Connect with us

ዋልታ ቴሌቭዥን፤ የፍርድ ቤቶች ጣልቃ ገብነት እንቅፋት ሆኖብኛል አለ

ዋልታ ቴሌቭዥን፤ የፍርድ ቤቶች ጣልቃ ገብነት የምርመራ ዘገባዎችን ለመሥራት እንቅፋት ሆኖብኛል አለ
Photo: Social Media

ህግና ስርዓት

ዋልታ ቴሌቭዥን፤ የፍርድ ቤቶች ጣልቃ ገብነት እንቅፋት ሆኖብኛል አለ

የመገናኛ ብዙሃን ተቆጣጣሪው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን በበኩሉ ፍርድ ቤቶች ዘገባዎች እንዳይተላለፉ የሚጥሉትን እገዳ በተመለከተ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል።

የዋልታ ቴሌቪዥን “ዋልታ ምርመራ” በተሰኘ ፕሮግራሙ በሰብዓዊ መብት፣ መልካም አስተዳደር እና በሙስና ጉዳዮች ላይ የተለያዩ የምርመራ ዘገባዎችን ያቀርባል።

ይሁን እንጂ ተቋሙ በሚሰራቸው የምርመራ ዘገባዎች ላይ “እጃቸው የረዘመ ፈርጣማ ክንዶችና የፍርድ ቤት ጣልቃገብነት” ፈተና እንደሆነበት ይገልጻል።

የተቋሙ የምርመራ ዘገባ አዘጋጅ ጋዜጠኛ ብርሃኑ ወልደሰማያትና ረዳት አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጀማል መሀመድ እንዳሉት፣ በኢትዮጵያ የምርመራ ዘገባዎችን መሥራት የማይታሰብ ሆኗል።

የምርምራ ዘገባዎች ሲሰሩ በአንድ በኩል ከማስረጃዎቹ ጀርባ የተደበቁ በጉልበት፣ በገንዘብ ወይም በሥልጣን የፈረጠሙ ክንዶች አደጋ እየፈጠሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ዋልታ ቴሌቪዥን መረጃዎችን ከሁሉም አቅጣጫ አጣርቶ የሕዝብ ቅሬታዎችን እየሰራ ቢሆንም በአቋራጭ በፍርድ ቤት በኩል በሚመጣ እገዳ ዘገባዎች እንዳይተላለፉ እየተደረገ ነው ብለዋል

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተደረገውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በአፋር ክልል በአፍዴራ ጨው ላይ የሚደረገውን ምዝበራ በተመለከተ የተዘጋጁ የምርመራ ዘገባዎች ለሕዝብ ሳይደርሱ በፍርድ ቤት እግድ ተጥሎባቸዋል ብለዋል ጋዜጠኞቹ።

በተመሳሳይ በሶደሬ ሪዞርት ዙሪያ የቀረበውን ቅሬታና ሌሎች ተያያዥ ዘገባዎች በፍርድ ቤት እግድ ተጥሎበታል ነው ያሉት።

ፍርድ ቤቶች ለቆሙለት ዓላማ ለእውነትና ለፍትህ መሥራት ሲገባቸው በተቃራኒው መቆማቸው ትክክል አለመሆኑንም ጋዜጠኞቹ ገልጸዋል።

የምርምራ ዘገባዎችን ከሁሉም ወገን ለማጣራት ጥረት እንደሚደረግ ገልጸው፤ በዘገባው ላይ ስህተት ከፈጠረ ስህተቱ በዝርዝር ቀርቦ በማስረጃ በሕግ መጠየቅ ይገባው ነበርም ሲሉ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን በተሰጠው ሥልጣን መሠረት እየደረሰብን ያለውን በደል ሊያይልን ይገባል በማለትም ጋዜጠኞቹ ጠይቀዋል።

የባለሥልጣኑን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ በበኩላቸው “ጉዳዩ ከብሮድካስት ሥልጣን ውጭ በመሆኑ ምላሽ መስጠት አልችልም” ብለዋል።

ጠበቃና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ወንድሙ ኢብሳ ጋዜጠኛ በቦታው ተገኝቶ በማስረጃ የሚያቀርባቸው ዘገባዎች የአስፈፃሚው አካል አጋዥ ናቸው ብለዋል።

በመሆኑም የመገናኛ ብዙሃን የሚሰሯቸውን ዘገባዎች ለሕዝብ ከመድረሳቸው በፊት እንዳይተላለፉ ማድረግ በሕግም ተቀባይነት የለውም ነው ያሉት።
ፍርድ ቤቶች የእግድ ትዕዛዝ ለማስተላለፍ ከሳሽና ተከሳሽ ቀርበው ማስረጃዎችን ከተመለከተ በኋላ መሆን እንዳለበትም ገልጸዋል።

ተቋማት ወይም ግለሰቦች ትዕዛዝ የሚተላለፍባቸው ቢያንስ ሦስት ጊዜ መጥሪያ ከቀረበባቸው በኋላ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ምንጭ:- ኢዜአ፣ ኢኘድ

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top