወገንተኛ እንዲመስሉ አድርጓቸዋል ።በተለይም ፖለቲካዊና ጠንከር ያሉ አለመግባባቶችን በደንብ ሳያዩ፣ እርቅ የሚፈጥረው አካል ያለውን አመለካከትም ሳያጤኑ መግባታቸው ተአማኒነታቸውን ጥያቄ ውስጥ እንደከተተው ይገልጻሉ።

ለውጤታማ ሽምግልና እነዚህ ነገሮች መሰረታዊ ሊሆኑ ይገባል ሲሉ ይመክራሉ።ይህ ባለመሆኑ ለግጭቶች መክረር፤ ሁሉም የራሱን ቦታና የራሱን ሀሳብ ይዞ እንዲመጣና ቁርሾው የበለጠ እንዲገን ያደርገዋል። ትልልቅ ጉዳዮች ሲሸመገል ጥልቀት ያለው ጥናት ማድረግ፣ አካሂዶችን በሚገባ ማወቅ ይገባል።ስልጣን ላይ ያለው መንግሥት ውሳኔ፣ ህዝቡ የሚፈልገውና ፖለቲከኞች የሚያነሱት ሀሳብ በሽምግልና ስርዓት ውስጥ በትክክል በጥናት ተመርኩዞ በሃሳብ እንዲግባቡ መደረግ ይኖርበታል።ይህ የማይደረጉ ከሆነ ግን ውጤታማነቱ ጥያቄ ውስጥ ይገባል።ስለሆነም አገራዊ መግባባትን አምጥቶ በሽምግልና ባህላችን ውጤት ለማምጣት ጉዳዩን በጥልቀት መረዳት ቀዳሚ መሆን እንዳለበት ይናገራሉ።

‹‹ሽምግልና በባህላችን የሚበረታታና የኖርንበት ነው።በዚያ ላይ ሃይማኖተኛ በመሆናችን እንደሽማግሌ አምነን ሃሳባችንን የምናካፍለው የለም።ስለሆነም እኛ ለእርቅ ቅርብ ነን።ግን የፖለቲካው ጣልቃ ገብነት በምንረዳው መልክ ሊሆን ይገባል። ቀደምት ታሪኮቻችን እንደሚነግሩን ነገስታት እርቅ ለመፈጸም ሽማግሌዎችን በደንብ ተጠቅመውባቸዋል። በተለይ በሃይማኖት መሪዎች ብዙ ግጭቶች መፍትሄ አግኝተዋል፤ ደም መፋሰሶች ቆመዋል፤ አገሪቱ ችግር ውስጥ እንዳትገባ አድርጓል።ግን ስልጣን ላይ በተቀመጠው አካል እያደር ፈተና ገጥመውታል።ለዚህም አብነት የሚሆነን የደርግ መንግስት ነው ›› ሲሉ ያስረዳሉ።

ደርግ ‹‹አሸናፊ ነኝ፤ ማንም ሊነካኝ አይችልም›› ብሎ ራሱን በማስቀመጡና ሽማግሌዎችን ‹‹ ይህ የባልና ሚስት ጉዳይ ሳይሆን የአገር ጉዳይ ነው›› ሲል በመመለሱ ወርቅ የሆነው የሽማግሌዎች ሀሳብ ቀርቶበታል።በዚህም ለውድቀት ተዳርጓል።እናም ዛሬ የሽማግሌዎች ምክርና ተግሳጽ የተለየ ዋጋ እንዳለው በማሰብ ለሁሉም አገራዊ ችግር መፍትሄ ልናደርገው ይገባል።ይህ የሚሆነው የሰዎቹን ማንነት ማስተካከል ሲቻል እንደሆነ ዶክተር ወዳጄነህ ይናገራሉ።

አገራችን ብዙ ያልወጡና ያልታወቁ፣ ለማንም የማይወግኑ፣ በህይወታቸው፣ በአመለካከታቸው የተሻሉ፣ በሁሉ ነገራቸው አርአያ የሚሆኑ፤ ለራሳቸው ሳይሆን ለሾማቸው ክብር የሚቆሙ፣ በእግዚአብሔር ፊት እንደሚቆሙና ፍርድ እንደአለባቸው እያመኑ የሚያደርጉ፣ ነገሮችን ሁሉ በመንፈሳዊ ዓይን የሚመለከቱ፣ ፖለቲካዊ ንክኪ የሌለባቸው ሽማግሌዎች አሏት።ስለዚህ የሚታወቁትን ብቻ ሳይሆን እነዚህንም በመጠቀም ታሪካችንን ልናስቀጥለው እንደሚገባም ይመክራሉ።

‹‹ ሽምግልና በሁለትና ከዚያ በላይ ባሉ ሰዎች አማካኝነት የሚከናወን ጥላቻን በማራቅ ፍቅርና ይቅርታን በልብ ውስጥ በመዝራት የሚፈጸም ባህላዊ የእርቅ ስርዓት ነው›› ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ጥናት ከፍተኛ ባለሙያ መምህር መክብብ ገብረማርያም ናቸው። ይህ ባህል የሀሳብ መላቅ፣ መምከርና መመረቅ ያሉበት ስርዓት ነው።ማህበረሰቡም መልካሙን ሁሉ በእነርሱ ምርቃት እንደሚያገኝ በማመን ተበድሎ እንኳን ሽምግልናው ይሻለኛል ብሎ የሚመርጠው ነው።በዚህም እርቅና ሰላም ይወርዳል።ይሄ ደግሞ በተለይ ተተኪው ትውልድ በመልካም ስነምግባር ታንጾ እንዲያድግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል።

እስከዛሬ በምናየው ማህበራዊ መስተጋብሮች በፖለቲካው፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ብዙዎች ግጭት ውስጥ ገብተዋል።ቅራኔና ቁርሾ ተፈጥሯል። ሆኖም ግን ኢትዮጵያውያን ለባህላዊ ሽምግልና ልዩ ቦታ ይሰጣሉና ለያዥ ለገናዥ ያስቸገረውን ‹‹ አንተም ተው፤ አንተም እርሳው›› በማለት በእርቅና በግሳጼ ሰላም እንዲሰፍን ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ሽምግልና ሰላምን ሲያሰፍን ጥላቻና ቂምን ያጠፋል።ደም መመለስ ይቆማል።እርቁ ሲካሄድ ተመርቆም ፣ ተረግሞም የሚከናወን በመሆኑ አምላክ ፍርዱን ይሰጣል ተብሎ ስለሚታመንበትም ሸምጋዮች ያሉት ተቀባይነት ይኖረዋል።ይሄ በፍጹም ፍቅር የሚያልቅ እርቅ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

መምህር መክብብ እንደሚሉት፤ ሽምግልና ዓለም አቀፋዊ ነው። ሁለት ያልተቀራረቡና ቅሬታ ውስጥ የገቡ አገራትን በፖለቲካው መስመር አሊያም ተሰሚነት ባላቸው አካላት ሙያዊ በሆነ ቋንቋ ተግባብተው ወደ አንድ እንዲመጡ ማድረጊያ የድርድር መንገድ ነው።ስለዚህም ዓለም አቀፋዊ ሲሆን፤ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን በደምብ በሚያሳምኑ ሙያተኞች አለያም ተደራዳሪ የመንግሥት አካላት የሚከወን ነው።

ሽምግልና ትክክለኛ ባህሪውን የሚይዘው ግን አገራዊ ሲሆን መሆኑን ይናገራሉ።ምክንያቱም ባህላዊና ሃይማኖታዊ መንፈስ ይታከልበታል።አተገባበሩም ልዩ ልዩ ነው። ግቡ ግን እርቀሰላም ማውረድ ነው።

ሽምግልና በአገራችን ደረጃ ህግ ሆኖ በማህበረሰቡ ልብ ውስጥ የተጻፈ ነው የሚሉት መምህር መክብብ ፤ እርጥብ ሳር በእጃቸው ይዘው ብቅ በማለት ብቻ አስፈሪ ግጭትን በአንድ ጊዜ ያቆሙትን የጋሞ አባቶች ማስታወሱ ለዚህ በቂ ማሳያ መሆኑን ይጠቅሳሉ።ወጣቶችም ለአባቶች ታዛዥ መሆናቸውን አሳይተዋል።ስለዚህ ሽምግልና ቂም በቀል የማይኖርበት፣ ደም የሚደርቅበት፣ በትዳር ተሳስሮ የሥጋ ዝምድና የሚፈጠርበት ባህላዊ ጥበብ ነው።

ሽምግልና ቀደም ሲል በመሳፍንቱና በመኳንንቱ ዘመን እስከ መስቀል ተሸክሞ የሚለመንበት በመሆኑ ማንም ነገር በእንቢተኝነት የሚቋጭ አልነበረም።እንደውም ለሀገር ሰላም ፣ለአንድነት እና ለህዝቦች ፍቅር ግቦች ማሳኪያ ሆኖ ነው የቆየው።አሁን ግን ብዙ ግድፈቶች ይታዩበታል።ለዚህም ዋነኛው ችግር የፖለቲካው ጣልቃገብነትና የሸምጋዮቹ ማንነት መሆኑን ይገልጻሉ።በዚያ ላይ መንግሥት ውሳኔ ባስተላለፈበት ጉዳይ ላይ እንዲወያዩ ይደረጋል።ህዝቡም ለይስሙላ ስለሚያደርገው ቂሙን ከውስጡ አያወጣውም ይላሉ።

የመንግሥት ባለስልጣናት ሽምግልናን ራሳቸው አምነውበት አይደለም ወደ ባህሉ የሚቀላቀሉት።በግዴታ እነርሱ ያላመኑትን ሌሎች እንዲያምኑላቸው ይጥራሉ።ስለዚህም ከልብ በሌለ ሁኔታ ስምምነት ተደርጓል ተብሎ ይተዋል።ይህ ደግሞ እንቁ የሆኑ ሽማግሌዎቻችንን ዋጋ እንዲያጡ አድርጓቸዋል።ክብርና ሞገስ ኖሯቸው ህዝብም እንዳይታዘዝላቸው እንቅፋት ይፈጥሯል።እናም ትክክለኛ ባህላችንን ለመተግበር ፖለቲካዊና ህዝባዊ ሽምግልናን አናቀላቅል።አርአያ የሚሆኑ አባቶች በራሳቸው የሚሰሩበትን እድል እንስጣቸው መልዕክታቸው ነው።

አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2012

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top